በመተከልና በትግራይ ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ኢትዮጵያዊያን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ፡፡
ጥሪው የቀረበው የግሎባል አሊያንስ፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር፣ የበጎ ፈቃደኞች ማኅበር፣ እንዲሁም ሌሎች ተቋማት ማክሰኞ የካቲት 2 ቀን 2013 ዓ.ም. በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡ ወቅቱም ‹‹ሰብዓዊነትና ፍቅር ለትግራይና ለመተከል›› በሚል መሪ ቃል የሚተገበር መርሐ ግብር መሆኑን ተገልጿል፡፡
የግሎባል አሊያንስ ሊቀመንበር ታማኝ በየነ እንደገለጸው፣ በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍ መንግሥትም ሆነ ማኅበረሰቡ የበኩለን መወጣት እንዳለበት አስረድቷል፡፡
የማናለብኝነትን ስሜት በመተው ሜዳ ላይ የወደቁ እናቶችን፣ አረጋውያንንና ሕፃናትን በመደገፍ፣ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት የተጀመሩ ድጋፎች በማጠናከር የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀዬአቸው መመለስ እንደሚያስፈልግ ታማኝ አሳስቧል፡፡
የተፈናቀሉ ዜጎች ካሉበት ችግር ወጥተው መሠረታዊ የሆነ ፍላጎታቸው እንዲሟላ ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይገባል ብሏል፡፡
በትግራይና በመተከል የተጎዱ ወገኖች ያሉበት ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ በቁሳቁስ፣ በምግብ፣ በገንዘብም ድጋፍ በማድረግ ካሉበት ችግር እንዲወጡ ለማድረግ የተጀመረው እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑን የትግራይ ክልል ዕርዳታ አሰባሳቢ በጎ ፈቃደኞች ማኅበር ሰብሳቢ ወ/ሮ ፍሬወይኒ ገብረ ፃዲቅ ተናግረዋል፡፡
የተጀመረው ድጋፍ በዘላቂነት ለማስቀጠልና በቂ ግብዓቶችን ለተፈናቀሉ ዜጎች ለማድረስ፣ በጋራ መሥራት እንደሚገባ ወ/ሮ ፍሬወይኒ አሳስበዋል፡፡
በአዲስ አበባ በጣይቱ ሆቴል፣ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ጽሕፈት ቤትና ከአዲስ አበባ ውጪ በሚገኙ የቀይ መስቀል ማኅበር ቅርንጫፎች የቁሳቁስ ማሰባሰቢያዎች መዘጋጀታቸው ተገልጿል፡፡
የገንዘብ ድጋፍ ለሚያደርጉ ሰዎችም በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ስም በተከፈተው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሒሳብ ቁጥር 10003277016559፣ እንዲሁም በመላው ዓለም ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን በግሎባል አሊያንስ በኩል በተከፈተው ‹‹በትግራይና በመተከል ለተጎዱ ወገኖቻችን የበኩልዎን ይረዱ ዘንድ እናሳስባለን›› በማለት በተከፈተው ‹‹ጎ ፈንድ ሚ አካውንት›› መደገፍ እንደሚቻል ተገልጿል፡፡