Monday, May 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሦስት የግብርና ሜካናይዜሽን ማዕከላት በተያዘው ዓመት እንደሚቋቋሙ ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በተያዘው የበጀት ዓመት የግብርና ግብዓቶችንና የሜካናይዜሽን አገልግሎቶችን የሚያቀርቡ ሦስት ማዕከላትን በደቡብ ምዕራብ፣ በሰሜንና በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች እንደሚያቋቁም አስታወቀ፡፡

ቀደም ሲል በተናጠል ይሠሩ የነበሩ አምስት ድርጅቶች ሲያከናውኑ የነበሩትን ተግባራትን አንድ ወጥ በሆነ የኮርፖሬት አመራር እንዲያከናውን ኃላፊነት የተሰጠው የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የዘር፣ የአፈር ማዳበሪያና የፀረ ተባይ ኬሚካሎች፣ የእርሻ መሣሪያዎችና መለዋወጫዎች፣ እንዲሁም የሜካናይዜሽን አገልግሎቶች የሚቀርቡባቸውን ማዕከላትን በደቡብ ምዕራብ ቦንጋ፣  በደቡብ ምዕራብ ጎንደርና በራያ አላማጣና መሆኒ በተባሉት አካባቢዎች በተያዘው የበጀት ዓመት እንደሚገነባ አስታውቋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የመጀመሪያው የግብርና ግብዓትና ሜካናይዜሽን አገልግሎት መስጫ ማዕከል በደቡብ ምዕራብ ቦንጋ በሁለት ሔክታር መሬት ላይ ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ መገንባት ይጀመራል፡፡ ቦታውን ለማልማት የዲዛይን ሥራ እየተጠናቀቀ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በተያዘው ዓመትና ኮርፖሬሽኑ ባስጠናው የአሥር ዓመት ዕቅድ ላይ እንደተቀመጠው፣ በመንግሥት የተያዘ የኩታገጠም እርሻ በሜካናይዜሽን አገልግሎት የተለያየ የፈረስ ጉልበት ያላቸው ትራክተሮችን፣ መለዋወጫዎችን፣ እንዲሁም የጥገናና የሥልጠና አገልግሎት በመስጠት የግብርና ቴክኖሎጂን ተደራሽ ለማድረግ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላቱን በማስፋፋት ላይ ነው፡፡

ኮርፖሬሽኑ በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ አማካይነት ባስጠናው የአሥር ዓመት ዕቅድ፣ በጠቅላላው አሥር ማዕከላትን ለማስፋፋት አቅዷል፡፡ ከ2013 እስከ 2017 ዓ.ም. ባለው የዕቅዱ የመጀመሪያው አምስት ዓመታት ከአሥሩ ማዕከላት ሰባቱን እንደሚገነባ አቶ ክፍሌ አስታውቀዋል፡፡

ታዳጊ ክልሎችን ታሳቢ ያደረገ ተደራሽነትና አገልግሎት ከመስጠት አኳያ ኮርፖሬሽኑ ምን እያከናወነ እንደሚገኝ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ክፍሌ ሲመልሱ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚቋቋመው ማዕከል ከጅማ እስከ ጋምቤላ የሚደርሰውን አካባቢ ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ አፋር፣ ሶማሌ፣ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ክልሎችን በይበልጥ በመድረስ የምርጥ ዘር አቅርቦት፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ የፀረ ተባይና የፀረ ዓረም፣ እንዲሁም የተለያዩ የፈረስ ጉልበት ያላቸው ትራክተሮችና ኮምባይነሮችን ከውጭ በማስመጣት ከማዕከላቱ መግዛት ለሚችሉ አርሶ አደርና አርብቶ አደሮች በሽያጭ፣ አቅሙ ለሌላቸው ደግሞ በተመጣጣኝ ዋጋ የማከራየት አገልግሎት ለመስጠት እየተሠራ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ለኢትዮጵያ ግብርና ምርታማነት መጨመር አሰተዋጾ ከሚያደርጉት የግብርና ግብዓቶች አንዱ የአፈር ማዳበሪያ እንደሆነ የገለጹት አቶ ክፍሌ፣ ኮርፖሬሽኑ ከመቋቋሙ በፊት የማዳበሪያ ግዥ ይፈጸም የነበረው በቀጥታ ከአምራች ኩባንያ ሳይሆን በወኪሎች ይፈጸም የነበረውን ሒደት በማስቀረት ግልጽ የዓለም አቀፍ ጨረታ ሥርዓት በመከተል፣ አምራች ኩባንያዎች ማሳተፍ የሚያስችል የጨረታ ሥርዓት በመዘርጋት የዋጋ ቅናሽ ማግኘት መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች