የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከሚያስተዳድራቸው ቤቶች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ ጊዜያት ያለ ምንም ካሳ ላፈረሳቸው ከ980 በላይ ቤቶች በተደጋጋሚ ካሳ እንዲከፍል ቢጠየቅም፣ ሊከፍል ባለመቻሉ ፓርላማው መፍትሔ እንዲሰጠው ጥያቄ አቀረበ።
በከተማ አስተዳደሩ በቅርቡ የፈረሱትን ሳይጨምር ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ በፖሊስና በደንብ አስከባሪዎች በመታገዝ ያለ ምንም ቅድመ ጥንቃቄ ካፈረሳቸው 1,357 ቤቶች ውስጥ፣ ለ370 ቤቶች ብቻ ካሳ እንደተከፈለውና ለቀሪዎቹ ምንም ዓይነት ካሳ እንዳልተሰጠው የኮርፖሬሽኑ የበላይ ኃላፊዎች ተናግረዋል።
የቤቶቹን መፍረስ አስመልክቶ ከቀድሞው ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ጋር በመነጋገር ጥናት ተደርጎ ጥናቱ ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት የቀረበ ቢሆንም፣ ‹‹በካቢኔ እናይና እንወስናለን›› ተብሎ ችግሩ ሳይፈታ አዲስ ምክትል ከንቲባ እንደተሾሙ የኮርፖሬሽኑ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ይርጋም ኩምሊት ተናግረዋል።
አቶ ታከለ ጉዳዩን ሳይፈቱት በመሄዳቸው ኮርፖሬሽኑ ጥያቄውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በማቅረብ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለፈረሱት ቤቶች የካሳ ክፍያ ጥያቄ በአስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም እሱም እንዳልተሳካ ገልጸዋል፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተሰጠ ትዕዛዝ መሠረት የከንቲባ ጽሕፈት ቤትና የቤቶች ኮርፖሬሽን ኃላፊዎች ያሉበት ኮሚቴ ተቋቁሞ ለምክትል ከንቲባ ለወ/ሮ አዳነች አቤቤ ቢቀርብም፣ ጥናቱ በቀድሞው አመራር የተሠራ በመሆኑ እንደ ገና ጥናት ይደረግበት ማለታቸውን አቶ ይርጋለም ገልጸዋል።
የኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች የቀድሞ አመራር የተባለው የከተማ አስተዳደሩ የራሱ አመራር የነበረና የተፈረመበት እንደሆነ ለማስረዳት ቢሞክርም፣ እንደ ገና ተጠንቶ ይምጣ በሚል ለሁለተኛ ጊዜ ስለቤቶቹ መፍረስ ጥናት እንዲደረግ መወሰኑን አክለው ተናግረዋል።
በዚህም የተነሳ ስለቤቶቹ መፍረስ በድጋሚ እንዲጠና የከንቲባ ጽሕፈት ቤት አካላት ባሉበት ሌላ ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ ቤቶቹ ያለ ካሳ መፍረሳቸው ለሁለተኛ ጊዜ እንደተረጋገጠ ገልጸዋል።
ኮርፖሬሽኑ ሁለተኛውን ጥናት ለምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች በአስቸኳይ ያቀረበ ቢሆንም፣ አሁንም ምላሽ እየጠበቀ እንደሆነና ፓርላማው እጁን እንዲያስገባ ጠይቀዋል።
ችግሩ ለፈረሱት ቤቶች ካሳ አለመከፈሉ ብቻ ሳይሆን ቤቶቹን እንዳሉ በመቁጠር (ባለመሰረዛቸው) እንደ ተሰብሳቢ ሒሳብ ተወስዶ ሳይሰበሰብ የቀረ በማለት በየዓመቱ የኦዲት አስተያየት በውጭ ኦዲተር በመቅረቡ፣ በፋይናንስ አስተዳደሩ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረባቸው መሆኑን ምክትል ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
ኮርፖሬሽኑ ጥያቄውን ያቀረበው የ2013 ዓ.ም. በጀት ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን ጥር 26 ቀን 2013 ዓ.ም. ለከተማ ልማት፣ ትራንስፖርትና ኮንስትራክሽን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ነበር።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል እንደሚሉት ካሳ ተከፍሎባቸዋል የተባሉት ቤቶች እንኳ ዋጋቸው ከ40 እስከ 50 ሚሊዮን የሚያወጡ ቢሆን፣ የገባው ገንዘብ ከ200 ሺሕና ከ300 ሺሕ ብር እንደማይበልጥ ነው።
‹‹በኮሚቴ አጣርተን ላቀረብነው ጉዳይም ምን አገባችሁ ተብለናል፤›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ‹‹ከመስቀል ፍላወር እስከ ፒያሳ ፕሮጀክት ያለ ካሳ 17 ቤቶችን እናፈርሳለን፣ አታፈርሱም በሚል ክርክር ለመጀመርያ ጊዜ በመንግሥት የተከሰሰ ተቋም ነው ሲሉ ገልጸዋል፤›› አቶ ረሻድ።
‹‹አንዳንድ ጊዜ የማይደፈር እየደፈርንና እየተጋፈጥን በመሆኑ፣ ምክር ቤቱ ሊያግዘን ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ የከተማ አስተዳደሩ 96 ቤቶችን ያለ ምንም ውል እየተጠቀመ ነው ሲሉ ጠይቀዋል።
ኮርፖሬሽኑ በተለያዩ ጊዜያት የመንግሥት ኃላፊዎች ከኃላፊነት ሲነሱና ሲቀያየሩ ከተሰጣቸው ቤቶች ያለ መውጣት ችግርን ለመቅረፍና የቤቶች ፍላጎት ለማጣጣም በሥራ ላይ ላሉ ለሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ ኮሚሽነሮችና ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ብቻ የሚሰጡ ቤቶችን በገርጂ አካባቢ እየገነባ እንደሆነ ገልጸዋል።
ኮርፖሬሽኑ ከሁለት ዓመት በፊት ባደረገው የንግድ ቤቶች የኪራይ ዋጋ ማሻሻያ ምክንያት፣ ‹‹አንዳንድ አካላት ለሚዲያ ገንዘብ እየሰጡ እየደለሉ እንቅልፍ እየነሱን ነው፤›› ሲሉ ወቀሳቸውን ሰንዝረዋል።
‹‹ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እየሆነ ባለው ማስተካከያ በመጀመርያው ዓመት የማስተካከያውን 35 በመቶ፣ በ2012 ዓ.ም. 35 በመቶና በተያዘው 2013 ዓ.ም. ቀሪውን 30 በመቶ ማስተካከያ እንዲከፍሉ መወሰኑ የሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ በዚህ ዓመት ማለቅና መስተካከል ያለበትን 30 በመቶ የኪራይ ዋጋ ማስተካከያ ለማስቀረት ሰላማዊ ሠልፍ እየተወጣብን ነው፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ በድሬዳዋ ከተማ ሩሲያ ካምፕ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፣ የመንግሥት አመራሮችና ቤተሰቦቻቸው የሚኖሩባቸው 155 ቤቶች ላይ በተደረገው የዋጋ ማስተካከያ፣ ከንቲባው ጭምር ሰላማዊ ሠልፍ ለመውጣት እየዳዳቸው ነው ሲሉ አቶ ረሻድ አስታውቀዋል።