Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹ገመና ከታቹ››

‹‹ገመና ከታቹ››

ቀን:

ዕድሜያቸው ወደ 40 እንደሚጠጋ ይናገራሉ፡፡ አዲስ የተገነባላቸውን መኖሪያ ቤት ግድግዳ በአንድ እጃቸው እያሻሹ አንድ እጃቸውን ደግሞ ወደ ፈጣሪያቸው ዘርግተው ‹‹አሁንማ ገመናዬ ተከተተ›› አሉ፡፡ ወ/ሮ አሰለፈች ነጋሽ ከ25 ዓመታት በላይ ያሳለፉትን አኗኗር አስታወሱ፡፡

ከአዲስ አበባ ለሥራ ወደ ሰላሌ ያቀኑት የዛሬው ባለቤታቸው አዲስ አበባ ለመምጣታቸው ምክንያት ናቸው፡፡ ወ/ሮ አሰለፈች አዲስ አበባ ቢመጡም ያረፉት የባለቤታቸው ጓደኛ ባጋሯቸው የቀበሌ ቤት ውስጥ ነበር፡፡ አራት በአራት የነበረው ቤት በመጋረጃ እኩል ተከፍሎ ኑሮ ተጀመረ፡፡

አንድ ልጅ ወልደው አልጋቸው ግርጌ እያስተኙ ኑሮን የጀመሩት ወ/ሮ አሰለፈች ሦስት ልጅ እስኪወልዱ የባለቤታቸው ጓደኛ ላጤ በመሆናቸው አልተቸገሩም ነበር፡፡ ትዳር ይዘው ልጅ ሲያፈሩ ግን የጋራ ቤታቸው ተጣበበች፡፡ ለሁለት ሰው ብቻ የነበረው የቀበሌ ቤት ከሁለቱም ወገን ቤተሰብ በመጨመሩ ዘጠኝ ሰዎችን አቅፋ ያዘች፡፡ ይህ ደግሞ ይዋደዱ የነበሩ ጓደኛሞችን አጋጨ፡፡ በውኃ ቀጠነ ሰበብ አምባጓሮ ሆነ፡፡

ወ/ሮ አሰለፈች ‹‹ጎረቤት፣ ሰፈር፣ ፖሊስ ፀባችን ሰልችቶት ነበር፡፡ በአንድ ዓመት በዓል ጊዜ በተነሳ ግጭት ሁላችንም ከቤቱ ወጥተን ወደ ቤተሰቦቻቸው ሄደን እንድናከብር ተወስኖብን ነበር፤›› ሲሉ ይህ መቼም ከልባቸው እንደማይጠፋ የመጡበትን አኗኗር ያብራራሉ፡፡

ገመና ከታቹ

ጊዜው 1973 ዓ.ም. ነው፡፡ ቦታው የዛሬው ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 ሞላ ማሩ፣ ከረዩ ሰፈር ይባላል፡፡ በአካባቢው በቀበሌ፣ በመንግሥትና በግላቸው ቤት ቤት የሚኖሩ 52 አባወራዎች ነበሩ፡፡ መንግሥት ሥፍራውን ዓለም ማያ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ለመገንባት ስለፈለገው እንዲለቁና ለእያንዳንዳቸው 4×4 የሆነ በቆርቆሮ የተሠሩ 52 መኖሪያ ክፍሎች ውስጥ እንዲገቡ ይወሰንባቸዋል፡፡

በወቅቱም ወደ ቤቶቹ ለመግባት የተስማሙት የያኔው ትምህርት ሚኒስቴር ቤት እንደሚሠራላቸው ስላስታወቃቸው እንደነበር ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ ይህን የሚከታተሉ ኮሚቴዎች ከነዋሪዎቹ ተውጣጥተው ነበር፡፡ ሆኖም ሰሚ እንዳጡና ኮሚቴዎቹ በእርጅናና በሞት በመለያየታቸው፣ ጉዳያቸውን የሚከታተል ቀርቶ የት እንደወደቁ የሚያስታውሳቸው እንደጠፋም ያክላሉ፡፡ ዛሬ መንደሩ ከመፍረሱ በፊት አንድ ክፍል ውስጥ ከአራት እስከ 12 የሚሆኑ ቤተሰቦችና ደባሎች ላለፉት 40 ዓመታት ኖረዋል፡፡  

በእነዚህ የቆርቆሮ መኖሪያ መንደሮች በወቅቱ የቀን ሥራ የሚሠሩ፣ አስተማሪዎች፣ የጉሊት ነጋዴዎች የሚተዳደሩ ይኖሩባቸው እንደነበሩ በአካባቢው ከ30 ዓመት በላይ የኖሩት ወ/ሮ ኪሮስ በርሄ ያስታውሳሉ፡፡ እሳቸውም እንደ ሌሎቹ ከሌላ የቤተሰብ አባል ጋር በደባል ስምንት ሆነው ይኖሩ ነበር፡፡ ሁለት ልጆቻቸውንና ባለቤታቸውን አስታመው ቀብረዋል፡፡

‹‹የቆርቆሮ ቤት ቀን ፀሐይ፣ ማታ ብርዱ›› የሚሉት ወ/ሮ ኪሮስ፣ አንድ ሽንት ቤት ለአራት አባወራ አንድ ኩሽና ለአራት አባወራ በመሆኑ መኖር መከራ እንደነበር ያወሳሉ፡፡ ቀድሞ በነበረው መንደር ሐዘንም ደስታም ይከናወን የነበረው ከመንደሩ መግቢያ ላይ ባለች ክፍት ቦታ ነበር፡፡ በተደጋጋሚ የተነሳ እሳት ሁለት ቤቶችን አውድሞ ያውቃል፡፡ በአንድ ወቅት በተከሰተው የተቅማጥ ወረርሽኝ አካባቢው ተጎድቶም ነበር፡፡

በውስጡ ያሉ ነዋሪዎች ወትሮም እጅ አጠር የነበሩ ሲሆን፣ የኑሮ ውድነቱ እየከፋ ሲመጣም ቤት ውስጥ ቆጥ በመሥራትና ልጆቻቸውን አልጋ ስር በማስተኛት ቆጡን በከተማዋ ላሉ የኔ ቢጤዎችና ጎዳና ተዳዳሪዎች ማደሪያ በማከራየት ኑሮዋቸውን ይደጉሙ እንደበር ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡

የባህል መጠጥ የሚሸጡ አልፎ አልፎ ሴተኛ አዳሪነት የሚሠሩበት እንደነበርና ቀስ እያለም ከመኖሪያ መንደርነት የቀለጠው መንደርነት ተቀይሮ ንፅህናው የጎደለ፣ ሁሉም ነገር የጋራ የሆነበት፣ ምንም ዓይነት የግል ገበና የማይደበቅበት፣ ለልጆች አስተዳደር ምቹ ያልሆነና እስትንፋስን ብቻ ለማቆየት ትግል የሚደረግበት አካባቢ ሆነ፡፡

ዛሬ የተለያየ በሽታ ያሉባቸውና በመንደሩ ነዋሪዎች ዕርዳታ የሚተዳደሩት ወ/ሮ ሲሳይ መላክ፣ ከዛሬ 30 ዓመት በፊት ጀምሮ የነበረውና ከሁለት ወር በፊት የተቀየረውን የመንደሩን ገጽታ ያብራራሉ፡፡

ማንም የመንግሥት አካል መጥቶ ጠይቋቸው እንደማያውቅና በአንድ ወቅት የዶ/ር ጀንበር ተፈራ የዕርዳታ ድርጅት ቤቱን ለመሥራት መጥቶ የቀበሌው ሥራ አስኪያጅ ‹ከእነሱ የባሱ በካርቶን የሚኖሩ አሉ› በማለት እንደመለሰባቸው ያስታውሳሉ፡፡

ወደ መንደሩ ለመግባት በሞላ ማሩ በበርበሬ ተራና በጌጃ ሰፈር በኩል መግባት ይቻላል፡፡ ቤቶቹ ተጠጋግተው በጭቃ የተሠሩ ናቸው፡፡ ሕፃናት፣ የቤት እንስሳት፣ መንገድ ላይ የሚሰጡ ልብሶች አሁንም በዚያ አካባቢ የሚያድሩ የኔ ቢጤዎች የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ በአካባቢው ካሉ የአረቄ ቤቶች የሚሰማው ሁካታ፣ በራቸው ላይ ስካር የጣላቸው ሰዎች፣ ግማሽ ጣራቸውና መስኮታቸው በላስቲክ የተሠሩ ቤቶች ከመንገዱ ግራና ቀኝ ያሉ የፍሳሽ ቱቦዎች ሽታ፣ ጉሊት ቸርቻሪዎች፣ ጫት ቤቶች፣ በኮብልስቶን የተሠራው መንገድ የከረዩ ሰፈር መገለጫ ናቸው፡፡ ለ52 አባወራዎች የሠራውና ጥር 27 ቀን 2013 ዓ.ም. የተመረቀው ‹‹ዋሊያ መንደር›› ተብሎ ተሰይሟል፡፡

ሄኒከን ኢትዮጵያ ‹‹ደራሽ›› በሚለው ፕሮጀክቱ ከ8.4 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ 52ቱን የቆርቆሮ ቤቶችን በብሎኬት በመሥራት ለነዋሪዎቹ አስረክቧል፡፡

የመኖሪያ መንደሩ በየብሎኮች የተከፋፈለና 52ቱም አባወራዎች ሳይነጣጠሉና ማኅበራዊ ግንኙነትቸው ሳይበተን ቀድሞ ይኖሩበት በነበረው ቦታ ላይ የተገነባ ነው፡፡ ክፍሎቹ ጣራቸው እስከ አራት ሜትር ከፍ ተብሎ የተሠራ በመሆኑ ቆጥ መሳይ በመሥራት ተጨማሪ ክፍል ለማግኘት ያስችላቸዋል፡፡ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ጨምሮ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ዝርጋታ ያለው ነው፡፡ የጋራ መፀዳጃ ቤቶችም ተሠርተዋል፡፡ ደባሎች የነበሩም ዛሬ የራሳቸውን ክፍል አግኝተዋል፡፡ መንደሩ ዛሬ ከቀድሞው በተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ ግንባታውን ሙሉ ለሙሉ ገንብቶ ለመጨረስ ሁለት ወር ፈጅቷል፡፡ የሄኒከን ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ በሻህ፣ በአካባቢው ላይ የሚገኝ ሲቪሲዶ የሚባል ግብረ ሰናይ ድርጅት አካባቢው በሚኖሩ ከ200 በላይ አቅመ ደካሞች ምሳ እንዲያበሉ መጠየቁና በዚህ አጋጣሚ ሁለቱ ሰዎች ኑሮዋቸው ምን ይመስላል በሚል ለማየት ወደ መንደሩ በማቅናታቸው ቤቶቹን ለማደስ እንዳነሳሳቸው ይናገራሉ፡፡ የሁለት ሰው ብቻ ለይቶ መሥራት ከባድ በመሆኑ 52 ቤቶች የተያያዙ በመሆናቸው ሁሉንም እንደ አዲስ ሠርተዋል፡፡

በምረቃው ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥራቶ በየነ፣ ‹‹እንደዚህ ያሉ ግንባታዎች መለመድ ያለባቸውና በተለይ ለታችኞቹ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከሌሎች የከተማ ነዋሪዎች እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ሊቀጥልና ሊበረታታ ይገባዋል፤›› ብለዋል፡፡ የማኅበረሰብ ኃላፊነታቸውን ለሚወጡ ድርጅቶች የአስተዳደሩ ዕገዛ እንደማይለይም ገልጸዋል፡፡

እነ ወ/ሮ አሰለፈች ነጋሽና የመንደሯም ነዋሪዎች ገመናችን ተከተተ በማለት ቁልፋቸውን ከአስተዳደሩና ከሄኒከን ኢትዮጵያ ኃላፊዎች እጅ ተረክበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...