መንግሥት የትግራይ ክልልን ሲመራ የነበረው የሕወሓት ኃይል በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ሰንዝሯል በማለት፣ የሕግ ማስከበር ዘመቻ ከጀመረ ሦስት ወራት አልፈው አራተኛው ወር ተጀምሯል፡፡
በዚህም መሠረት ከጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከወጣ በኋላ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይ መቋቋሙ የሚታወስ ነው፡፡
በእነዚህ ጥቂት ወራት ውስጥ መንግሥት በክልሉ እያደረገ ያለውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ በተመለከተ የሚያወጣቸው መረጃዎች ሲፈልግ በመንግሥት ሚዲያዎች በኩል፣ ካልሆነ ደግሞ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይ በኩል እንጂ የአገር ውስጥም ሆነ የዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በቦታው በመገኘት እንደ መንግሥት ሚዲዎች ሁሉ አስፈላጊው ከለላ ተደርጎላቸው በክልሉ ያሉ አጠቃላይ ሁኔታዎቸን በቅጡ ሲዘግቡ አይስተዋልም፡፡
እንዲህ ዓይነቱ ወጥነት የሌለው የተስተካከለ የመረጃ አሰጣጥ ባልተዘረጋበትና ግልጽነት በማይታይበት አካሄድ ደግሞ የመረጃ ክፍተቶች፣ ግድፈቶችና አንዱ ከአንዱ የሚጋጩ መረጃዎች በተደጋጋሚ ይሰማሉ፡፡
ለአብነትም ያህል በኅዳር ወር መጨረሻ አካባቢ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ለጋዜጠኞች በመጀመርያ ዙር አካሄድኩት ባለው የመስክ ምልከታ መሠረት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በሕወሓት ኃይሎች ከትግራይ ክልል ወደ አማራ ክልል በሚገኙ የጎንደርና የባህር ዳር የአውሮፕላን ማረፊዎች ዒላማ አድርገው የተተኮሱ ሮኬቶች በኤርፖርቶቹ ላይ እዚህ ግባ የሚባል አደጋ እንዳላደረሱ ተናግሮ ነበር፡፡
በተመሳሳይ ጥር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና ፌዴራል ፖሊስ በትግራይ ክልል በተደረገው የሕግ ማስከበር ዘመቻ አደረግነው ያሉትን የመጀመርያ ዙር የምርመራ ሪፖርት ይፋ አድርገዋል፡፡
ሪፖርቱን ለጋዜጠኞች ያቀረቡት የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ዘለዓለም መንግሥቴ፣ ከትግራይ ክልል በቀጥታ በተተኮሱት ሮኬቶች ምክንያት የባህር ዳርና የጎንደር አውሮፕላን ማረፊያዎች ከጥቅም ውጪ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል በማይካድራ ከተማ በተደረገው ጭፍጨፋ ሕይወታቸውን ያጡ የንፁኃን ዜጎች ቁጥር የአስቸኳይ ጊዜ መርማሪ ቦርዱ በመጀመርያ ዙር አካሄድኩት ባለው ምርመራ መሠረት፣ ወደ 700 የሚጠጉ ዜጎች እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡
ከዚሁ ጉዳይ ሳይወጣ ምክትል ኮሚሽነር ዘለዓለም ስለተገደሉት ሰዎች ሲናገሩ የተገለጸው ቁጥር የተጋነነ እንጂ፣ እንደተባለው የበዛ ቁጥር እንዳልሆነና በቅርቡም ሙሉ ጥናቱን አጠናቆ መረጃውን እንደሚያቀርብ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከማይካድራ ጭፍጨፋ ጋር በተገናኘ አጠናቀርኩት ያለው የምርመራ ሪፖርት ደግሞ፣ በቦታው በቀን ሠራተኝነት ሲሠሩ የነበሩ ወደ 600 ዜጎች ተገድለዋል ይላል፡፡
እንግዲህ ለአብነት ይህ ይበል እንጂ በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡ መረጃዎች አሁንም ትክክለኛነታቸው አጠራጣሪ የቀጠለ ሲሆን፣ አስተማማኝ ቁጥሮች ማግኘት አልተቻለም፡፡
በተያያዘ ከጥቂት ቀናት በፊት በትግራይ ክልል መቀመጫቸውን ያደረጉ ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሳልሳዊ ወያኔ፣ ብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ ባይቶናና ውድብ ናፅናት ትግራይ የተባሉ ፓርቲዎች በክልሉ ያለውን ጉዳይ አስመልክተው የጋራ መግለጫ አውጥተዋል፡፡
በመግለጫቸው በተለይም በትግራይ ክልል ከ50 ሺሕ በላይ ንፁኃን ዜጎች እንደተጨፈጨፉ፣ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ደግሞ እንደተፈናቀሉ፣ ከ4.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው፣ ከ150 ሺሕ በላይ ዜጎች ከአገር እንደተሰደዱና ከ4.8 ሚሊዮን በላይ የቁም እንስሳት ተነድተው እንደጠፉ ይፋ አድርገዋል፡፡
ይህንን መረጃ ትልልቅ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ጭምር በፊት ገጾቻቸው ሲዘግቡት የሰነበቱ ሲሆን፣ ሪፖርተር ፓርቲዎቹ ያወጡትንና በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻቸው የለቀቁትን መግለጫ እንዴት እንዳጠናቀሩት፣ በምንና ከየት እንዳገኙት ለማጣራት የሦስቱንም ፓርቲዎች ተወካዮች ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ መርማሪ ቦርድ ሰብሳቢና የሕዝበ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ለማ ተሰማ ስለጉዳዩ መረጃ ሪፖርተር ጠይቋቸው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የሚባለውን ነገር ሁሉ ሄደን የምናረጋግጠው እንጂ፣ ከወሬ ያለፈ ትክክለኛ ነው ብለን የምንወስደው ነገር የለም ሲሉ፤›› ተናግረዋል፡፡
ከሁለት ወራት በፊት ሪፖርቱን ያቀረበው መርማሪ ቦርዱ ለሦስተኛ ዙር ምልከታ ወደ ቦታው ለመሄድ ዝግጅት ላይ እንደሆነ የተናገሩት አቶ ለማ፣ ከሚነሱት ችግሮች አንፃር ጊዜው አልረዘመም ወይ? እስካሁን መሄድ አልነበረባችሁም ወይ ለተባሉት ሲመልሱ ማንኛውም አካል በክልሉ አሉ ለሚባሉ ጉዳዮች ለመርማሪ ቦርዱ ጥያቄ ቢኖረው በስልክ፣ በአካልና በኢሜይል መጠየቅ የሚችልበት መንገድና አሠራር አለ ብለዋል፡፡
‹‹በውጭ እንደሚወራው ሁሉ ዕርዳታ ለማቅረብ ተከለከልኩ፣ በክልሉ ረሃብ ተከስቷል ወይም ተራብኩ የሚል አካል ሲናገር አልሰማንም፣ ነገር ግን መንግሥት አቅሙ በፈቀደ መጠን ማድረግ ያለበትን እያደረገ ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
‹‹ዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ዕርዳታ ለማቅረብ መሄድ አልቻልንም የሚለውን እየሰማሁ ያለው ገና ካንተ ነው፡፡ እኔ የደረሰኝ ነገር የለም፡፡ ዕርዳታ ለማድረስ መንገዱ ክፍት ነው፡፡ ምንም የሚከለክል ነገር የለም፤›› ብለዋል፡፡
ስለዚህ መሄድ አልቻልንም ማለት ለማስፈጸም የሚፈለጉት ሌላ ዓላማ ከሌላቸው በስተቀር ለሕዝቡ ዕርዳታ ለማድረስ የሚፈልጉ አካላት ካሉ፣ ‹‹ዛሬውኑ መሄድ ይችላሉ፣ እኛም መርዳት እንችላለን፤›› ብለዋል አቶ ለማ፡፡
የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ በትግራይ ክልል ስላለው የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ሲገልጹ፣ በክልሉ በመጀመርያው ዙር በተካሄደው አሰሳ ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ድጋፍ ፈላጊዎች አሉ ብለዋል፡፡ በቀጣይ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች ለመለየት ሥራ መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የአስአኳይ ጊዜ ድጋፍ የሚያቀርቡ ከ26 በላይ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዳሉ፣ እንዲሁም በመንግሥት አማካይነት ድጋፍ እየተደረገ እንደሆነና ምግብ ነክ የሆነ አቅርቦት ችግር እንደሌለ ገልጸው፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች ላይ ግን አሁንም በቂ አቅርቦት አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡
ሰኞ የካቲት 1 ቀን 2013 ዓ.ም. የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ወይዘሮ እቴነሽ ንጉሤን፣ በክልሉ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ሪፖርተር ደውሎ አነጋግሯቸዋል፡፡
ኃላፊዋ በክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ፈላጊዎች ቁጥር ከ4.5 ሚሊዮን በላይ እንደሆነ፣ አሁን እየተደረገ ያለው የአቅርቦት ሁኔታ ደግሞ ፍትሐዊነት የጎደለው ነው ብለዋል፡፡ ‹‹የተመዘገበው ሕዝብ ምንም ሊረካ ባለመቻሉ በየቀኑ አልደረሰንም የሚል አቤቱታ እየደረሰን ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ከአገር ሽማግሌዎች ጋር ውይይት ስላደረጉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ኃላፊዋ ሲናገሩ፣ ነዋሪዎቹ የዕርዳታው ጉዳይ በትክክል እንዲዳረስና የወደሙ መሥሪያ ቤቶች ተመልሰው ወደ ሥራ እንዲገቡ መጠየቃቸውን ጠቁመዋል፡፡
ሌላውና በተደጋጋሚ ከተለያዩ አካላት እየተነሳ ያለው ነገር ግን ከመንግሥት በኩል እምብዛም በግልጽ መልስ ሲሰጥበት የማይስተዋለው ጉዳይ፣ በትግራይ ክልል የኤርትራ ወታደሮች በክልሉ በተደረገው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ተሳትፈዋል መባሉ ሲሆን፣ አሁንም ድንበር ጥሰው በትግራይ ክልል አካባቢ መንቀሳቀሳቸው እየተነገረ መሆኑ ነው፡፡
የጊዜያዊ አስተዳደሩ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ የኤርትራ ወታደሮች ወደ ትግራይ ክልል መግባትን አስመልክቶ ባለፈው እሑድ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ከአገር ሽማግሌዎች ጋር በነበራቸው ውይይት በተደጋጋሚ የተነሳ ጉዳይ እንደነበር አውስተዋል፡፡
በተለይም በደቡባዊ የትግራይ ዞኖች ከአማራ ክልል፣ በምዕራብ ዞኖች በኩል የኤርትራ ወታደሮች ድንበር ጥሰው መግባታቸውን፣ መሬት መወረሩንና ከዚያም አልፎ ሕዝቡ እየተገደለና እየተዘረፈ መሆኑን የአገር ሽማገሌዎች በተደጋጋሚ እንዳነሱና ፕሬዚዳንቷ ጉዳዩን ለሚመለከተው አካል አቀርባለሁ ማለታቸውን ኃላፊዋ አክለው ገልጸዋል፡፡
የዓለም የምግብ ድርጅት ከሦስት ቀናት በፊት በድረ ገጹ ያሰፈረው መረጃ እንደሚያሳየው፣ በትግራይ እስከ ሦሰት ሚሊዮን ዜጎች የዕለት ደራሽ ምግብ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፣ አሁንም የዕለት ደራሽ ምግብ በአፋጣኝ ሊቀርብ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
በተመሳሳይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአስቸኳይ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ከሰሞኑ ያወጣው ሪፖርት ደግሞ፣ በትግራይ አልፎ አልፎ በተለያዩ አካቢዎች በሚታየው የፀጥታ ችግር ምክንያት የተበጣጠሰ የዕርዳታ አቅርቦት መኖሩ የዕለት ደራሽ ምግብ አቅርቦቱ የበለጠ አስፈላጊ መሆኑን ማሳያ ነው ይላል፡፡
በተጨማሪም ከድጋፍ አቅርቦቱ ውስንነት በተጨማሪ የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ አቅርቦት ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች በክልሉ በተለይ በገጠራማው አካባቢ ያሉ ነዋሪዎችን ተደራሽ ማድረግ አለመቻሉን፣ ወሳኝ የሆኑ የዕለት ደራሽ ምግቦችን ለማድረስ እየታየ ያለው ችግር አሳሳቢና በተለያዩ አከባቢዎችም የረሃብ መጠኑ ከፍተኛ አንደሆነ አመላክቷል፡፡
የስልክና የኤሌክትሪክ የመሳሰሉት መሠረተ ልማቶች መዘጋጋትና የሕክምና አገልገሎት አለመኖር የተበታተነ አቅርቦት ከፀጥታ ችግሩ ጋር ተዳምሮ በክልሉ ያለው የሰላም ሁኔታ የማይገመት መሆን፣ የመጠለያና የምግብ አቅርቦት አለመኖር፣ ዝርፊያ፣ በንፁኃን ዜጎች ላይ የሚደረግ ጥቃት፣ ፆታዊ ጥቃት፣ የነዋሪዎች በግዴታ ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ መደረግ በክልሉ ትልቅ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡
ከቀናት በፊት ከዓለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቤስሊ ጋር በመቀሌ ጉብኝት ያደረጉት የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪት ካሚል፣ በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለውን የሰብዓዊ ድጋፍ ክምችት ሥርጭት አስመልክተው በቀጣይ ሁለት ወራት 2.5 ሚሊዮን ለሚሆኑ የተቸገሩ ወገኖችን መደገፍ የሚያስችል ክምችት በመጋዘኖቹ እንዳለ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አሥፍረዋል፡፡
በክልሉ የአስቸኳይ ድጋፍ አቅርቦት ይፈልጋል ከተበሉት 2.5 ሚሊዮን ዜጎች ውስጥ፣ እስካሁን መድረስ የተቻለው ሁለት ሚለዮን ለሚሆኑ ዜጎች ብቻ እንደሆነ የገለጹት ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ናቸው፡፡
አቶ ምትኩ በክልሉ በአቅርቦት ረገድ መንግሥት 70 በመቶውን፣ 30 በመቶው ከተለያዩ ዕርዳታ ምንጮች የሚሸፈን እንደሆነ፣ በርካታ ድርጅቶችም ወደ ክልሉ እየገቡ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን ከ60 በላይ የሚሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ሠራተኞች ወደ ክልሉ ለመግባት የኢትዮጵያን መንግሥትን ፈቃድ እየተጠባበቁ መሆኑን፣ የተባበሩት መንግሥታ ድርጅት ከቀናት በፊት በድረ ገጹ አስታውቋል፡፡
የድርጅቱን ቃል አቀባይ ዋቢ አድርጎ የወጣው መረጃ ለሦስት ወራት የቀጠለው ግጭት አሳሳቢ እንደሆነና የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ፍላጎት መጨመር የሚያስፈራ መሆኑን በመጠቆም፣ የዕለት ደራሽ ምግቦችን ለማድረስ መንግሥት ኮሪደሮችን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ክፍት እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡