መንግሥት በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻ ከጀመረበት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ምንም ዓይነት ገቢ ባለመሰብሰቡ ምክንያት፣ ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ አለማግኘቱን ገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሚኒስቴሩ የበላይ ኃላፊዎች የተቋሙን የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባለፈው ሳምንት አቅርበዋል።
ገቢዎች ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ ካቀደው 290 ቢሊዮን ብር ውስጥ በትግራይ ክልል ለማግኘት ታቅዶ የነበረው 7.8 ቢሊዮን ብር የነበረ ቢሆንም፣ በክልሉ በነበረው የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት ለሦስት ወራት ያህል ምንም ዓይነት ገቢ አለመሰብሰቡን ሚኒስትሩ አቶ ላቀ አያሌው ለሪፖርተር ተናግረዋል።
የሕግ ማስከበር ዘመቻው ከመጀመሩ በፊት በነበሩ ጥቂት ሦስት ወራት ወደ 1.8 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ መሰብሰቡን፣ በጥቅምት ወር መጨረሻ የሕግ ማስከበር ዘመቻው ከተጀመረ በኋላ ግን ምንም ዓይነት ገቢ እንዳልተሰበሰበ አቶ ላቀ አክለው ገልጸዋል።
ከሐምሌ እስከ ጥቅምት ወራት ከተሰበሰበው ገቢ የአገር ውስጥ ገቢ ከ563 ሚሊዮን በላይ ብር እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ በገቢዎች ሆነ በጉምሩክ ቅርንጫፍ ምንም ዓይነት ሥራ ባለመሠራቱ ከትግራይ ክልል ለማግኘት የታቀደውን፣ ለሌሎች የአገሪቱ ቅርጫፎች በማከፋፈል መገኘት የነበረበትን ገቢ ማሳካት እንደተቻለ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
እንደ ሚኒስተሩ ገለጻ በትግራይ ክልል መሰብሰብ የነበረበት ገቢ ባለመሰብሰቡ የታሰበውን አገራዊ ገቢ የሚያናጋ አይደለም፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፉት ስድስት ወራት 149 ቢሊዮን ብር የሰበሰበ መሆኑን፣ ከአጠቃላይ ገቢው ከ93 ቢሊዮን ብር በላይ ከአገር ውስጥ ገቢ፣ 56 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ደግሞ ከጉምሩክ ገቢ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው በትግራይ በተፈጠረው ሁኔታ ካልተሰበሰበው ሁለት ቢሊዮን ብር ገቢ ውስጥ፣ በመቀሌ ጉምሩክ ጣቢያ ከጉምሩክ ገቢ መገኘት የነበረበት 800 ሚሊዮን ብር እነደነበር ገልጸዋል፡፡
በመቀሌ ጉምሩክ ኮሚሽን ቢሮዎች መሰባበራቸውና ንብረት መዘረፉን የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ የደረሰውን ጉዳት ለማወቅ ጥናት እያደረገ እንደሆነና አንዳንድ ቢሮዎቹ ከቅርብ ቀናት በፊት ወደ አገልግሎት ተመልሰው የገቢ መሰባሰቡን ሥራ እንደ ጀመሩ ተናግረዋል።
ኮሚሽነሩ የሕገወጥ ንግድና የኮንትሮባንድ ንግድን አስመልክቶ ሲናገሩ፣ በስድስት ወራት ብቻ ከ19.2 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ንብረቶች በቁጥጥር ሥር እንደ ዋሉ ገልጸዋል።
ምንም እንኳ ቁጥጥሩ ቢጨምርም ባለፉት ስድስት ወራት ኮንትሮባንድና ሕገወጥ ንግድ አለመቀነሱን፣ አሁንም ሕገወጦች ሰንሰለታቸውንና ዘዴያቸውን በመቀያየር እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸዋል።
በዚህም የተቋሙ ሠራተኞች በሕገወጥ ነጋዴዎች ላይ በሚያደርጉት ቁጥጥርና ግብግብ፣ ጥይት ተተኩሶባቸው የቆሰሉ እንዳሉና አንድ ሠራተኛም እንደተገደለ ተናግረዋል።
ከቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ እንዲቆጣጠር የተቋቋመው የፀረ ኮንትሮባንድ ግብረ ኃይል ከአደረጃጀቱና ከስሙ ባለፈ ትርጉም ያለው ሥራ እያከናወነ እንዳልሆነ፣ በየጊዜው የሚታየውን ሕገወጥ ንግድ ለመቆጣጠር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አሠራሩን እንዲፈትሽ ሲሉ ጠይቀዋል።
አቶ ደበሌ በግማሽ ዓመቱ በሕገወጥ ሥራ እንደተሠማሩ ከተጠረጠሩና መያዝ ከነበረባቸው 810 ግለሰቦች፣ 680 ያህሉ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተናግረዋል።