የዓድዋ ድል ወሩን ሙሉ ይከበራል
‹‹ቀደም ሲልም ሆነ በአሁኑ ጊዜ ያለው ሥርዓተ ትምህርት በውጭ ተፅዕኖ የወደቀ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት የሥርዓተ ትምህርት አካሄድ ታሪካችንን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነታችንንም ብንረሳ ምንም ሊፈረድብን አይገባም፤›› ሲል የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር አስታወቀ፡፡
የዓድዋን 125ኛ የድል በዓል ምክንያት በማድረግ ‹‹የዓድዋ ድል ተምሳሌትነት›› በሚል ርዕስ እና ‹‹ቱባ ወግ›› በሚል ስያሜ የካቲት 3 ቀን 2013 ዓ.ም. በተካሄደው ውይይት ላይ ሚኒስትሯ ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ባለፈውም ሆነ አሁን ባለው ትምህርት ላይ አማርኛን ጨምሮ ሌሎቹም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በውጭ ሥርዓተ ትምህርት ቀራጮች የተሠሩ ናቸው፡፡
‹‹እኔ በማስተምርበት የትምህርት ዘርፍ የውጭ ሥርዓተ ትምህርት ቀራጭ ሊያስፈልገን አይገባም ነበር፡፡ በተለይ መርሐ ትምህርቱ (ሲለብስ) ሲዘጋጅ እኔም ስለነበርኩ እጅግ በጣም የሚያሳፍር ነገሮች አይቻለሁ፡፡ ይኸውም በእንግሊዝኛ የተዘጋጀ ሲለብሰ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ እንዲሠራበት ተደርጓል፤›› ብለዋል፡፡
የጋራ ታሪካችን ባህላችንና አገር በቀሉ ዕውቀታችንን፣ እንዲሁም ትውልድን ከትውልድ፣ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያገናኝ፣ የሚያሰባስብ፣ የሚያስተሳስር፣ ብሎም ለዕድገት፣ ለልማት ለሰላም፣ ለተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችና ምርምር መሠረት ወይም ድንጋይ ሆኖ እንደሚያገለግል ነው ሚኒስትሯ የተናገሩት፡፡
ነገር ግን ሥርዓተ ትምህርቱ በውጭ ተፅዕኖ የሚወድቅ ከሆነ ድልድዩ ይፈርስና በምትኩ ድልድይ የማይሆኑ ነገሮች ሊሠሩ እንደሚችሉ፣ የዚህ ውጤት ደግሞ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ከማምጣት ይልቅ መጠላላትን፣ መራራቅንና መልካም ያልሆኑ ዕሴቶች የሚፈጠሩበት ሊሆኑ እንደሚችሉ ከገለጻቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡
እንደ ሒሩት ካሰው (ዶ/ር) ማብራሪያ ትውልድ የሚገነባው ወይም የሚቀረፀው መጀመርያ በቤተሰብ፣ ቀጥሎ በትምህርት ቤት፣ ከዛም በሃይማኖት ተቋማት ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ትውልድ ከሁሉም በላይ የሚገነባው በትምህርት ቤት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የዓድዋ ድል ታሪክ በኮርስ ደረጃ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ በቀሩት ትምህርት ቤቶች ደግሞ በታሪክ ትምህርት ዘርፍ መሰጠት ይኖርበታል፡፡
የዓድዋ ድል በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ብሎም የጥቁር ሕዝቦችን የይቻላል መንፈስ፣ ሥነ ልቦና፣ የአንድነትን፣ የፍትሕን፣ በአጠቃላይ የሰው ልጅ ጥቁርም ይሁን ነጭ በውስጡ ባለው ደም እኩል ለመሆኑ ማሳያ ነው፤›› ብለዋል፡፡
በዚህም የተነሳ 125ኛውን የዓድዋ ድል በዓል ለየት ባለ መልኩ ለማክበር የሚያስችል ፕሮግራም ተቀርጾ ለተግባራዊነቱ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ እስካሁንም በተካሄደው እንቅስቃሴ በፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የሚመራ ሚኒስትሮች፣ ታላላቅ ምሁራን፣ ታዋቂ ሰዎችና የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አመራሮች በአባልነት የተሳተፉበት የበዓል አዘጋጅ ምክር ቤት መቋቋሙን አስረድተዋል፡፡
ከዚህም ሌላ 125ኛው የዓድዋ ድል በዓል በየካቲት ወሩን ሙሉ እየታሰበ እንደሚውልና በእነዚህም ቀናት ውስጥ የዓድዋን ድል የሚያንፀባርቁ ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች በየተራ ለሕዝብ እንደሚቀርብ፣ ከዚህም ሌላ ዋናው በዓል የካቲት 23 ቀን እንደሚከበር፣ ይህም እንደ ከዚህ በፊቱ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ እንዲሁም የአገር ውስጥና የውጭ አገር ታላላቅ ሰዎች በተገኙበት በመላው የአገሪቱ ክፍሎች እጅግ በደመቀ ሁኔታ ለማክበር የሚያስችሉ ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑ ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡
ሥርዓተ ትምህርቱም ይህን አካሄድ ተቀብሎ ለኢትዮጵያውያን ብሎም ለአፍሪካና ለቀሩትም ጥቁር ሕዝቦች የሚያስተምር፣ መመኪያና መኩሪያ የሆነውን የዓድዋ ድል በዓል ታሪክ ከማካተት አልፎ በኮሌጅ ደረጃ እንደ አንድ ኮርስ ሆኖ እንዲሰጥ መደረግ እንዳለበት ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አውሮፓውያን አፍሪካን ለመቀራመት የቻሉት ኋላቀርነትን ብቻ ሳይሆን የአንድነት አለመኖርን፣ የተበታተነ ሁኔታ መኖሩን መሠረት አድርገው ሲሆን ይህ ግን ኢትዮጵያ ላይ እንዳልተሠራ ተናግረዋል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት የብዝኃ ብሔርና የብዙ ባህል ባለቤት መሆኗ ለአሸናፊነት እንዳበቃት፣ ይህም ሕዝቡን በአንድነት የሚያስተሳስር ብቻ ሳይሆን ብልኃትን እንደሚያመነጭና ለአሸናፊነትም እንደሚያበቃ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
‹‹እንደ እኔ እምነት ዓድዋን የተዋጋው አንድ ብሔረሰብ ቢሆን ኖሮ አናሸንፍም ነበር፡፡ ያሸነፍነው የብዝኃ ባህል ባለቤትና ሕብረ ብሔራዊ ስለሆን ነው፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዱ ብሔረሰብ የተለያየ ባህል አለው፡፡ የተለያየ ባህል ደግሞ የተለያየ ብልሃት፣ የጦር ወይም የውጊያ ስልት በማምጣት እንድናሸንፍ አድርጎናል፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
በካፒታል ሆቴል የስብሰባ አዳራሽ በተከናወነ በዚሁ የውይይት መድረክ ላይ፣ አራት ምሁራን በዓድዋ ድል ታሪክ ላይ ያጠነጠኑ የመነሻ ሐሳቦችን አቅርበዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪ አህመድ ሁሴን (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ሕዝብ በዓድዋ ላይ የተቀዳጀው ከፍተኛ ድል የአፍሪካና የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ድል መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
ወራሪውን የጣሊያን ሠራዊት ለመመከት ወደ ጦርነቱ የተመመውም ሕዝብ የብሔር፣ ብሔረሰቦች ተዋጽኦ እንዳለው፣ ቅጣት አለብህ በመባሉ የተነሳና የተመመ ሳይሆን በአንድ ወኔና በአንድ ሐሳብ ታሪክ ለመሥራት የተሰበሰበ እንደነበር፣ በዚህም ወደ 50,000 ሴቶችና በብዙ መቶ የሚቆጠሩ መነኮሳት ዘምተው እንደነበር፣ ከእነዚህም መካከል ሴቶቹ ስንቅ በማዘጋጀት፣ መነኮሳቱ ደግሞ ወደ ውጊያው የሚገባውን በማናዘዝ፣ የደከመውን በማበረታታት፣ ቸል ያለውን በመገዘት የሞቱትን በመገነዝና በመቅበር ላቅ ያለ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ነው የታሪክ ተመራማሪው የተናገሩት፡፡
‹‹ከዓድዋ ድል ታሪክ ላቲን አሜሪካውያን፣ አውሮፓውያንና አፍሪካውያን ተጠቅመውበታል፡፡ ካሜሩን ያውንዴ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ካሪኩለም ተቀርፆለትና መምህራንም ሲያስተምር አይቻለሁ፤›› ብለዋል፡፡
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተርና የታሪክ ተመራማሪ አበባው አያሌው (ረዳት ፕሮፌሰር) ማብራሪያ፣ ‹‹አፄ ምኒልክ የውጫሌን ውል ሰርዤዋለሁ፡፡ እንደሌለም ቆጥሬዋለሁ፤›› ካሉ በኋላ ጣሊያኖች አንድ መላ ይዘው ብቅ አሉ፡፡ መላውም ኢትዮጵያን ማሸነፊያ መንገድ ከጦር ኃይል በተጨማሪ በአፄ ምኒልክ ላይ ቁርሾ ያላቸውን መሳፍንት ወደ እነሱ ማዞር ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ እነ ራስ መንገሻንና ሌሎችንም መሳፍንትን ለማማለል ሞክረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡
ጣሊያን በዓድዋ ድል በመመታቷ የገጠማትን ሽንፈት ለመበቀል ከ40 ዓመት በኋላ አየር ኃይሏን ጭምር አደራጅታ ኢትዮጵያን ለመውረር ስትመጣ የኢትዮጵያ ጦር የጠበቃት ግን ያንን ምንሽርና ዝናሩን በመያዝ ነው፡፡ የጦር ትምህርት ቤት ለመክፈት ጥረት የተደረገው በወረራው ዋዜማ ስለነበር ሊሳካ እንዳልቻለ፣ ከወረራው በኋላ ግን ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ መጀመርያ የተንቀሳቀሱት ወታደራዊ ኃይል መገንባት እንደነበርና ይህም እንደተሳካላቸው ነው የተናገሩት፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ወታደራዊ ኃይልን መገንባት የህልውና ጉዳይ መሆኑን ገልጸው በተለይ ኢትዮጵያ ያለችበት ጂኦፖለቲካ፣ በውኃ፣ በድንበር፣ በስትራቴጂካዊ አቀማመጡ ጋር ተያይዞ የግድ ወታደራዊ አቅሟን ማበልፀግ እንደሚገባት፣ ይኼም በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ የታየው እንቅስቃሴ ጥሩ እንደነበር ከዛ ወዲህ የታየው የቁጥርና የመሣሪያ መብዛት የትም እንደማያደርስ አስረድተዋል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰሩ በመጨረሻም ‹‹አሁን በጣም የሚያሳስበኝ ወታደራዊ አቅማችን ምን ያህል ነው? የሚለው ነው፡፡ የዘመኑ ወታደር በዕውቀቱ የተራቀቀ መሆን አለበት እንጂ ስምንተኛ፣ አሥረኛና መሰናዶ ትምህርት ያቃተው ሁሉ መሰባሰቢያ መሆን የለበትም፤›› ብለዋል፡፡