Thursday, September 21, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሠራተኞችን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ የተደረገ የብድር ስምምነት

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ረዘም ያለ ዕድሜና ጠንካራ የሠራተኛ ማኅበራት አሏቸው ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ የ59 ዓመታት ዕድሜ ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ተጠቃሽ ነው፡፡ ከ17 ሺሕ በላይ ሠራተኞች ያሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የሠራተኞች ማኅበር፣ የሠራተኞችን መብትና ጥቅም ከማስጠበቅ ባሻገር፣ የሠራተኞች መሠረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት በሚያደርገው ጥረት ይታወቃል፡፡ ይህ ጥረት ከአየር መንገዱ ማኔጅመንት ጋር በመተባበርም ጭምር ሲሆን፣ በተናጠልም ሲከናወን እንደነበር በተለያዩ መንገዶች ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

ከዚህ ቀደም ሠራተኞች የቤትና የተሽከርካሪ ባለቤት እንዲሆኑ ስምምነቶች የተደረጉ ቢሆንም፣ የካቲት 2 ቀን 2013 ዓ.ም. አብዛኛውን ሠራተኛ ተጠቃሚ ያደርጋል የተባለውና በአነስተኛ ወለድ የቤትና መኪና መግዣ ብድር ለማግኘት የሚያስችለው ስምምነት የአየር መንገዱ የሠራተኛ ማኅበር ከኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ማኅበር ባንክ ጋር ተፈራርሟል፡፡

በፊርማው ሥርዓት ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም እንደገለጹት፣ አየር መንገዱ አቅሙ በፈቀደ መጠን ለሠራተኞቹ ትኩረት ሰጥቶ የተለያየ ጥቅማ ጥቅሞችን ይሰጣል፡፡ አሁንም ዕቅድ ይዞ እየሠራ ነው፡፡

የሠራተኛው ቁጥር እያደገ ሲሄድ የሠራተኛው ትራንስፖርት ተግዳሮት ሆኖብናል፡፡ በጣም ብዙ አውቶብሶችና መኪኖች አሉ፡፡ ምናልባትም ከአንበሳ አውቶብስ ቀጥሎ ሁለተኛው አየር መንገድ ነው፡፡ ይህንንም እያሰፋ ነው፡፡ እስከ ከስምንት መቶ ሰዎች የሚያስተናግዱ ካፍቴሪዎች አሉ፡፡ የሚዲካል ኢንሹራንስና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች እንዳሉ ሆነው ሌሎች ሥራዎችም ስለመሠራታቸው ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ ቀደም ብሎ በተጠና ጥናት መሠረት ቁልፍ ችግሮች ሆነው የተገኙ የመኖሪያ ቤትና መጓጓዣ በመሆኑ፣ ቤት መሥራት አለብን ብለን ዕቅድ ይዘን በመጀመርያው ምዕራፍ 1,200 ቤቶች ሠርተው ማስረከባቸውንም አስታውሰዋል፡፡

የሁለተኛው ምዕራፍ ከታሰበው በላይ ቢዘገይም ወደ 11 ሺሕ የሚሆን አፓርትመንትና ሁሉንም ሠራተኞች ሊባል በሚችል ደረጃ ልናደርስበት የሚያስችል ፕሮጀክቶች አሁንም በሥራ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ይህንን ከግብ ለማድረስ ጥረት እንደሚቀጥል አመልክተው፣ ወደፊት ሠራተኞችን የሚደግፉ ሥራዎች እንደሚቀጥሉም ካደረጉት ገለጻ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

በዕለቱ ከኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ጋር የተደረሰው ስምምነትም የዚሁ አካል መሆኑን በማኅበሩ ብርቱ ጥረት ለመኪና፣ ለቤት፣ ለመግዛት የሚያስችል የብድር ስምምነት ተደርጎ ወደ ተግባር እንዲገባ የሚያስችል ነው፡፡

ወጣቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የሠራተኞች ማኅበር ሊቀመንበር ኢንጂነር ተሊላ ደሬሳ እንዳመለከቱትም፣ ማኅበሩ የሠራተኛውን ጥቅም ለማስጠበቅና ሊያገኝ የሚገባውን ጥቅም እንዲያገኝ የተለያዩ ጥረቶች ሲደርግ መቆየቱን፣ ከአንድ ዓመት በፊት የመጀመርያውን የቤትና የመኪና ግዥ ብድር ስምምነት የተደረገው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ነበር፡፡ ይህ ስምምነት አሁንም አለ፡፡ በዚህ ስምምነት ሠራተኞች ቤትና መኪና እየገዙ ይገኛል፡፡ ወደፊትም የሚቀጥል ይሆናል፡፡

ነገር ግን ሠራተኛ ማኅበሩ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የተደረገው ስምምነት ጥሩ ቢሆንም፣ ይህ ስምምነት የሚጠቅመው ግን ከፍተኛ ደመወዝ ያላቸውን ሠራተኞችን ነው በሚል ከሠራተኞች ይቀርብ የነበረ አቤቱታም ሌሎች አማራጮችን ለመመልከት እንዳስገደደው ኢንጂነር ተሊላ ተናግረዋል፡፡ እንደ ሠራተኛ ማኅበር ቢያንስ ሠራተኞችን ‹‹50 +1 = ማስደሰት አለብን ብለን ነው የምናምነው፤›› ያሉት ኢንጂነሩ፣ ከኢትዮጰያ ንግድ ባንክ ጋር በተደረገው ስምምነት ሲታይ ሠራተኞቻችን 50 + 1 ባለመድረሱ በአሁኑ ወቅት መሠረታዊ የሆነውን የተሽከርካሪ አቅርቦት እያገኙ እንደ ሠራተኛ ማኅበር ሠራተኞች ታክሲ ላይ መጋፋት እንደሌለባቸው ታምኖ ይህንን ለማሟላት የቻልነውን ነገር ሁሉ ስናደርግ ነበር ያሉት ኢንጂነር ተሊላ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የተደረገው ስምምነት አብዛኛውን ሠራተኛ ሊደርስ አልቻለም፡፡ ወለዱም ከፍተኛ ነው ተብሎ ቅሬታ ሲቀርብ ነበረውን የሠራተኛ ጥያቄ ይዞ ከአየር መንገዱ ማኔጅመንት ጋር በመነጋገር የተሻለ ስምምነት ከወጣ ለመፍቀድ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በተለይ አቶ ተወልደ በዚህ ሐሳብ ተስማምተው የሚመጣውን ስምምነት ለመፈረም ቃል ገቡ፡፡

አገልግሎት ለማቅረብ ለባንኮች በቀረበ ጥሪ መሠረት ኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ለአየር መንገዱ ሠራተኞች ከሰባት በመቶ ጀምሮ የብድር ወለድ ምጣኔ ብድር አቀርባለሁ ብሎ በመቅረቡ የዛሬው የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ሊፈጸም ችሏል፡፡

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የሠራተኞች ማኅበርና በኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ መካከል የተደረሰውን ስምምነትና ይህንን ስምምነት በተመለከተ ከአንድ ዓመት በላይ ሲካሄድ የነበረውን ድርድርና ውጤት አስመልክቶ የማኅበሩ ሊቀመንበር ኢንጂነር ተሊላ እንዳመለከቱትም፣ ሠራተኞች የተሻለ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ዕድል ለማመቻቸት 18ቱንም የአገሪቱን ባንኮች ማንኳኳታቸውን ነው፡፡

ይህ ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የነበረውን የሠራተኞች የብድር ስምምነት እንዲሻሻል ጭምር ጥያቄ እስከማቅረብ ደርሰው እንደነበርም አመልክተዋል፡፡ እንዲያውም ከሌላ ባንኮች ጋር ከመነጋገራችን በፊት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስምምነቱን እንዲያሻሽል በርካታ ሐሳቦችን ማቅረባቸውን ሁሉ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ይህ የማኅበሩ ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ ቆይቷል፡፡

በዚህም ምክንያት ስምምነቱ ማሻሻያ እንዲደረግበት የቀረበውን ጥያቄ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በኩል እንዲቀርብ ከተደረገ በኋላ ግን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰጠው ምላሽ ሌላ አማራጭ የሌለ መሆኑንና በነበረው ስምምነት መሠረት ይቀጥል የሚል ነበር፡፡ በወቅቱ በአቶ ባጫ ጊና የሚመራው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስምምነቱን ማሻሻል እንደማይችሉ ነገሩን፡፡

ይሁንና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አብዛኛውን ሠራተኛ በተሻለ የብድር ወለድ ምጣኔ ለቤትና ለመኪና ግዥ የሚሆን ብድር እንዲቀርብለት ለማድረግ የቀረበው ማሻሻያ ባለመሳካቱ ሌሎች አማራጮችን ለመፈለግ ለ18ቱም ባንኮች ጥያቄ ቀርቦ በደብዳቤ ተጠየቁ፣ አንዳንዶቹ ደብዳቤው እንደደረሳቸው እንኳን ምላሽ ያልሰጡ ነበሩ፡፡ አንዳንዶቹ ባንኮች ደግሞ የሰጡን ዕድል በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ሊሆን የማይችል ነበር፡፡ ከዚሁ ለባንክ ላቀረብነው ጥያቄ ትክክለኛ ምላሽ የሰጡት የአብዛኛውን ሠራተኛ ፍላጎት የሚሞላ ሰነድ በማቅረብ ብቸኛው ባንክ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ በመሆኑ በዚሁ መሠረት አብዛኛውን ሠራተኛ ሊጠቅም የሚችለውን ስምምነት ለመፈራረም ተችሏል ተብሏል፡፡

አቶ ተወልደም የኢሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ይህንን ዕድል ሲሰጠን ከሌሎች የተሻለ ወለድና አገልግሎት በማቅረቡ ነው ብለዋል፡፡ በዕለቱ የተፈረመውን ስምምነት አስፈላጊነትና ተገቢነት በተለያየ መንገድ አቶ ተወልደና ኢንጂነር ተሊላ የገለጹ ሲሆን፣ በዚህ ዕድል እንዲጠቀሙ ሁሉንም ባንኮች በመጋበዝ የተሻለ አገልግሎት ለማግኘት  ‹‹ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአገራችን አልፎ የአፍሪካ ኩራት ከሆነው አየር መንገድ ሠራተኞች ጋር ባንካቸው በጋራ ለመሥራት ያደረገው ስምምነት ትልቅ ትርጉም አለው ያሉት የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ድርቤ አስፋው እንደ ቤተሰብ ሆነን አብረን እንሠራለን ብለዋል፡፡

አያይዘውም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የባንክ አገልግሎት ሲታይ በጣም ጥቂት ቁጥር ያላቸው ሰዎች ብድር የሚያገኙበትና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ገንዘብ የሚቆጥቡበት የባንክ ሥርዓት ነው ያለው፡፡ አብዛኛው ብድር የማይገኝበት ስለሆነ የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ የመጣው ከደሃው አርሶ አደር በመሆኑ ሠራተኞችን ልብና ስሜት ቀረብ ብለን በመወያየታችን የዚህ ውድድር አሸናፊ መሆን ችለናልም ብለዋል፡፡

በትናንቱ ስምምነት ላይ ሌላው ጎልቶ የታየው እውነታ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማኔጅመንት ከሠራተኛ ማኅበሩ ጋር ያለው ግንኙነት በመደገፍ ላይ የተመሠረተ መሆኑ ነው፡፡

በተለይ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ያበረከቱት አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን በማኅበሩ ሊቀመንበር ተደጋግሞ መገለጹ ነው፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚውን በተመለከተ ኢንጂነር ተሊላ፣ ‹‹እኔ አልዋሽም፡፡ መናገር ያለብኝን በቀጥታ እናገራለሁ፡፡ ይህ ተፈጥሮዬ ነው፡፡ አንድ አባባል ልጥቀስ ‹ነብይ በአገሩ አይከበርም ይባላል› ብለው፣ አቶ ተወልደ በአገሩ ያልተከበረ ነብይ ነው በማለት እንደ ሥራቸውና አስተዋጽኦቸው እንዳልተከበሩ፣ ነገር ግን ሊከበሩ የሚገባ ጠንካራ ሰው መሆናቸውን የተለያየ ምሳሌዎችን ጠቅሰው አቶ ተወልደን አወድሰዋል፡፡ ዕንቁ ኢትዮጵያዊም ብለዋቸዋል፡፡ በዕለቱ ከኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ጋር ለተደረገው ስምምነት የእርሳቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ከእርሳቸው ብዙ የተማሩ ስለመሆኑ የጠቀሱት የማኅበሩ ሊቀመንበር የሠራተኛው መሪ ሆነው ከተሰየሙ ጊዜ አንስቶ ለሠራተኛው ይኼ ይሁን ብዬ ጠይቄ አቶ ተወልደ አንዳችም ዕንቢ ያሉት ነገር የለም በማለትም ገልጸዋቸዋል፡፡  

በትናንትናው ዕለት ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች የቤትና የመኪና መግዣ ብድር ለማቅረብ ስምምነት የደረሰው የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ከ65 በመቶ በላይ የሚሆኑ ገበሬዎች ባለአክሲዮን የሆኑበት ባንክ ነው፡፡

ባንኩን የሚለይ በመሆኑ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞችና የባንኩ ባለአክሲዮኖች የሆኑት አርሶ አደሮች በጋራ የሚጠቃቀሙበት ይሆናልም ተብሏል፡፡

ከባንኩ ጋር በሌሎች ሥራዎች ላይም እየሠራን ነው ያሉት አቶ ተወልደ፣ በተለይ ከኬተሪንግ ጋር ተያይዞ አርሶ አደሩን በሚጠቅሙ ሥራዎች በጋራ የሚሠሩ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡ የዕለቱን ስምምነት በተለየ የገለጹት ደግሞ ኢንጂነር ተሊላ ናቸው፡፡ ኢንጂነር ተሊላ በተለየ የገለጹት፣ የዛሬ 75 ዓመት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሥራ ሲገባ ‹‹የአየር መንገዳችንን 75ኛ ዓመት ለማክበር ሽር ጉድ እያልን ነው፡፡ ከ75 ዓመት በፊት እዚህ ቦታ ምን ነበር ብዬ ሳስብ አቶ ሾቡ ኢጀርሳና አቶ ሶራ ቡኔ የሚባሉ ገበሬዎች ነበሩ፡፡

ይኼ አየር መንገድ ሲቋቋም እነዚህም ሰዎች ለእኛው አገር ነው ብለው ቦታቸውን ለቀው ነው የሄዱት፡፡ ከዚያም አየር መንገዱ እዚህ ቦታ ላይ ከተቋቋመ 75 ዓመት በኋላ እነዚህ ገበሬዎች አልተውንም፡፡ አሁን ደግሞ ተደራጅተው መጥተው መኪናና ቤት ካልገዛንላችሁ አሉን፡፡ ስለዚሀ የዛሬ 75 ዓመት ሁለቱ ገበሬዎች በሕይወት የሉም፡፡ ዛሬ በሕይወት ያለ ገበሬ ሆኖ የመጣው ደግሞ አቶ ድርቤ አስፋው ነው በማለት የዕለቱን ስምምነት ገልጸውታል፡፡

የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ በአሁኑ ወቅት በኢንዱትሪው ውስጥ ካሉ 16 የግል ባንኮች አንዱ ሲሆን፣ በ2012 የሒሳብ ዓመት 1.6 ቢሊዮን ብር በማትረፍ ከግል ባንኮች ሦስኛውን ትልቁን ትርፍ ያስመዘገበ ባንክ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሠራተኞች ማኅበር በአየር መንገዱ ውስጥ ሁለተኛው ማኅበር ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች