- ዕቅዱ የወደፊት የውጭ ብድር ግኝትን እንዳያስተጓጉል ሥጋት ጭሯል
የቡድን 20 አገሮች የውጭ ዕዳ ክምችት ለተጫናቸው ታዳጊ አገሮች ማቅለያ ካመቻቹት ዕድል በተጨማሪ፣ ከውጭ የግል አበዳሪዎች ተመሳሳይ የዕዳ ጫና ማቅለያ ኢትዮጵያ ልትጠይቅ እንደምትችል መንግሥት አስታወቀ።
የገንዘብ ሚኒስቴር ባለፈው ሰኞ ጥር 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው በዓለም አቀፉ የገንብ ተቋም አይኤምኤፍ አማካይነት የቡድን 20 አገሮች እ.ኤ.አ. በ2020 አጋማሽ ላይ በከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ ለሚገኙ ታዳጊ አገሮች ካመቻቹት የዕዳ ማቅለያ በተጨማሪ የውጭ የግል አባደሪዎች ተመሳሳይ የዕዳ ጫና ማቅለያ እንደሚጠይቅ አስታውቋል።
መንግሥት ይህንን የሚያደርገው የኢትዮጵያን የውጭ ዕዳ ጫና ለመቀነስ እንደሆነ የገለጸው መግለጫው፣ ከዚህ በተጨማሪ የአገሪቱን የውጭ ዕዳ ጫና ለመቀነስ በዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ድጋፍ የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ እንደሆነ አመልክቷል።
የግል የውጭ አበዳሪዎች ለኢትዮጵያ የሰጡት ብድር የመክፈያ ጊዜ እንዲራዘም ወይም የመክፈያ ጊዜ እፎይታ እንዲሰጡ የሚጠይቀው የኢትዮጵያን የወደፊት የውጭ ብድር የማግኘት ዕድል በሚያስጠብቅ መንገድ እንደሚሆንም ገልጿል።
የቡድን 20 አገሮች ባመቻቹት የዕዳ ጫና ማቅለያ ተጠቃሚነት መስፈርትን ካሟሉ ከፍተኛ የውጭ ዕዳ ጫና ያለባቸው 74 አገሮች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን፣ በተሰጠው ዕድል እስከተጠናቀቀው 2020 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ መክፈል የነበረባት 472 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ዕዳ የክፍያ ጊዜ ለዓንድ ዓመት ያህል ተራዝሞላታል።
ኢትዮጵያ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ያገኘችው የዕዳ መክፈያ ጊዜ እፎይታ ከአበዳሪ አገሮችና የጋራ የሆኑ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የተገኘ ብድር የመክፈያ ጊዜን ብቻ የሚመለከት እንደሆነ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም መረጃ ያመለክታል።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋምና የቡድን 20 አገሮች ካመቻቹት የዕዳ ጫና ማቅለያ መስፈርት ጋር ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ የሆነ ቀመር የውጭ የግል አበዳሪዎች ቀርፀው የዕዳ ማቅለያ እንዲያመቻቹ ከሁለት ወራት በፊት ምክረ ሐሳብ ያቀረቡ ሲሆን፣ በዚህ መሠረት በተመቻቸ ዕድል የቻድ መንግሥት የመጀመርያ ተጠቃሚ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት በአሁኑ ወቅት 29 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕዳ ያለበት ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ለአውሮፓ የቦንድ ገበያ በተሸጠ ዩሮ ቦንዶ የተገኘው አንድ ቢሊዮን ዶላር በውጭ የግል አበዳሪዎች ዘርፍ ውስጥ የሚገኝ ዕዳ ነው።
የዚህ የብድር መክፈያ ጊዜ እ.ኤ.አ. በ2024 የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በገባችው ስምምነት መሠረት አንድ ቢሊዮን ዶላሩን ከነወለዱ በአንድ ጊዜ ውስጥ መመለስ ይጠበቅበታል።
ከዚህ በተጨማሪም ለአዋሽ ወልዲያ ሐራ ገበያ የባቡር መስመር ግንባታ ተመሳሳይ መጠን ያለው ብድር ከውጭ የግል አበዳሪዎች አግኝታለች።
ከእነዚህ የውጭ የግል አበዳሪዎች የተገኘ ብደርን የመክፈያ ጊዜ እንዲራዘም ማድረግ፣ አገሪቱ አሁን ካለባት ከፍተኛ የውጭ ዕዳ ሸክም አንፃር አስፈላጊ መስሎ ቢታይም፣ ይህንን ማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕዳዋን መክፈል የማትችል አገር አድርጎ ሊያሰይም እንደሚችልና ይህም የወደፊት የውጭ ብድር ፍላጎት ላይ በር የሚዘጋ በመሆኑ፣ መንግሥት ጥንቃቄ እንዲያደርግ ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ይህንን አዝማሚያ በማየትም ሙዲስ የተባለው ዓለም አቀፍ የውጭ ዕዳ ገምጋሚ ቡድን ከጥቂት ወራት በፊት ባወጣው ሪፖርት፣ ኢትዮጵያን ዕዳ በመክፈል ረገድ ጥንቃቄ ሊደረግባት የምትገባ አስጊ አገር ብሎ እንደፈጃት ማሳያ በማቅረብ ሥጋታቸውን ገልጸዋል።