ጊዜው ራቅ ቢልም ድርጊቱ ግን አሁንም አይረሳኝም፡፡ ዕለቱ ረቡዕ ሲሆን ሥፍራው ደግሞ አራት ኪሎ ነው፡፡ ከቱሪስት ሆቴል ፊት ለፊት ያለ ካፌ ውስጥ፡፡ ከዓመታት በፊት ዲቪ ደርሶት አሜሪካ ከሄደ ጓደኛዬ ጋር ጋዜጣና መጽሔቶችን እያጋላበጥን ከቡና ጋር ወግ ይዘናል፡፡ ከእኛ ቀጥሎ ያለውን ጠረጴዛ የከበቡ ሦስት ሰዎች በዝምታ ሻያቸውን ፉት እያሉ ናቸው፡፡ እኛ የባጥ የቆጡን እየቀባጠርን ሳለ አንድ ረጅም ቀላ ያለ ሪዛም ሰው ሦስቱን ሰዎች ሰላምታ ሰጥቶ ተቀላቀላቸው፡፡ የሰውየውን መምጣት በጉጉት እየተጠባበቁ መሆኑን የተረዳነው፣ ገና ከመቀመጡ በጥያቄ ሲያዋክቡት ነው፡፡ ሰውየው በሚኮላተፍ አማርኛ በሐዘን ስሜት፣ ‹‹ጉድ ሠራን ላገኘው አልቻልኩም…›› ሲላቸው አንደኛው ጎረምሳ መሰል በንዴት፣ ‹‹የገባበት ገብተን እንገድለዋለን እንጂ ገንዘባችንን በልቶ አይቀራትም…›› እያለ በተሰባበረ አማርኛ ሲደነፋ የካፌዋን ተጠቃሚዎች ትኩረት አገኘ፡፡
እኔና ጓደኛዬም ሆንን ሌሎች ሰዎች ምን እንደተፈጠረ ሳናውቅ የሰዎችን ንግግር መከታተል ስንጀምር፣ በጥድፊያ ሒሳባቸውን ከፍለው መልስ ሳይቀበሉ አራቱም ተከታትለው ወጡ፡፡ ሰዎቹን ምን እንደገጠማቸው ባናውቅም ከበድ ያለ ችግር ለመኖሩ አስረጂ አያስፈልግም ነበር፡፡ ነገር ግን የገጠማቸው ችግር ምን ይሆን የሚለው ነበር ያልገባን፡፡ ሰዎቹ ተንጋግተው ወጥተው ከሄዱ በኋላ ግን ጥግ ላይ ከካሸሯ አጠገብ ያለ ወንበር ላይ የተቀመጠ ቀጭን ወጣት ከት ብሎ ሳቀ፡፡ አሳሳቁ ድንገተኛ ስለነበር ሁላችንም ማለት ይቻላል ምን ሊል ይሆን ብለን ትኩረታችንን ወደ እሱ አደረግን፡፡ ወጣቱ ሳቁ ጋብ ሲልለት አንገቱን እየነቀነቀ፣ ‹‹ሌባን ሌባ ቢሰርቀው ምንኛ ይደንቀው ነው የተባለው አይደል…›› እያለ እንደገና ሲስቅ የሰዎቹን ሚስጥር እንደሚያውቅ ተረዳን፡፡
ይኼኔ ካሸሯ ፈራ ተባ እያለች፣ ‹‹አንተ ልጅ ተው ብዬሃለሁ፣ እነዚህ ሰዎች ቀላል እንዳይመስሉህ፡፡ ጭንቅላትህን በጥይት በታትነው አስፋልት ላይ ነው የሚያሰጡህ…›› በማለት ሥጋቷን ስትነግረው፣ ‹‹ዝም በይ እባክሽ፣ እነሱ ከአገር ላይ የዘረፉትን ገንዘብ ጮሌዎች ሴብል ባንከረባብት አድርገው እንደ በሉዋቸው ድፍን አራት ኪሎ የሚያውቀው ነው…›› አላት፡፡ አሁንማ ካፌው ውስጥ ያለነው በሙሉ ይህንን ጉድ ለመስማትና የጨዋታው ተሳታፊ ለመሆን አሰፈሰፍን፡፡ ‹‹ለመሆኑ የተፈጠረው ነገር ምንድነው?›› ብሎ አንዱ የተሳትፎ መድረኩን አመቻቸው፡፡ ‹‹ምን መሰለህ ሰዎቹ ሜርኩሪ ለመግዛት ሻጭ ነው ከተባለ ሰው ጋር ይቃጠራሉ፡፡ አገናኙ ደግሞ ባለሀብት ነው የተባለ መርሰዲስ የሚይዝ ዘናጭ ነው፡፡ ከሻጭ ጋር ከመገናኘታቸው በፊት ቀብድ 300 ሺሕ ብር ክፈሉ ተብለው ክፍያ ከፈጸሙ በኋላ አራዳው ተሸበለለ…›› ብሎ እንደገና ሲስቅ ነገሩ ገባን፡፡
ደርግ ወድቆ ኢሕአዴግ አገር በተቆጣጠረበት ጊዜ የሜርኩሪ ቢዝነስ ወሬ ደርቶ ብዙዎች ጉድ መሠራታቸው አይዘነጋም፡፡ ኢሕአዴግ የፈረሰውን የቀድሞ ጦርና ከየመሥሪያ ቤቱ የተሰናበተውን በርካታ ሠራተኛ በመሥጋት፣ በደኅንነት ክፍሉ አማካይነት የፈጠራ ወሬ በመንዛት ብዙዎች ቀልባቸውን ስተው ሜርኩሪ ሲያሳድዱ እንዲውሉ አድርጎ ነበር፡፡ በደርግ ዘመን ከውጭ የገባ ከፍተኛ መጠን ያለው ሜርኩሪ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለ፣ ዓረቦች እሱን ፍለጋ በሻንጣ ዶላር አጭቀው መምጣታቸው በሰፊው ስለተናፈሰ ከበረከቱ ለመቋደስ ሲሉ በርካቶች የጫማቸውን ሶል ከመጨረስ አልፈው፣ ንብረታቸውን እየሸጡ የአጭበርባሪዎች ሲሳይ ሆነው ነበር፡፡ ያ ቀጭን ወጣት 300 ሺሕ ብር የተበሉት እነዚያ ሰዎች የኢሕአዴግ አባላት ናቸው ሲለን በጣም ተገረምን፡፡
ልብ በሉ ይህ ድርጊት የተፈጸመው በ1985 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ነው፡፡ የዚያን ጊዜ 300 ሺሕ ብር ማለት አንድ ዶላር በሕጋዊ መንገድ በሦስት ብር ሲመነዘር ነው፡፡ በዛሬው የምንዛሪ ተመን ብንመታው በርካታ ሚሊዮን ብሮች ይሆናል፡፡ እኔና ጓደኛዬ ሰንጋ ተራ ካለው ኮሜርስ ኮሌጅ ተመርቀን ንግድ ባንክ ስንሠራ ደመወዛችን ከ400 ብር አይበልጥም ነበር፡፡ ከበረሃ ብጭቅጫቂ ቁምጣ ለብሰው አዲስ አበባ ሲገቡ ያየናቸው ኢሕአዴጎች ወይም የሕወሓት ሰዎች፣ በምን ተዓምር ነው ያን ጊዜ ያን ያህል ገንዘብ ለሜርኩሪ መግዣ ሊያገኙ የቻሉት? እኔና ጓደኛዬ በዚህ እየተብሰለሰልን እያለን ቀጭኑ ወጣት፣ ‹‹ሌሎች አራዶችም እኮ የእነዚህን ጓደኞች አራተኛ ክፍለ ጦር አካባቢ በጣም ብዙ ገንዘብ ሸውደዋቸዋል…›› እያለ ሲስቅ፣ ‹‹አንተ ልጅ ተው ብየሃለሁ…›› የምትለው ካሸሯ ነበረች፡፡
ዓመት ሌላ ዓመት እየተካ ሲሄድ ሁላችንም በፈለግነው ሳይሆን በኑሮ ግዴታ ከአንዱ ወደ ሌላው ሳያልፍልን ስንዘል፣ የሕወሓት/ኢሕአዴግ ሰዎች ግን ተዓምር ሊባል በሚችል መምዘግዘግ የሀብት ማማ ላይ መንጠላጠላቸውን ቀጠሉ፡፡ ከእናት አገር በዘረፉት ሀብት መርካቶ በመባል የሚታወቀውን ገበያ ከመቆጣጠር አልፈው፣ እያንዳንዱ ንግድ ውስጥ ሰተት ብለው ገቡ፡፡ በኮንድሮባንድ ከሚያስገቡዋቸው ሸቀጣ ሸቀጦችና የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች በተጨማሪ፣ ከቀረጥ ነፃ ዕድልን በገፍ በመጠቀም የተዋጣላቸው ብረት ነጋዴዎች ሆኑ፡፡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ግዥዎች በሙሉ በመቆጣጠር በጀቱን ጠቅልለው ኪሳቸው ከተቱት፡፡ ይህ አልበቃ ብሏቸው በሕዝብ ላብ የሚገነባውን የህዳሴ ግድብ ገንዘብ በምንጣሮና በማሽን ኪራይ ሰበብ ዘረፉት፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች መሬት እየወረሩ በመሸጥ በሕንፃ ላይ ሕንፃ ገነቡ፡፡ አገሪቱን አጥንቷን ጭምር ጋጡት፡፡
ይህ ሁሉ መከራ ታልፎ በሕዝብ እንቢታ ተገደው ከአራት ኪሎ ሲባረሩ አገሪቱን አራቁተው የነበረ ቢሆንም፣ በቃ ከላያችን ላይ ከተነሳችሁ በቂ ስለሆነ አርፋችሁ ተቀመጡ ቢባሉ አልሰማ አሉ፡፡ ትግራይ ገብተው ሌሎች ክልሎች ውስጥ ግጭት እያስነሱ ሕዝብ ማስፈጀትና ማፈናቀል ሥራቸው ሆነ፡፡ ጥጋባቸውና ዕብሪታቸው ከመጠን በላይ ስለነበር፣ ባደራጁት ኃይል አማካይነት የአገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝን አጥቅተው የሠራዊታችንን አባላት በግፍ ገደሉ፣ የታጠቀውን መሣሪያ ገፈፉ፡፡ አራት ኪሎ ተመልሰው ለመምጣት ተነሱ፡፡ ይህን ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትዕግሥቱ አልቆ ነበርና በአንድ ላይ ተነስቶ ለሠራዊታችን ደጀን ሆነ፡፡ ሠራዊቱን የወጉ ጊዜ ላያቸው ላይ ቤንዚን አርከፍክፈው እሳት እንደለኮሱ ያልገባቸው ሕወሓቶች፣ በሠፈሩት ቁና ተሠፈሩ፡፡ ዳግም እንዳይመለሱ ተደርገው ተደቆሱ፡፡ የእነሱ መዘዝ ግን ለትግራይ ሕዝብ ተረፈ፡፡
የሕወሓት ግልገሎች በየቦታው ሲያላዝኑ ይገርመኛል፡፡ ዋናውን ርዕሰ ጉዳይ ሆን ብለው እየዘለሉ በትግራይ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ሰቆቃ ሌላ ባለቤት ይፈልጉለታል፡፡ ሕወሓት ጥጋቡና ዕብሪቱ ልቡ ላይ ፈልቶ ቢመከርና ቢዘከር አልሰማ ብሎ እሳት ውስጥ ሲገባ፣ ይህ ሁሉ መከራና ሥቃይ ሊመጣ እንደሚችል ተተንብዮ ነበር፡፡ ሕወሓት በጥጋቡ ምክንያት ያመጣውን ሰቆቃ ራሱ ኃላፊነቱን መውሰድ ሲገባው፣ የሕወሓት የእንግዴ ልጆች ጣታቸውን ሌላ ቦታ እየቀሰሩ ሲያላዝኑ ያስቁኛል፡፡ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊትም ሆነ ከተጀመረ በኋላ በአሸናፊነት ስሜት ሲመፃደቁና ያዙኝ ልቀቁኝ ሲሉ የነበሩ በሙሉ፣ ሽንፈትን ሲጎነጩ ሌላ ተረት ይዘው ይዘባርቃሉ፡፡ ውሸት እየፈበረኩ ድል በድል ሆነናል ባሉ ማግሥት አለቆቻቸው ሲደመሰሱና እጅ ሲሰጡ ሲያዩ ደግሞ፣ በትግራይ ሕዝብ ስም ማላዘን ይጀምራሉ፡፡ ከዚህ በላይ ድንቁርና ከየት ሊመጣ ይችላል? ሰሞኑን አውሮፓና አሜሪካ ሠልፍ ወጥተው መሬት ላይ ሲንደባለሉ የነበሩ ቢጤዎቻቸውን ሲታዘብ የነበረው ያ የጥንቱ ጓደኛዬ፣ ‹‹ከእንበር ተጋዳላይ ወደ እንበር ተንደባላይ እንኳን አደረሳችሁ!›› በማለት ትዊተር ላይ የጻፈው በእጅጉ አዝናንቶኛል፡፡ ምድረ ሌባ አለቆቻቸው እንዳይመለሱ ተደርገው ሲሸኙ ጥቅማቸው ጎድሎ እንጂ፣ ለትግራይ ሕዝብ ብለው በዚህ ቅዝቃዜ በረዶ ላይ እንደማይንደባለሉ የታወቀ ነው፡፡ ማን ነበር ‹ይኼ ለቅሶ ከፍየሉ በላይ ነው› ያለው?
(ነገደ ሥዩም፣ ከሩፋኤል)