የአበበ ቢቂላን ፈለግ ተከትሎ በትውልድ ቅብብሎሽ ዛሬ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ፣ በኮቪድ-19 ምክንያት ለአንድ ዓመት ተራዝሞ ከወራት በኋላ በጃፓኗ ቶኪዮ ከተማ ለሚካሄደው ኦሊምፒክ በከፍተኛ ዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ተስፋ ከጣለችባቸው አትሌቶች አንዱ የሆነው ሰለሞን ባረጋ፣ ባለፈው ቅዳሜ በፈረንሣይ ሜትዝ በተደረገው በ1,500 ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር አሸናፊ ሆኗል፡፡ ታዳጊዋ እንስት ሀብታም ዓለሙም በ800 ሜትር አሸናፊ ሆናለች፡፡
‹‹ሜትዝ ሞሶሌ አትሌቶር›› በሚል በፈረንሣይ በተካሄደው የቤት ውስጥ ውድድር አሸናፊ የሆነው ሰለሞን ባረጋ፣ ርቀቱን ለማጠናቀቅ 3፡ 34. 62 ጊዜ የፈጀበት ሲሆን፣ ኬንያዊው ብራያን ቤትዌል 3፡ 34. 67 በመግባት ሁለተኛ ሆኗል፡፡ እንግሊዛዊ ግሌስ ኤሊዮት ደግሞ ሦስተኛ ወጥቷል፡፡
በትልልቅ ዓለም አቀፍ መድረኮች በዚህ ርቀት ከኢትዮጵያውያን ይልቅ ኬንያውያን አትሌቶች በውጤታማነት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ኦሊምፒክን ጨምሮ በሌሎችም ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ኬንያውያን በመነሳት ሰለሞን ባረጋ ያስመዘገበው ውጤት ምናልባትም ኢትዮጵያ ከአምስት ወራት በኋላ በቶኪዮ ይከናወናል ተብሎ በሚጠበቀው ኦሊምፒክ ላይ ተስፋ ካደረገቻቸው አትሌቶች አንዱ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
የመካከለኛ ርቀት አንድ አካል በሆነው 800 ሜትር እንደ ሰለሞን ሁሉ፣ እንስቷ ሀብታም ዓለሙ ያስመዘገበችው ውጤት፣ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ሌላዋ የኢትዮጵያ ተስፋ ሆና ብቅ ብላለች፡፡ እንደሚታወቀው በ800 ሜትር ከዚህ በፊት በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሜዳሊያ በማስመዝገብ በቀዳሚነት መሐመድ አማን ይጠቀሳል፡፡ በትልልቅ መድረኮች በወንዶች እሱን የሚተካ እስካሁን ማፍራት አልተቻለም፡፡ በሴቶችም ቢሆን በአንድ ወቅት ብቅ ብላ ከጠፋችው ፋንቱ ሜጌሶ በስተቀር በርቀቱ ብዙም ሊጠቀስ የሚችል ተፎካካሪ አትሌት ማፍራት እንዳልተቻለ የሚታወቅ ነው፡፡