የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶለት በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀው የካፒታል ገበያ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ በፓርላማ ሲፀድቅ፣ የሚያነቃቃቸውና እንደ አዲስ እንዲመሠረቱ የሚያደርጋቸው ዘርፎች በርካታ እንደሆኑ ተገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸው ሴሉላር ኮንሰልተንሲና ኮርነር ስቶን የተባለ በካፒታል ገበያ ላይ ትኩረት አድርጎ ከሚሠራ የአማካሪ ድርጅት በጋራ ባዘጋጁት የካፒታል ገበያ የሚፈጠሩ የኢንቨስትመንት ዕድሎችንና አጠቃቀማቸውን የሚዳሰስ ሴሚናር፣ ሐሙስ የካቲት 4 ቀን 2013 ዓ.ም. በኔክሰስ ሆቴል በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡
በውይይቱ ላይ የመነሻ ገለጻና ሙያዊ ማብራሪያ የሰጡት የኮርነር ስቶን አማካሪ ድርጅት ባለድርሻ አቶ ቶማስ ፈረደ እንደገለጹት፣ የካፒታል ገበያን ሒደት እጅግ በጣም ውስብስብ አድርጎ የማሰብ ዝንባሌ አለ፡፡ ምንም እንኳን ሒደቱ ውስብስብ እየሆነ የሚሄደው የካፒታል ገበያው ሲስፋፋ ቢሆንም፣ ነገር ግን በኢትዮጵያ የሚጀመረው ግን ቀላል ከሚባለው የግብይት ሒደት ነው ብለዋል፡፡
የካፒታል ገበያ በቀጥታ የሚገባበት ሳይሆን የተለያዩ ጥናቶችና የሕግ ማዕቀፎች ታይተው የሚገባበት እንደሆነ የገለጹት ባለሙያው፣ አንድ ባለሀብት በካፒታል ገበያ አንድን ድርጅት ወይም የድርጅት ድርሻን ከመግዛቱ በፊት የፋይናንስ አቅም የሚያሳይ መረጃ ስለሚያስፈልገው፣ መረጃውን የሚመረምሩለት የተጠናከሩ የሒሳብ አዋቂ ድርጅቶች ያስፈልጉታል፡፡
የካፒታል ገበያ በሰነድ ግብይት ላይ የተመረኮዘ እንደ መሆኑ መጠን፣ ያለ ሕግ ባለሙያዎችና ድርጅቶች ዕገዛ የቱንም ያህል ዕርምጃ መሄድ እንደማይቻል ገልጸው፣ ከዚህ በተጨማሪ ባለሀብቶች የተሳሳተ መረጃ ይዘው ወደ ካፒታል ገበያ እንዳይገቡ የጥናትና ማማከር ድርጅቶች ከፍተኛውን ሚና እንደሚጫወቱ፣ የካፒታል ገበያ መቋቋም ተቋማትን የማስፋፋትም ሆነ የማነቃቃት ዕድሉ ሰፊ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ቶማስ ገለጻ፣ በኢትዮጵያ ባንኮችን የሚቆጣጠር አካል እንዳለ ሁሉ፣ የካፒታል ገበያ እንቅስቃሴም በዚያው ሒደት ወደ ሥራ ይገባል ብለው እንደሚጠብቁ አስታውቀዋል፡፡ ምናልባት በኢትዮጵያ የሚገኙ ተቋማት በጣም ካለመዳበራቸው የተነሳ የካፒታል ገበያ የመጀመርያ የግብይት ማዕከላት የሚሆኑት ባንኮችና የቴሌኮም አገልግሎት ድርሻዎች እንደሚሆኑ አስታውቀው፣ በሒደት ግን ሌሎች ድርጅቶችም ያላቸውን ሀብትና አሠራር አስጠንተው ገበያውን የሚቀላቀሉበት ሁኔታ እንደሚኖር አስረድተዋል፡፡
የሰርበረስ ካፒታል ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንትና ከፍተኛ አማካሪ፣ እንዲሁም በብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ኃይለ ሚካኤል በውይይቱ እንደገለጹት፣ ሰዎች የአንድ ኩባንያ ድርሻን ገዝተው ኢንቨስት ለማድረግ ሲያስቡ መጀመርያ ለግብይት የቀረበው ኩባንያ ምን እንደሠራ፣ ዕድገቱና ሌሎች ከድርጅቱ ጋር የሚያያዙ ነገሮች ዓይተው እንጂ ሰነድ ስለመጣ ብቻ ወደ ግዥ የሚገባበት ሁኔታ ሊኖር አይገባም ብለዋል፡፡ ስለሆነም ወደ ካፒታል ገበያ ግብይት ተቋማት ሲገቡ የካፒታል ገበያውን የሚያስተዳድረው አካል በሚያወጣው የሕግ ማዕቀፍና ዕውቅና መሠረት አሠራሩ የሚከናወን ይሆናል ሲሉ አስረድተዋል፡፡