ግብፅ በኤርትራ የባህር ግዛት ላይ ፈቃድ ሳይኖራቸው በመገኘታቸው የተያዙት ግብፃውያን ዓሳ አጥማጆች እንደሆኑ በመጥቀስ ዜጎቿ እንዲለቀቁ የኤርትራን መንግሥት ጠየቀች።
በአምስት ጀልባዎች በመሆን በኤርትራ የባህር ክልል ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የተገኙትን ግብፃዊያን የኤርትራ የባህር ኃይል በቁጥጥር ሥር ያዋለው ባለፈው ወር መሆኑን መረጃዎች የሚያመለክቱ ሲሆን፣ ‹‹ዓሳ አጥማጆች ናቸው›› የተባሉትን ግብፃዊያን ለማስለቀቅም የግብፅ መንግሥት ኦፊሳላዊ ጥያቄ ለኤርትራ መንግሥት ማቅረቡ ተሰምቷል።
የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሹክሪ ከኤርትራው አቻቸው ኦስማን ሳላህ ጋር በተጠናቀቀው ሳምንት ሐሙስ ዕለት ባደረጉት የስልክ ውይይት፣ ግብፃዊያኑ ዓሳ በማጥመድ የሚተዳደሩ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ የኤርትራ መንግሥት በፍጥነት እንዲለቃቸው መጠየቃቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በኤርትራና በግብፅ መንግሥት መካከል የጋራ ዓሳ የማጥመድ ስምምነት ቢኖራቸውም፣ ባለፈው ወር የተያዙት ግብፃዊያን ግን ሙሉ በሙሉ የዓሳ ማጥመድ ተልዕኮ ላይ እንዳልነበሩ የጠረጠረችው ኤርትራ፣ ግብፃዊያኑን በቁጥጥር ሥር ማዋሏን ሪፖርተር ከዲፖሎማቲክ ምንጮቹ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ግብፃዊያኑ ያልተገባ እንቅስቃሴ ላይ ምንአልባትም የስለላ ተልዕኮ የተሰጣቸው እንደሆኑ በኤርትራ በኩል በቂ ጥርጣሬ በመኖሩ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉንና እስካሁንም በምርመራ ላይ እንደሚገኙ ዲፕሎማቲክ ምንጮቹ ገልጸዋል።
ምንጮቹ እንደሚሉት ዓሳ አጥማጅ የተባሉት ግብፃዊያን በኤርትራ ግዛት የተገኙት ፈቃድ ሳይኖራቸው ከመሆኑ ባለፈ፣ የኤርትራ መንግሥት በአስመራ የተመደቡትን የግብፅ አምባሳደር ከአገር እንዲወጡ ባደረገች በሳምንታት ውስጥ የተከሰተ በመሆኑ፣ የኤርትራ መንግሥት ጥርጣሬ እንዲያይል ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል።
የግብፅ ሚዲያ አውታሮች በኤርትራ መንግሥት ቁጥጥር ሥር የዋሉትን ግብፃዊያን ለማስለቀቅ፣ የአገሪቱ መንግሥት ጥረት እያደረገ መሆኑን ቢገልጹም፣ በኤርትራ በኩል ስለተሰጠው ምላሽ ያሉት ነገር የለም።
ከኤርትራ በተጨማሪ በሳዑዲ ዓረቢያ የባህር ድንበር ውስጥ ያለፈቃድ ተገኝተዋል የተባሉ ግብፃዊያን ዓሳ አጥማጆች፣ ባለፈው ወር ላይ በሳዑዲ መንግሥት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና እስካሁንም አለመለቀቃቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።