Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከግብይት ሥርዓቱ ሸፍጦች ገላግሉን!

በግብይት ሥርዓታችን ውስጥ ያለው ችግር በርካታ መገለጫዎች አሉት፡፡ አደገኛም እየሆኑ ነው፡፡ ከጉሊት እስከ ትልቅ የገበያ ሥፍራዎች የምናየው የግብይት ሥርዓት ወግ የለውም፡፡ ደንበኛ ተኮር ወይም ሸማቾችን ያገናዘበም አይደለም፡፡

የአገልግሎት አሰጣጣችንን ጨምሮ የገበያ ዋጋ ምጣኔያችን፣ የትርፍ ህዳግ ሥሌታችን በዘፈቀደ የሚካሄድና ልክ አልባ ነው፡፡ ደንበኛን በአግባቡ የማስተናገድ ባህል አላዳበርንም፡፡ አብዛኞቹ የግብይት ቦታዎቻችንም ለሸማቾች ምቹ አይደሉም፡፡ ብዙዎቹ የገበያ ሥፍራዎች ንፁህና ፅዱ አይደሉም፡፡

ገበያ የምንለው ሥፍራ ውጫዊ ገጽታው ብቻ ሳይሆን በዚያ ገበያ ውስጥ ያሉ መደብሮች ውስጣዊ ይዞታዎችም ጭምር ፅዱና ምቹ ሊሆኑ ይገባል፡፡ በአንድ የግብይት ሥርዓት ውስጥ መኖር የሚገባው የውድድር መንፈስም የለም፡፡ ደንበኞችን ለመሳብ አንዱ ከሌላው የሚለይበት አሠራር አልጎለበተም፡፡ እንዲያውም በብዙ ገበያዎች ተመካክሮ ምክንያታዊ ያልሆነ ዋጋ በመትከልና ገበያን የመበረዝ ዝንባሌ የሚታይባቸው መሆኑም ይታያል፡፡

ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርቶችን ለተገልጋዮች ማቅረብ፣ ጊዜ ያለፈባቸውን ምርቶች ያለ ይሉኝታ በመደብር ሼልፎች ላይ ደርድሮ መሸጥም ለእኛ አገር ገበያ ብርቅ አይደለም፡፡

ታላቅ የዋጋ ቅናሽ ተብሎ ምንም ቅናሽ የሌለው ሽያጭ ሲፈጸምና ተገልጋዮችን በማታለል የሚፈጸመው ድርጊቶች የአገራችን የግብይት ሥርዓት ሌላው መገለጫ ሆኖ እየተስፋፋ ነው፡፡ ከባዕድ ነገሮች ጋር ተቀላቅለው የሚዘጋጁ ምርቶች ገበያ ውስጥ ያለ ችግር የመሸጣቸው ነገርም ነጋ ጠባ የሚሰማ ነው፡፡ ዛሬም የአገራችንን አጠቃላይ የግብይት ሥርዓት ምን ያህል በክፋት የታጀለ መሆኑን የሚያሳዩን አሳዛኝ ድርጊቶች ከመሻሻል ይልቅ ብሶባቸዋል፡፡

በአንዳንድ ፋርማሲዎች በአደባባይ መሃላ የገቡለትን አደራ የበሉ ባለሙያዎች  በኮንትሮባንድ የመጡና ፈዋሽነታቸው ያልተረጋተጡ መድኃኒቶችን ደርድረው ይሸጣሉ መባሉን ስንሰማ ደግሞ፣ ሕገወጥ ግብይት ወይም በተጭበረበረ መንገድ ገንዘብ ከደረት ለማስገባት የማይጣርበት የቢዝነስ ዘርፍ የለም ብለን እንድንደመድም ያደርገናል፡፡

ይህ ባልተገባ መንገድ የሚፈጸሙ የግብይት ሥርዓቶች ምን ያህል እንደተስፋፉ ከማመልከቱም በላይ፣ እንዲህ ያሉ ፅዩፍ ተግባራት ትውልድን እያበላሹ እስከመቼ ይቀጥላሉ የሚለው ጉዳይ በእጅጉ ሊያሳስበን ይገባል፡፡

በልኬት ሚዛን ላይ የፈጸመውን ማጭበርበር ካነሳንም የሸማች ፍዳ ብዛት ተቆጥሮ አያልቅም፡፡ አንቱ የሚባሉ አስመጪዎች በትዕዛዝ የሚያመጡትን ዕቃ በርካሽ ለማስገባት የሚመረትበት አገር ድረስ ሄደው ከደረጃ በታች የሆነ ዕቃ አዘው አገር ውስጥ በከፍተኛ ትርፍ ሲቸበችቡት፣ የሚሸጡት ለወገናቸው ስለመሆኑ የሚረሱት ይመስላል፡፡

እንዲህ እንዲህ እያልን በየቢዝነስ ዘርፉ ያሉበትን ከገበያ ጋር የተያያዙ ሸፍጦች እንዘርዝር ከተባለ ጠቅሰን አንጨርሰውም፡፡ ሥነ ምግባር የሚባል ነገር በብዙዎች የቢዝነስ ዘርፎች አይታይም፡፡

በጥቅል ሲታይ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ በሚታዩ ሸፍጦች ከታች እስከ ላይ በሰፊው የተንሰራፋ ደንበኛ ተኮር ሳይሆን፣ የራስን ጥቅም በማስጠበቅ የሚፈጸም፣ ለሌሎች ደንታ ቢስነስ የሚታይበት ነው፡፡ በሥነ ምግባር የማይመራ ስለመሆኑም በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡

በግብይት ውስጥ የሚታዩ ብልሹ አሠራሮችንና ሸማቾች ላይ የሚፈጠረውን ችግር ይፈታሉ፣ ቁጥጥርም ያደርጋሉ የተባሉ ተቋማትም ቢሆኑ እየተንሰራፋ የመጣውን ትልቅ ችግር ጉዳዬ አላሉትም፡፡ የእነሱ አቅም ማጣትና በሕግ የተቋቋሙለትን ተግባር አለመፈጸም ድርጊቱ እንዲስፋፋ ዋነኛ ምክንያት ሆኖ ሊቀርብ እንደሚችል መዘንጋት የለብንም፡፡

በሌላ በኩልም ሸማቾችም መብታቸውን ለማስከበር ወኔ ማጣታቸው ለችግሩ መስፋፋት የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በአግባቡ አለመነገድና ነግዶ ለማትረፍ የግድ ሕገወጥ ተግባር መፈጸም አለበት ወይ? ብሎ የሚጠይቅ ማኅበረሰብና ሕግ ፊት አጥፊዎችን የሚያቆም ሕግ አስፈጻሚ ያሻናል፡፡

ሕገወጥ ተግባራት በተበራከቱ ቁጥር በበጎ ህሊና ለመሥራት የሚጥሩትንም እየበረዘ ይሄዳልና ሥነ ምግባር ያለው ለህሊናውም ጭምር የሚሠራ አገልጋይ ለመፍጠር ሕገወጦችን አደብ ማስገዛት የግድ ነው፡፡ ማኅበረሰቡም ጠያቂ መሆን አለበት፡፡

ዛሬ አላግባብ ለመበልፀግ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መካከል ንፁኃንም አሉ፡፡ ባልተገባ መንገድ ለመጠቀም ገበያ ውስጥ ትርምስ የሚፈጥሩ ግለሰቦች ምንም ሳይሆኑ ያዩ በሥነ ምግባር የሚሠሩ ዜጎችም ሕገወጥ መንገዱን እንዳይመርጡ በብርቱ ሊሠራ ይገባል፡፡ ድርጊቱ ሄዶ ሄዶ ንፁኃንንም እየበከለ፣ በከተሞች አካባቢ የተወሰነ ነው የተባለው የማጭበርበርም ወደ ገጠር እየገባ የቢዝነስ ትርጉሙን እያዛባው እንደሆነም መረዳት አለብን፡፡

ችግሩ እየተስፋፋ መሆኑን ለማሳየት ሰሞኑን አንድ ዘመዴ ከአዲስ አበባ ውጪ የገጠመውንና እኔም በዓይኔ ያየሁትን አንድ ድርጊት የዛሬው ጽሑፍ ማጠናቀቂያ ላድርግ፡፡

ዘመዴ ከአዲስ አበባ ውጪ ቆይቶ በሻሸመኔ መንገድ ወደ ቤቱ ሲመለስ ለቤቱና ለቅርብ ዘመዶቹ ስድስት ‹‹ኩንታል›› (ትልቁ ማዳበሪያ) ከሰል እያንዳንዱን በ600 ብር ገዝቶ ይመጣል፡፡ ለራሱ ያለውን ቤት ያስቀርና ቀሪውን እመረቅ ብሎ አስቦ ለገዛላቸው ቤተሰቦች ይሰጣል፡፡ አንድ ከሰሉን ለማሰናዳት ከማዳበሪያው የገለበጠ ዘመድ ስልክ መታለትና ከግማሽ በላይ የሚሆነው የማዳበሪያው ክፍል ከሰል ሳይሆን በበሃ ድንጋይ የተሞላ እንደሆነ ነገረው፡፡ ስድስቱም ኩንታል በአብላጫው የተያዘው በኮረት ሆነ፡፡ እንግዲህ ልብ በሉ የዋህ ፊት ይዞ አጭበርበሮ ለመክበር የሚፈጸመው ደባ እንዲህ ባለ ደረጃ ጭምር የሚጠቀስ ሆኗል፡፡

ይህ የሚያሳየን በጊዜ መቆጣጠር ያልቻልነው ብልሹ አሠራር በማጭበርበር ለመክበር መሞከር ያልደረሰበት ቦታ አለመኖሩን ነው፡፡ ይህ አጭበርብሮ ለመክበር የሚፈጸሙ ተግባራትን ተከትሉ ሥነ ምግባር ያለው ግብይት ለመፍጠር ከባድ ሥራ እንደሚጠይቅ ያሳያል፡፡ አሁንም አልረፈደምና የውንብድና ቫይረሱ ሁሉንም በክሎ ሳይጨርስ አንድ መላ ሊበጅለት ይገባል፡፡ የግብይትና የአሠራር ባህላችን ይቀየር፡፡ ለዚህም ሁሉም ኃላፊነቱን ይወጣ፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት