Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየመራጮች ድምፅ የማዳመር ሒደትን የማገድና ውጤት የመሰረዝ ሥልጣን ለፍርድ ቤቶች የሚሰጥ ደንብ...

የመራጮች ድምፅ የማዳመር ሒደትን የማገድና ውጤት የመሰረዝ ሥልጣን ለፍርድ ቤቶች የሚሰጥ ደንብ ለፓርላማ ቀረበ

ቀን:

በምርጫ ወቅት የሚቀርብ አቤቱታን በመመርመር አፋጣኝ ውሳኔ የመስጠት ኃላፊነትን ጨምሮ፣ የመራጮች ድምፅ የማዳመር ሒደትን የማገድና ውጤት የመሰረዝ ሥልጣን፣ ለፌዴራልና ለክልል ፍርድ ቤቶች የሚሰጥ ረቂቅ ደንብ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።

በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተረቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ይህ ረቂቅ ደንብ፣ ‹‹የምርጫ ጉዳዮች በፍርድ ቤት የሚስተናገዱበት የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ደንብ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆንረቂቅ ደንቡም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅንና የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የሥነ ምግባር አዋጅን መሠረት አድርጎ የቀረበ ነው። 

የፍርድ ቤቶች ሥልጣን የሚወሰነው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚወጣ አዋጅ ቢሆንምየኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ደንብ የማውጣት ሥልጣን ለምክር ቤቱ የሚሰጥ በመሆኑ፣ ይኸው ረቂቅ ደንብ በተጠናቀቀው ሳምንት ውስጥ ለምክር ቤቱ ቀርቧል። 

ረቂቅ ደንቡ በምርጫ ወቅት የሚነሳ አቤቱታ ለምርጫ አስፈጻሚው አካል ቀርቦ በተሰጠ ውሳኔ ላይ ቅር የተሰኘ አካል፣ አቤቱታውን ለፍርድ ቤት አቅርቦ አፋጣኝ ፍርድ የሚሰጥበትንና የክርክር ሒደት የሚመራበትን ሥነ ሥርዓት የሚደነግግ ነው። 

በዚህም መሠረት ድምፅ ለመስጠት የተከለከለ ማንኛውም ሰው፣ እንዲሁም በሌላ ሰው ላይ ድምፅ መስጠት የለበትም የሚል ተቃውሞ ያለው ማንኛውም ሰው ወይም የፖለቲካ ፓርቲ አቤቱታውን ለምርጫ ክልሉ ቅሬታ ሰሚ አመልክቶ በተሰጠው ውሳኔ ያልተስማማ እንደሆነ፣ አቤቱታውን ለፍርድ ቤት ማቅረብና ፈጣን ውሳኔ ማግኘት እንደሚችል የረቂቅ ደንቡ ድንጋጌ ያመለክታል። 

በዚህ ሁኔታ አቤቱታ የቀረበለት ፍርድ ቤት ለአቤቱታው መነሻ ምክንያት መኖሩን ከተገነዘበ አቤቱታው በቀረበለት ቀን መርምሮ ውሳኔ የመስጠትወይም ፍርድ ቤቱ ጉዳዩ መጣራት አለበት ብሎ ያመነ እንደሆነ ተጠርጣሪው ወይም ጉዳዩ የሚመለከተው ሰው 24 ሰዓት እንዲቀርብ ትዕዛዝ መስጠትና አቤቱታው ከቀረበለት ሰዓት ጀምሮ በሦስት ቀናት ውስጥ ውሳኔ ማሳለፍ እንደሚኖርበት ይደነግጋል። 

ፍርድ ቤቱ አቤቱታው በቀረበበት ወቅት በሕግ አግባብ አስፈላጊነቱ ላይ ካመነ አቤቱታው በቀረበበት የምርጫ ጣቢያ የምርጮች ድምፅ የማዳመር ሒደት እንዳይጀመር፣ ወይም ተጀምሮ ከሆነ እንዲቆም የማገድ ሥልጣን እንደሚኖረው የረቂቅ ደንቡ ድንጋጌ ያመለክታል። 

በተመሳሳይ ማንኛውም በድምፅ ቆጠራ ሒደትና ውጤት ላይ ቅሬታ ያለው የፖለቲካ ፓርቲ ወይም የግል ዕጩ አልያም ወኪል፣ ያላቸውን ቅሬታ ምርጫውን ለሚያስፈጽመው የምርጫ ቦርድ በማቅረብ ቅሬታው ተቀባይነት ያላገኘ ከሆነ አቤቱታውን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለማቅረብ እንደሚችል በረቂቁ ተደንግጓል። 

አቤቱታ የቀረበለት ፍርድ ቤት ቅሬታውን በሚመረምርበት ወቅት አስፈላጊ ነው ብሎ ካመነ፣ በምርጫ ሕጉ መሠረት ቅሬታ የቀረበበት ምርጫ ክልል ውጤት እንዳይገለጽ የማገድና ጉዳዩን መርምሮ ምርጫ ቦርድ የሰጠውን ውሳኔ የሚያሻሻል ወይም የሚሰረዝ ውሳኔ ማሳለፍ እንደሚችል በረቂቁ ተደንግጓል።

ፍርድ ቤቱ የቦርዱን ውሳን የሚሽር ወይም የሚያሻሽል ውሳኔ ካሳለፈ እንደ አግባብነቱ ቅሬታ የቀረበበትን የምርጫ ጣቢያ ወይም የምርጫ ክልል ውጤት በሙሉ ወይም በከፊል መሰረዝዳግም ቆጠራ እንዲካሄድ ወይም ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ ማዘዝ ይችላል።

ድምፅ አሰጣጥን በተመለከተ ሊቀርቡ ከሚችሉ አቤቱታዎች መካከልም ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ዜጋ፣ በምዝገባ ወቅት 18 ዓመት በታች የሆነ መራጭ፣ በምርጫ ክልሉ የኖረው ከስድስት ወራት በታች የሆነው፣ የያዘው ምርጫ ካርድ ሐሰተኛ ወይም የሌላ ሰው የሆነ፣ በመራጭነት ያልተመዘገበ ሰው ድምፅ መስጠቱን የሚገልጽ አቤቱታዎች ሊሆኑ እንደሚችል ተመልክቷል። 

የድምፅ ቆጠራ ሒደትና ውጤትን በተመለከተ ከሚቀርቡ አቤቱታዎች መከላከልየተበላሹና ዋጋ አልባ የሆኑ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ተቆጥረዋልና በአግባቡ የተሰጠ ድምፅ ዋጋ አልባ እንዲሆን ተደርጓል የሚል አቤቱታ፣ የምርጫ ውጤቱ ለሕዝብ ሳይገለጽ ያላግባብ ዘግይቷል የሚል ቅሬታ፣ የድምፅ ቆጠራው በሕግ ከተፈቀደው ቦታ ውጪ ተቆጥሯል የሚል አቤቱታ፣ የድምፅ መስጫ ሳጥን ተቀዷል፣ ተሰብሯል ወይም ብልሽት ደርሶበታል፣ እንዲሁም ቆጠራው በቂ የተፈጥሮ ወይም ሰው ሠራሽ ብርሃን በሌለበት ሁኔታ ተከናውኗል የሚሉ ቅሬታዎች የተወሰኑት ናቸው።

ፍርድ ቤቶች ቅዳሜና እሑድን እንዲሁም የበዓል ቀናትን ጨምሮ አገልግሎት የመስጠት ኃላፊነት የሚጣልባቸው ሲሆንየሚሰጡት ውሳኔ የመጨረሻ እንደሚሆንም ረቂቅ ደንቡ ያመለክታል። 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...