Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊጉዞ ወደ ቀበሌ ቤት . . .

ጉዞ ወደ ቀበሌ ቤት . . .

ቀን:

ዕድሜያቸውን በመጎሳቆል እንዳሳለፉት ፊታቸው ይመሰክራል፡፡ በጭስ እና ዕረፍት በማጣት የዓይናቸው ዕይታ ደብዝዟል፡፡ የሚያውቋቸው ሰዎች ሰላምታ ሲያቀርቡላቸው፣ ‹‹ልጄ ደህና ነሽ? ምነው ጠፋሽሳ?›› እያሉ ሰላምታ ሲሰጡ ያገኘናቸው ወ/ሮ ዘሐራ መሐመድ የሚጦር ወዳጅ፣ ዘመድና ልጅ እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት ቀጣና አንድ አካባቢ ከዘጠኝ ዓመታቸው ጀምሮ የቦረቁበት ነው፡፡ ሆኖም ቀድሞ የነበሩበትን የቀበሌ ቤት ‹‹ቁጥር በማጥፋት በጥገኝነት እንዲኖሩ በኋላም እንዲወጡ መደረጋቸው›› እዚያው አካባቢ በላስቲክ ቤት ቀልሰው እንዲኖሩ አስገድዷቸዋል፡፡

ወ/ሮ ዘሐራ እንጀራ ጋግረው በመሸጥ ይተዳደሩ ነበር፡፡ ኋላ ላይ ደግሞ ጧሪ ልጅና ዘመድ በማጣታቸው ከማኅበረሰቡ የሚያገኙትን እየበሉና እየለበሱ ከላስቲክ ጎጆዋቸው ጎናቸውን ያሳርፉ ነበር፡፡

የቀበሌ ቤት ዕድል ለማግኘት ሲጠባበቁ ረዥም ዓመታት እንዳለፉ የሚናገሩት እናት፣ አሁን ባለዕድለኛ ሆነዋል፡፡ በሕገወጥ የተያዙ የቀበሌ ቤቶች እየተለቀቁ በመሆናቸው፣ አንገት ማስገቢያ አግኝተዋል፡፡ ሌሎች ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው ሰዎች የእሳቸው ዕድል እንዲገጥማቸውም ይመኛሉ፡፡

‹‹ከዚህ ቀደም በወረዳው ከተለያዩ ቦታዎች መጥተው አንድ ወር ሳይቆዩ የቀበሌ ቤት ሲያገኙ፣ እኔ ፀጉሬ እስኪሸብት በኖርኩበት ሰፈር ዳስ ወጥሬ ስኖር ነበር፤›› ይላሉ፡፡ አሁን ዕድል ቀንቷቸው ከተለቀቁት የቀበሌ ቤቶች የአንዱ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ለዚህም ከአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ቁልፍ ተረክበዋል፡፡

ጥር 26 ቀን 2013 ዓ.ም. በአራዳ ክፍለ ከተማ በሕገወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ የቀበሌ ቤቶችን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች ሲተላለፉ ተጠቃሚ ከሆኑት፣ በሰባት ዓመቱ ከዝዋይ ከተማ እንደመጣ የሚናገረው አቶ ደምሰው ነጋሽም ይገኝበታል፡፡ አቶ ደምሰው የመንገድ ትራፊክ በማስተባበር፣ አረጋውያንን በመደገፍና በተለያዩ በጎ አድራጎት ሥራዎች እንደሚሳተፍ ያስረዳል፡፡

ከአያቱ ጋር ይኖር የነበረው የ30 ዓመቱ አቶ ደምሰው፣ በፀጉር ማስተካከል ሙያ የሚተዳደር ቢሆንም፣ ከልጁና ከባለቤቱ ጋር ኑሮን ለመግፋት እጅግ ተቸግሮ እንደነበር ያስረዳል፡፡

በፀጉር የማስተካከል ሙያ ከሚያገኘው ገንዘብ ከግማሽ በላይ ያህሉን ለቤት ኪራይ ስለሚያውለው የዕለት ተዕለት ኑሮውን ለማሻሻል ተቸግሮ እንደነበርም ያክላል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ የሚገኙ የመንግሥት ይዞታዎች፣ የቀበሌ ቤቶችና ኮንዶሚኒየም ዙሪያ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ጥናት ማስጠናቱ ይታወሳል፡፡ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሦስት ጥናት ሲደረግ ከተሳተፉት ወጣቶች የአንድ ልጅ አባት የሆነው አቶ ደምሰው ይገኝበታል፡፡

በየወረዳው ጥናት ሲደረግ ስለነበረው አሻጥር ብዙ መታዘቡን ይናገራል፡፡ ጥናት ሲያደርጉ በሕገወጥ ተይዘው ያገኙት 130 ቤቶች ናቸው፡፡ እነዚህ የቀበሌ ቤቶች በሕገወጥ መንገድ የሚኖርባቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ ሕገወጥ ግንባታዎች የሚከናወንባቸው እንደሆነም ይናገራል፡፡ የቀበሌ ቤት ውስጥ ተጨማሪ ቤት ሠርተው የሚያከራዩም በርካታ ናቸው፡፡

በወረዳው የተለቀቁ የቀበሌ ቤቶች ስምንት ብቻ መሆኑን፣ ሕገወጥ ተብለው በጥናቱ የተረጋገጡት 130 የቀበሌ ቤቶች መሆናቸውን የሚናገረው አቶ ደምሰው፣ የፍርድ ቤት ሒደት በተለይም እግዱ ቤቶቹ በቶሎ ለሚገባቸው እንዳይተላለፉ አድርጓል ብሏል፡፡  

በወረዳው በርካታ በሕገወጥ መንገድ የተያዙ ቤቶች መኖራቸውን መንግሥት ከወጣቶች ጋር በመሆን ሕገወጥ አሠራርን ማስቆም እንደሚገባ፣ ወጣቱ ማን ችግረኛ እንደሆነና ምን እንደሚሠራ ስለሚያውቅና ጥፋተኛን አሳልፎ እስከ መስጠት ስለሚደርስ በጋራ መሥራት ይገባል ብሏል፡፡

በጥናቱ መሠረት በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሦስት ብቻ ከ1,400 በላይ ሰዎች ቤት የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡ ሆኖም የኮንዶሚኒየም ዕጣ ደርሷቸው እያከራዩ በቀበሌ ቤት የሚኖሩ በርካታ መሆናቸው ችግሩ እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል፡፡

ኮንዶሚኒየም ደርሷቸው በቀበሌ ቤት ውስጥ የሚኖሩትን የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ቢያውቁም ስም ዝርዝራቸውን ይፋ ማድረግ ላይ ችግር መኖሩንም ገልጿል፡፡

በወረዳው ከ90 ያላነሱ አባወራዎች የኮንዶሚኒየም ዕድል ያገኙ ቢሆንም፣ ኮንዶሚኒየም ከደረሳቸው አባወራዎች ኃላፊነት ተሰምቷቸው ቁልፍ የሚያስረክቡ ጥቂቶች መሆናቸውን የቀበሌ ቤታቸውን ቁልፍ ያስረከቡት አሥር እንደማይሞሉም ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡   

‹‹ኮንዶሚኒየም የደረሳቸው ሰዎች ለምን አትወጡም ሲባሉ ‹ጊዜው ሲደርስ ያስወጡናል፣ ውጡ ሳይሉን ለምን እንወጣለን› ይላሉ፤›› ብሏል፡፡

በሥጋ ዝምድና የሌላቸው ሰዎች አረጋውያንን ልርዳ በሚል በቀበሌ ቤት ገብተው በኋላም ቅጽ ላይ ባለመኖራቸው ጎዳና ላይ የወደቁ እንዳሉ በማስታወስም፣ መንግሥት ሕገወጦች ላይ እየሠራ ቢገኝም ችግርን ለመፍታት ተብሎ ችግር እንዳይፈጠር በጥልቀት ማጣራት እንደሚገባ ተናግሯል፡፡

የአራዳ ክፍለ ከተማ ቤቶች ልማት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዲ ሙሉነህ፣ የከተማ አስተዳደሩ ሕገወጥነትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና በቀጣይ ሥርዓት ለማስያዝ በጥናትና በሕዝብ ጥቆማ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በጥቆማውና በጥናቱ መሠረት በመጀመርያው ዙር የተለቀቁ 139 የቀበሌ ቤቶች ዝቅተኛ ኑሮ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ተላልፈዋል ብለዋል፡፡

አቶ አብዲ፣ በክፍለ ከተማው በአጠቃላይ 19,996 ቤቶች መኖራቸውን፣ የከተማ ሜጋ ፕሮጀክቶች የሚያከናወኑበት በመሆኑም ከስምንት በላይ ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ ቤቶች በመልሶ ማልማት ምክንያት መፍረሳቸውን ጠቁመዋል፡፡

በክፍለ ከተማው ለልማት ብቻ ከ5,000 በላይ ቤቶች የፈረሱ ሲሆን፣ ካሉት ቤቶች ውስጥ በሕገወጥነት የተያዙ ቤቶች መኖራቸውን ተገልጿል፡፡

በጥቆማ ደረጃ ከተገኙት 340 ቤቶች ውስጥ 139 ቤቶች በኢኮኖሚ አቅማቸው ደከም ላሉ የኅበረተሰብ ክፍሎች እንዲደርስ ተደርጓል፡፡

የማኅበራዊ ቀውስ በማያስከትል መልኩ በሕገወጥ መልኩ የተያዙ የመንግሥት ቤቶችን የማስለቀቁ ሥራ እንደሚቀጥልም ኃላፊው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ከ139 ቤቶች ውስጥ 72ቱን ለሴቶች፣ 57 ለወንዶች የተሰጠ ሲሆን፣ ስብጥሩም አካል ጉዳተኛ፣ አረጋውያንና ወጣቶችን ያካተተ ነው፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ በሕገወጥ መንገድ የተወሰዱ የቀበሌ ቤቶችን በማስለቀቅ ለችግረኛ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቁልፍ ያስረከቡት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ናቸው፡፡

በክፍለ ከተማው ሕገወጥ የቤት ወረራን ለማስመለስ የተደረገውን ጥረት ያደነቁት ወ/ሮ አዳነች፣ ሌሎች ክፍለ ከተሞችም ከዚህ መማር አለባቸው ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ያለው ሕገወጥ የመሬት ወረራና መሰል ችግሮችን ለመፍታት ኅብረተሰቡ ከመንግሥት ጋር በመሆን መሥራት እንዳለበትና አራዳ ክፍለ ከተማን ጨምሮ በሌሎች የመዲናይቱ ቦታዎችም በሕገወጥ መንገድ የተያዙ የመንግሥት ይዞታዎችን የማስለቀቅና መሰል ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 10,565 የቀበሌ ቤቶች በቁልፍ ግዥ፣ ሰብሮ በመግባትና ሕጉ ከሚፈቅደው ውጪ በሕገወጥ መንገድ መያዙን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

የመሬት ወረራ፣ ሕገወጥ ግንባታ፣ የጋራ መኖሪያ ቤት የማስተላለፍ ሒደትና ተያያዥ ጉዳዮች እንዲሁም ከቀበሌ ቤት አስተዳደር ጋር የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማጥራት በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ አማካይነት ዝርዝር ጥናት በማካሄድ የጥናቱን ግኝት ለሕዝብ ይፋ ተደርጓል፡፡

ከክፍለ ከተማና ከወረዳ ቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤቶች በተገኘ መረጃ መሠረት አጠቃላይ በከተማ አስተዳደሩ ሥር 150,737 የቀበሌ መኖሪያና ንግድ ቤቶች ያሉ ሲሆን፣ በዚህ ጥናት ግን ተደራሽ መሆን የቻሉ 138,652 የመኖሪያና የንግድ ቤቶች ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ 10,565 የቀበሌ ቤቶች በቁልፍ ግዥ፣ ሰብሮ በመግባትና ሕጉ ከሚፈቅደው ውጪ በሕገወጥ መንገድ ተይዘዋል፡፡

በጥናቱ ተደራሽ ከተደረጉ የቀበሌ መኖሪያ ቤት ውስጥም 7,723 ቤቶች ውል በሌላቸው ሕገወጥ በሆኑ ሰዎች ተይዘዋል፡፡ 2,207 የቀበሌ ቤቶች፣ 2,207 ደግሞ ወደ ግል የዞሩ፣ 265 በሦስተኛ ወገን የተያዙና 164 ኮንዶሚኒየም በደረሳቸውና የራሳቸው ቤት ባላቸው ሰዎች የተያዙ የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች መኖራቸውም ታውቋል፡፡

137 ለመኖሪያነት የሚያገለግሉ የቀበሌ ቤቶች በሽያጭ ወደ ግል የተላለፉ፣ 1,243 ታሽገውና ተዘግተው የተቀመጡ፣ 5,043 የፈረሱና 180 አድራሻቸው የማታወቁና የጠፉ የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች እንዳሉ ተረጋግጧል፡፡

የቀበሌ ንግድ ቤቶችን በተመለከተም በአጠቃላይ የንግድ ቤቶች ብዛታቸው 25,096 ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ 4,076 በሕገወጥ መንገድ የተያዙ ናቸው፡፡

ውል የሌላቸው 1,070 ነጋዴዎች የቀበሌ የንግድ ቤቶች እየተጠቀሙባቸው መሆኑም ተለይቷል፡፡ 2,451 የቀበሌ የንግድ ቤቶች በ1,086 ነጋዴዎች እንደተያዙም ይህም አንድ ነጋዴ ከሁለት በላይ መያዙን ጥናቱ አመልክቷል፡፡

376 የቀበሌ ንግድ ቤቶች ደግሞ ለሦስተኛ ወገን የተላለፉ፣ እንዲሁም 179 የታሸጉ የንግድ ቤቶች እንዳሉም በጥናቱ ለመለየት መቻሉ ይታወቃል፡፡

የአራዳ ክፍለ ከተማ ሕገወጥ መሬት ወረራ የተከናወነበትና የቀበሌ ቤቶች ያላግባብ ከተያዙበት ውስጥ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...