Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የበይነ መረብ ግብይትን እያስፋፋ መሆኑን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ተገበያዮች ካሉበት ቦታ ሆነው ግብይት መፈጸም የሚችሉበትን የበይነ መረብ (የኦንላይን) ሥርዓት ለመተግበር የሚያስችለውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡ በየክልሉ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከላትን ለመክፈት የያዘውን ዕቅድ እየተገበረም ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ይህንን ያስታወቀው ሐሙስ ጥር 27 ቀን 2013 ዓ.ም.  በጎንደር ከተማ ለአገልግሎት ያበቃውን የኤሌክትሮኒክ ግብይት  ማዕከል  ሲያስመርቅ ነው፡፡

በዚህ ምረቃ ሥርዓት ላይ የተገኙት የምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድምአገኘሁ ነገራ እንዳመለከቱት፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አሠራሩን የበለጠ ለማዘመን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሦስተኛውን ጄኔሬሽን እያዘጋጀ ነው፡፡ ይህም ተገልጋዮች ካሉበት ቦታ ሆነው ግብይት መፈጸም የሚችሉበትን የኦላይን ሥርዓት ለመጀመር የሚያስችል ይሆናል፡፡

ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ በሚገኘው ዋናው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የግብይት ማዕከል ብቻ ይከናወን የነበረው የኤሌክትሮኒክ ግብይት፣ የግብይት ተዋናዮች ባሉበት አካባቢ ሆነው መገበያየት የሚችሉበትን ዕድል የፈጠረ ሲሆን፣ በተያዘው ዕቅድ መሠረትም ተጨማሪ የግብይት ማዕከላት እየተገነቡና ለአገልግሎት እየበቁ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

ከጎንደሩ ማዕከል ሌላ ተመሳሳይ አገልግሎት ለመስጠት ግንባታቸው የተጠናቀቁት የጅማና የአዳማ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከላት በቅርቡ አገልግሎት እንደሚጀምሩ አቶ ወንድምአገኘሁ ገልጸዋል፡፡

የጎንደር ኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከል የግንባታ፣ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች የቢሮ መገልገያዎችን ጨምሮ በጥቅል 14.8 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት መሆኑም ታውቋል፡፡ ይህ የግብይት ማዕከል በአንድ ጊዜ እስከ ዘጠና ተገበያዮችን ማስተናገድ ይችላል፡፡

የኤሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከሉ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ያለምንም የሊዝ ክፍያ ለምርት ገበያው በሰጠው ሁለት ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተገነባ ነው፡፡ ይህ ማዕከል በጎንደር ከተማ መከፈቱ በተለይም በአማራ ብሔራዊ ክልል በተለያዩ ዞኖች የሚገኙ አቅራቢዎችና የኅበረት ሥራ ማኅበራት አዲስ አበባ በመምጣት በዋናው ማዕከል ለመገበያየት የሚያወጡትን ወጪ፣ ጊዜና ጉልበት የሚያስቀርላቸው ነው፡፡

በዚህ ማዕከል የሚደረገው ግብይት አዲስ አበባ ላይ ከሚካሄዴው ግብይት የማይለይ፣ በተመሳሳይ ሥርዓትና ጊዜ የሚካሄድ በመሆኑ የማዕከሉ መገንባት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ተብሏል፡፡

በክልሉ ከሰሊጥ በተጨማሪ የተለያዩ ሰብሎችና ለግብርና ምርት ማቀነባባሪያ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆኑ ምርቶች በብዛት ስለሚገኙ ይህ የግብይት ማዕከል እነዚህንም የማገበያየት አቅም ይኖረዋል፡፡

ከዚህ ማዕከል በተጨማሪ በጎንደር ከተማ ኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከ61.8 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለውና በአንድ ጊዜ 150 ሺሒ ኩንታል የሚይዝ ዘመናዊ መጋዘን እያስገነባ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚሁ ጋር ዘመናዊ የምርት ጥራት መፈተሻ ላቦራቶሪ፣ የምድር ሚዛን፣ ቢሮዎችና ሌሎች አገልግሎቶች ይኖሩታል፡፡ ግንባታው በቅርቡ ተጠናቆም አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሏል፡፡

የምርት ገበያውን የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከልና ቅርንጫፍ ማስፋፋት ጋር ተያይዞ ምርት ገበያው እንዳስታወቀው፣ ወደ አርሶ አደሩ በመቅረብ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በኢትዮጵያ 23 የምርት መቀበያ ቅርንጫፎችን አቋቁሞ እየሠራ ነው፡፡ እያንዳንዳቸው የምርት ጥራት ደረጃ የሚፈተሽባቸው ላቦራቶሪዎች አሏቸው፡፡

በዚህ ዓመትም በቴፒና በሚዛን አማን ከተሞች ተጨማሪ ቅርንጫፎች ተከፍተው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ ከኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከል ግንባታ ሌላ በቅርቡ በባህር ዳር ቅርንጫፍ የሚከፈት ሲሆን፣ በሻኪሶና በቀለም ወለጋ አዳዲስ ቅርንጫፎች ለመክፈት ጥናት እያካሄደ መሆኑን ምርት ገበያው አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ጥር 2013 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ሰባት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ምርት በ299 ቢሊዮን ብር አገበያይቷል፡፡ በተለይም ኅዳር 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ በአንድ ቀን ውስጥ 502 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው ምርት እስከ ማገበያየት ስለመድረሱ አቶ ወንድምአገኘሁ ተናግረዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ለግብርና ምርት አቀነባባሪዎች በከፈተው ልዩ የግብይት መስኮት እስካሁን 191,645 ኩንታል አኩሪ አተር በ373 ሚሊዮን ብር አገበያይቷል፡፡ ይህም የግብርና ምርቶችን በጥሬው ወደ ውጭ ለመላክ እሴት ጨምሮ በማምረት ለጥሬ ዕቃዎች የሚውለውን ውጭ ምንዛሪ ለማዳንና ከአኩሪ አተር ኤክስፖርት የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት ለሚደረገው አገራዊ ጥረት ከፍተኛ አስተወጽኦ አለው ተብሏል፡፡

በቅርቡም አርሶ አደሮች፣ አቅራቢዎች፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራትና ላኪዎች ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚሰጣቸውን የምርት መረከቢያ ደረሰኝ ለባንክ በማቅረብ የአጭር ጊዜ ብድር የሚያገኙበት አሠራር ሥራ ላይ ማዋሉን የሚያመለክተው የምርት ገበያ መረጃ፣ በመጪዎቹ ዓመታትም ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸውንና ወደፊትም የምታፀድቃቸውን አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የንግድ ስምምነቶች መሠረት በማድረግ፣ የዘመናዊ ግብይቱን አድማስና ተደራሽነት ለማስፋት የሚያስችሉ ሥራዎች ይሠራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እንደ አቶ ወንድምአገኘሁ ገለጻ፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የሚበቃ በዘመናዊ የግብይት፣ የተለያዩ አሠራሮች ላይ ያተኮረ የምርምር፣ የሥልጠናና ሠርተፊኬሽን ማዕከል መክፈት እንዲሁም በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ ዜጎች በተለይም ለሴቶችና ለወጣቶች ገበያ ዕድል የሚያሰፋ ድጋፍ የማድረግ ሥራ ይሠራል፡፡

 የኢንዱስትሪና የማዕድን ምርቶችን ወደ ዘመናዊ  ግብይት ማካተት፣ የገበያ አድማስን ወደ አፍሪካ አገሮች ማሳደግ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች