በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የዳያስፖራ አባላት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ በአገር ውስጥ ለሚደረገው የመከላከል ሥራ 45.6 ሚሊዮን ብር መርዳታቸውን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ፍፁም አረጋ አስታወቁ፡፡
‹‹ለኮቪድ-19 ክትባት የማግኘት ሥጋትና ተስፋ›› በሚል መሪ ሐሳብ ፒፕል ቱ ፒፕል እና የኢትዮጵያ ዳያስፖስራ አማካሪ ካውንስል ጥር 29 ቀን 2013 ዓ.ም. ባደረጉት የበይን መረብ ውይይት የተሳተፉት አምባሳደር ፍፁም እንደገለጹት፣ በኮቪድ-19 ምክንያት የአሜሪካ ኢኮኖሚ በመመታቱ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ እንደማንኛውም ዜጋ ሥራ ቢያጣም፣ ካለው ጥሪት በማውጣት በኢትዮጵያ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ያዋጣው ገንዘብ ለዚሁ ተግባር በተከፈተ የባንክ ሒሳብ ገቢ ተደርጓል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ወረርሽኙን ለመከላከል የሚረዱ ቁሳቁሶችን በማሰባበሰብ በኢትዮጵያ አየር መንገድ 21 በረራዎች አማካይነት ወደ አገር ቤት እንዲላክ መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡
መድረኩን ያዘጋጁት ሁለቱ ተቋማት ለኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ትብብር ያደነቁት አምባሳደሩ፣ ክትባት በማግኘት ረገድ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታት የዳያስፖራ የዘርፉ ባለሙያዎች የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ኢኮኖሚውን፣ ማኅበራዊ ሕይወቱን፣ ሥነ ልቦናውንና የጤና ዘርፉን የጎዳው የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል አሁን ላይ በርካታ ክትባቶች እየተገኙ በመሆኑ፣ ማኅበረሰቡን ለመታደግ ተስፋ ነው ያሉት የፒፕል ቱ ፒፕል ፕሬዚዳንት እናውጋው መሐሪ (ዶ/ር)፣ ‹‹የትኛው ክትባት ጥሩ ነው? ጥቅሙና አደጋውስ? እንዴት ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል? በሚለው ላይ አማካሪ ካውንስሉና ድርጅታቸው ሙያዊ ዕገዛውን አጠናክሮ ይቀጥላል፤›› ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ክትባቱን ለማግኘት እየሠራች መሆኑን ያስታወሱት የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኤባ አባተ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በኅብረተሰቡ በኩል ተቀባይነት የማግኘትና የተደራሽነት ችግር ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ሆኖም ችግሮች ቢኖሩም ኅብረተሰቡ በተለይ በአዲስ አበባ አፍና አፍንጫውን እንዲሸፍን ወይም ማስክ እንዲያደርግ ከበፊት ጀምሮ እየተሠራበት መሆኑን አክለዋል፡፡