Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አየር መንገዱ ዓለም አቀፍ ቀውሱን በመቋቋም በአትራፊነት እንደሚቀጥል ተነገረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮሮና ቫይረስ የፈጠረውን ዓለም አቀፋዊ ቀውስ በመቋቋምና ያለ ምንም ድጋፍ በአትራፊነት የቀጠለ ብቸኛው አየር መንገድ ሊሆን እንደሚችል፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ገለጹ፡፡

አቶ ተወልደ ይህንን የገለጹት ማክሰኞ የካቲት 2 ቀን 2013 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሠራተኞች፣ የቤትና የመኪና መግዣ ብድር በአነስተኛ ወለድ እንዲያገኙ የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት፣ ከኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ጋር በተፈረመበት ወቅት ነው፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተለይ ባለፈው አንድ ዓመት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት  ትልልቅ የሚባሉ አየር መንገዶች ሥራ እስከማቆም ቢደርሱም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ችግሩን በመቋቋም ከሌሎች በተለየ አትራፊ ሊሆን መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በኮሮና ቀውስ ምክንያት የተለያዩ አየር መንገዶች በቢሊዮን የሚቆጠር የገንዘብ ድጋፍ ከመንግሥቶቻቸው ተደርጎላቸው ሥራቸውን እንዲቀጥሉ የተደረገበት ሁኔታም ተፈጥሮ ነበር ያሉት አቶ ተወልደ፣ በአፍሪካም ትልልቅ ኢኮኖሚ ያላቸው እንደ ደቡብ አፍሪካ ያሉ አየር መንገዶች እስከ መዘጋትና ሠራተኞችንም ማሰናበታቸውን ጠቁመዋል፡፡ የኬንያ አየር መንገድም ትልቅ ቀውስ ውስጥ እንደሚገኝና ከግማሽ በታች የሆነ አገልግሎት እየሰጠ ነው ብለዋል፡፡

ትልልቅ የሚባሉ አየር መንገዶች በኪሣራ በተዘፈቁበት ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን አፍሪካ ውስጥ ትልቁ አየር መንገድና ትርፋማ ሆኖ ሥራውን የቀጠለ መሆኑን አስታውሰው፣ ወቅታዊውን ችግር ልዩ በሆነ መንገድ እየተወጣው ይገኛል ሲሉም የአየር መንገዱን ጥንካሬ አመላክተዋል፡፡

‹‹ይህንን ወቅት በልዩ ሁኔታ ልንወጣ የቻልንበት ዋናው ምክንያት፣ የሠራተኛው ታታሪነትም ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹እኛ እንደ ማኔጅመንት ስትራቴጂ እናወጣ ይሆናል እንጂ፣ ትልቁ ምሰሶ ሠራተኛው ከእኛ ጋር በአንድ አቅጣጫና ዓላማ ለድርጅቱ ስለቆመ ነው፤›› በማለት አቶ ተወልደ ሠራተኞችን አመሥግነዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬት ዋነኛው ሠራተኛው ነው ብለው እንደሚያምኑ የጠቀሱት አቶ ተወልደ፣ ከትልልቆቹ አየር መንገድ ጋር ሲወዳደር ትልቁ መወዳደሪያው ሠራተኛው እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች ከሚገባቸው በላይ የሚሠሩና የአየር መንገዱን ህልውናና ዕድገት ከምንም በላይ አስቀድመው የሚፈለገውን መስዋዕትነት የሚከፍሉ መሆናቸውን ባለፉት 75 ዓመታት ያስመሰከሩ ቢሆንም፣ ባለፈው አንድ ዓመት ያሳዩት የሥራ ክንውን እጅግ በጣም የሚደነቅ ነው፤›› በማለት አየር መንገዱ ከአሁን በኋላ ምንም ዓይነት ቀውስ ቢያጋጥመው ማለፍ የሚችል መሆኑን ለዓለም ያስመሰከረበት ወቅት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በተለይ ባለፈው አንድ ዓመት በአንድ በኩል ኮሮናን ለመከላከል በሌላ በኩል ካርጎም ሆነ የመንገደኛ አገልግሎት ተቀራምተው ተወዳድረው በማሸነፍ በቂ ገንዘብ በማግኘት፣ ብድሮቻቸውን ስለመክፈላቸውም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ‹‹ቋሚ ወጪዎቻችን ሸፍነንና ደመወዝ ከፍለን መቀጠል እንድንችል ከፍተኛ የሠራተኛ ርብርብ በሚደረግበት ጊዜ፣ የሠራተኛ ማኅበሩ በቀዳሚነትና በመሪነት ሠራተኛውን አስተባብሮ ከማኔጅመንቱ ጋር በመቆም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፤›› በማለት ማኅበሩም ምሥጋና ይገባዋል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች