የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለዓመታት ሲጠቀምበት የቆየውን የብድር ወለድ ምጣኔ ላይ ጭማሪ አደረገ፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በብድር ወለድ ምጣኔ ላይ ካደረገው ማሻሻያ ባሻገር፣ በዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎቶችም ላይ ተመሳሳይ የዋጋ ማሻሻያ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
‹‹በባንኩን የገቢና የወጪ መዛባትን ለማስተካከል የተደረገ ነው›› የተባለውን የአገልግሎት የዋጋ ማሻሻያ በሁሉም የአገልግሎቶቹ ላይ የሚፈጸም እንደሆነ አስታውቋል፡፡
በባንኩ መረጃ መሠረት በአብዛኞቹ አገልግሎቶቹ ላይ ከአንድ በመቶ ያልበለጠ የዋጋ ጭማሪ የተደረገ ሲሆን፣ በብድር ወለድ ምጣኔው ላይ ግን እንደየ ብድር ዓይነቶቹ ተከፋፍሎ የብድር ወለድ ምጣኔ ቀድሞ ከነበረበት ከፍ ማለቱ ታውቋል፡፡
በባንኩ የብድር ወለድ ምጣኔ የዋጋ ማሻሻያ መሠረት ለኮርፖሬት የብድር ወለድ ምጣኔ ከስምንት በመቶ ወደ ዘጠኝ በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ ለቤቶች ልማት የሚሰጥ ብድር ደግሞ በአንድ በመቶ ጨምሮ ወደ 10.5 በመቶ ከፍ እንዲል ተወስኗል፡፡
ዛሬ ይፋ በተደረገው አገልግሎት ዋጋ ማስተካከያ መሠረት ከፍተኛ ጭማሪ የተደረገው በውጭ ምንዛሪ አገልግሎት ዘርፍ ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡ ለውጭ ምንዛሪ አገልግሎት ለዘጠና ቀናት ለሚሠሩ አገልግሎት ይከፈል የነበረው የ5.5 በመቶ ክፍያ ወደ 9.5 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡
በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ ለሚሰጥ የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት አንዳንድ ምርቶች ላይ ዝቅ ባለ የአገልግሎት ዋጋ ይስተናገዳሉ፡፡ በዝቅተኛ በ4.5 በመቶ የአገልግሎት ዋጋ ይስተናገዳሉ የተባሉ የምርት ዓይነቶች ደግሞ ማዳበሪያ፣ መድኃኒት፣ ስኳርና ዘይት ምርቶች ናቸው፡፡ ለእነዚህ ምርቶች ይጠየቅ የነበረው የውጭ ምንዛሪ የአገልግሎት ዋጋ 4.5 በመቶ ከመሆኑ ውጪ ሌሎች የውጭ ምንዛሪ አገልግሎቶች በአዲሱ ተመን መሠረት የሚስተገዱ ይስተናገዳሉ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ንግድ ባንክ በሌሎች አገልግሎቶቹ ላይ እንደየ አገልግሎቱ ዓይነት ያደረገው የዋጋ ማሻሻያ አሁንም በኢንዱስትሪ ውስጥ ዝቅተኛ የሚባል ተመን ስለመሆኑ ይጠቀሳል፡፡
ባንኩ እንዲህ ካለው ውሳኔ ላይ የደረሰው አብዛኞቹ አገልግቶች ወቅታዊውን የገበያ ሁኔታ ያላገናዘበ የአገልግሎት ዋጋ ይዞ በመዝለቁ በባንኩ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ በመምጣቱ መሆኑም ተገልጿል፡፡
በዚሁ ጉዳይ ማብራሪያ የሰጡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ በባንኩ ገቢና ወጪ ላይ የተከሰተውን ጫና ለመቀነስ ይህ ማሻሻያ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ሌላ በዝቅተኛ ወይም በነፃ በሚሰጥባቸው አገልግሎቶች ላይ አነስተኛ ማስተካከያ ለማድረግና ከገበያው ጋር ለማቀራረብ በአብዛኛው የአገልግሎት ዘርፎች ላይ ከአንድ በመቶ ያልበለጠ የወለድ ምጣኔ መጨመር የሚያስችለውን የዋጋ ማሻሻያ ስለመደረጉ ፕሬዚዳንቱ መግለጻቸው ታውቋል፡፡
የወጪ ንግድን ለማበረታታት ግን ከወጪ ንግድ ጋር የተያያዙ ብድሮች አገልግሎቶቹን ላይ ሲያስከፍል የነበረውን የወለድ ምጣኔ፣ እንዲሁም መንግሥት ለሚያስመጣው መድኃኒት ለማቅረብ የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት ተመን ላይ ቅናሽ ተደርጓል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እስከ 2012 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ ይዞት በመንቀሳቀስ ላይ የቆየው የካፒታል መጠን 49.6 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ አጠቃላይ የቅርንጫፎቹን ቁጥር ደግሞ 1,825 አድርሷል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2013 የጀመርያው የሩብ ዓመት ከታክስ በፊት ያስመዘገበው ትርፍ 3.1 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህ ትርፍ ግን ከ2012 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ቅናሽ የታየበት ሆኗል፡፡ በ2012 የመጀመርያ ሩብ ዓመት ከታክስ በፊት አትርፎ የነበረው 6.1 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡