የመንግሥት ተቋማት የተበደሩት 53 በመቶ ነው
ሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮችና 16ቱ የግል ባንኮች የሰጡት ከተበዳሪዎች የሚፈለግ የብድር መጠን፣ በሃያ በመቶ በመጨመር ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ መድረሱ ተገጸ፡፡
ሰሞኑን ይፋ የተደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የ2012 ዓ.ም. ዓመታዊ ሪፖርት እንዳመለከተው፣ ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ የደረሰው የብድር መጠን እስከ ሰኔ 2012 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ የተመዘገበ ነው፡፡
በሪፖርቱ እንደተጠቀሰው በ2012 የሒሳብ ዓመት ተሰብሳቢ ሆኖ ከተመዘገበው ብድር ውስጥ 53 በመቶ፣ ወይም ከ530 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነው ለመንግሥት ተቋማት የተሰጠ ነው፡፡
ከግሉ ዘርፍ የሚጠበቁት ተሰ ብሳቢ ብድሮች መጠን ደግሞ 484.4 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ባንኮች ከሰጡት ጠቅላላ ብድር ውስጥ 47 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይይዛል፡፡
በግሉ ዘርፍ ያልተሰበሰበው የብድር መጠን የ28.3 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት የታየበት መሆኑን የሚያመለክተው የብሔራዊ ባንክ ዓመታዊ ሪፖርት፣ ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ከሆነው ብድር ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው የማዕድን፣ የኃይልና የውኃ ዘርፍ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡ ከጠቅላላው ብድር ውስጥ ሦስቱ ዘርፎች 29.5 በመቶ ድርሻ አላቸው ተብሏል፡፡
ከእነዚህ ቀጥሎ ከፍተኛ ብድር ያለበት ዘርፍ ኢንዱስትሪው ሲሆን፣ ከጠቅላላ ተሰብሳቢ ብድር ውስጥ 21.5 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይዟል፡፡ የዓለም አቀፍ ንግድ 13 በመቶ፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን 13 በመቶ፣ የአገር ውስጥ ንግድ 8.5 በመቶ፣ ትራንስፖርትና መገናኛ 6.7 በመቶ፣ ሌሎች ደግሞ 9.6 ድርሻ እንዳላቸው የብሔራዊ ባንክ ዓመታዊ ሪፖርት ያመለክታል፡፡