Tuesday, July 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምበኢራን ላይ የተጣለው ማዕቀብ አለመነሳት

በኢራን ላይ የተጣለው ማዕቀብ አለመነሳት

ቀን:

አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከመመረጣቸው በፊት አሜሪካ በኢራን ላይ የጣለችውን የኢኮኖሚ ማዕቀብ ሊያነሱ ይችላሉ ተብሎ የተገመተ ቢሆንም፣ ይህ እንደማይሆን አስታውቀዋል፡፡

አልጄዚራ እንደዘገበው፣ ኢራን እ.ኤ.አ. በ2015 የገባችውን የኑክሌር ስምምነት ዳግም ተግባራዊ ካላደረገች የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ ያጠነከሩት ማዕቀብ እንደማይነሳ ገልጸዋል፡፡

በ2015 ኢራን ከአሜሪካ፣ ከቻይና፣ ከፈረንሣይ፣ ከጀርመን፣ ከሩሲያና ከእንግሊዝ ጋር ከገባቸው የኑክሌር ስምምነት፣ ትራምፕ በ2018 አሜሪካን አግልለው ተነስቶ የነበረውን  ማዕቀብ ዳግም መጣላቸው ይታወሳል፡፡

‹‹የኑክሌር ማብላያው ለሰላማዊ ጥቅም ነው›› በማለት ስትከራከር የኖረችው ኢራን፣ ከ2018 ወዲህ ያላትን የዩራኒየም ክምችት ማሳደግም ጀምራለች፡፡ የበለፀገ የዩራኒየም ክምችት ደግሞ እንደ ኃይል ምንጭ ብቻ ሳይሆን የኑክሌር ብምብ ለመሥራትም ያገለግላል፡፡

የኢራን ዩራኒየም ክምችት ለኑክሌር ጦር መሣሪያ እንዳይውል ሥጋት የገባችው ኃያላን አገሮች፣ ከስድስት ዓመት በፊት በደረሱት ስምምነት ዓለም አቀፍ ተቆጣጣሪዎች የዩራኒየም ማብላያውን ሥፍራና ቁሳቁስ እንዲጎበኙና የበለፀገ ዩራኒየም ክምችትም መሆን ያለበት መጠን ላይ ስምምነት ተደርሶ ነበር፡፡ ሆኖም አሜሪካ ያንን ስምምነት ከሁለት ዓመት በፊት ጥላ በመውጣቷና የኢኮኖሚ ማዕቀብ ዳግም በመጣሏ በኢራንና በአሜሪካ መካከል ጋብ ብሎ የቆየው የኑክሌር ውዝግብ ዳግም አገርሽቷል፡፡

የትራምፕ መንግሥት በኢራን ላይ ዳግም የጣለው ማዕቀብ እንዳይፀና፣ አሜሪካም ከስምምነቱ እንዳትወጣ ፈራሚ አገሮቹ ጥረት ቢያደርጉም፣ አልተሳካም ነበር፡፡ ጆ ባይደን ወደ ሥልጣን ሲመጡ ኢራንና አሜሪካ በኑክሌር ላይ ያላቸውን ውዝግብ ይፈታሉ፣ ዳግም በኢራን ላይ የተጣለው የኢኮኖሚ ማዕቀብ ዕልባት ያገኛል ተብሎ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም፣ ባይደን በኢራን ላይ የተጣለው ማዕቀብ የሚነሳው ኢራን የ2015 ስምምነትን ተግባራዊ ስታደርግ ነው ብለዋል፡፡

ባይደን በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ኢራንን ወደ ኑክሌር ስምምነት ለመመለስ ተስፋ እንዳላቸው አስታውቀው ነበር፡፡ ሆኖም ወደ ዋይት ሐውስ ከገቡ በኋላ አስተዳደራቸው ኢራን ቀድማ ወደ 2015 ስምምነት ካልመጣች ማዕቀቡን አናነሳም ብሏል፡፡

ትራምፕ በኢራን ላይ ከፍተኛውን ጫና ለመፍጠር ብለው ከስምምነቱ መውጣታቸውን ተከትሎ ኢራን የዩራኒየም ማበልፀግ ሥራዋንና ክምችቷን አጠናክራ መቀጠሏ የተነገረ ሲሆን፣ የባይደንን ውሳኔ ተከትሎም የሚቀየር ነገር እንደማይኖር ታውቋል፡፡

የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያ ቶላህ አልሃሚኒ አሜሪካ ወደ 2015ቱ ስምምነት ቀድማ መምጣት አለባት ብለዋል፡፡

‹‹ኢራን ወደ 2015ቱ የኑክሌር ስምምነት እንድትመለስ አሜሪካ የጣለችውን ማዕቀብ ሙሉ በሙሉ ማንሳት አለባት፣ ይህ በቃል ሳይሆን በወቀት ላይ መስፈር አለበት፣ ማዕቀቡን ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ እኛም መነሳቱን እናረጋግጣለን፤›› ብለዋል፡፡

የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሃመድ ጃቫድ ዛሪፍ በበኩላቸው፣ የአውሮፓ ኅብረት ባለሥልጣናት የኑክሌር ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን ማመቻቸት አለባቸው ብለዋል፡፡ በአሜሪካ በኩል የሚለወጥ ነገር እንደማይኖር ደግሞ የባይደን አስተዳደር አስታውቋል፡፡

በኢራን ላይ የተጣለው ማዕቀብ አለመነሳት

 

የኢራን ኑክሌር ስምምነት ለምን ፈረሰ?

በ2015 በኢራንና በስድስቱ አገሮች አሜሪካ፣ ቻይና፣ ፈረንሣይ፣ ጀርመን፣ እንግሊዝና ሩሲያ መካከል የተደረሰው ስምምነት፣ ኢራን የዩራኒየም ክምችት ገደብን እንዳታልፍና ዓለም አቀፍ ተቆጣጣሪዎችም የዩራኒየም ማብላያ ጣቢያዎችን እንዲጎበኙ ነበር፡፡

ኢራን ይህንን ስታደርግ በርሷ ላይ ተጥለው የነበሩ ማዕቀቦች ተነስተዋል፡፡ ሆኖም ትራምፕ በ2018 ኢራን ላይ ተጨማሪና ጠንከር ያሉ ክልከላዎች ለማስቀመጥ አዲስ ስምምነት ለማድረግ አስበው ከስምምነቱ ወጥተው ነበር፡፡ ተነስቶ የነበረውን የኢኮኖሚ ማዕቀብ መልሰው ጫኑት፡፡

ትራምፕ ይህን ያደረጉት የኢራንን የባለስቲክ ሚሳየል ልማት ለማስቆም ፈልገው እንደነበረም ይነገራል፡፡ ነገር ግን አሜሪካ ከስምምነቱ ራሷን ማግለሏን ተከትሎ ኢራን ዩራኒየም እያበለፀገች ነው፡፡ ከአሜሪካ ጋር ለድርድር ያቀረበችውም አሜሪካ ማዕቀቡን ስታነሳ ኢራን የ2015 ስምምነት ትተገብራለች የሚለውን ሐሳብ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...