Monday, October 3, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

  የሳምንቱ ገጠመኝ

  ቀን:

  ታሪክን ወደኋላ መለስ ቀለስ እያልን መልከት ማድረግ አስፈላጊ ቢሆንም፣ ያለፈው ታሪክ ላይ ተንጠልጥለን በክፉና በደግ ድርጊቶች ላይ መወዛገብን ሥራችን ካደረግን፣ ተስፋም አይኖረንም፡፡ ዛሬን በሚገባ ከተጠቀምንበት ነገን ለማሳመር እንችላለን፡፡ ዛሬን ካበላሸን ግን ነገ የባሰ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የእኔም ገጠመኝ መነሻ ይህ ነው፡፡ ከሃያ ዓመታት በፊት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ፣ በተለይ ከክልል የሚመጡ ተማሪዎች ለምን እርስ በርስ ይጋጩ እንደነበር ግራ ይገባኝ ነበር፡፡

  እኔ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ ተወልጄ ባድግም፣ አብሮ አደጎቼ እንደ እኔ እዚያው ሠፈር ውስጥ ተወልደው ያደጉ ቢሆንም፣ የማን ቤተሰብ ሥረ መሠረቱ ከየት እንደሆነ እንሰማ ነበር፡፡ ነገር ግን ቤተሰቦቻችን የተወለዱበትን አካባቢ ጥለው መጥተው አዲስ አበቤ ሆነው ስላሳደጉን፣ እነሱም ሆነ እኛ ልጆቻቸው ማንነት ላይ ተንጠልጥለን ሳይሆን እዚህ በመሠረትነው ማኅበራዊ መሠረታችን ላይ እንደ ቤተሰብ አብሮን ኖረናል፡፡ በዚህም ምክንያት የሰሜን ማዘጋጃ ሠፈር ልጆች ሆነን ዓመታትን በፍቅር ዘለቅን፡፡

  እኛን ከሰብዓዊ ፍጡርነት የዘለለ ግንኙነት ሳይበግረን ወይም በማንነታችን ዳራ ምክንያት ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ እምነቶች ውስጥም ሆነን ስላደግን ሌላው ጉዳያችን ትዝ ብሎንም አያውቅም፡፡ አንዳንዴ በአንዳንድ ምክንያቶች ስንጋጭ እንኳ ካላግባባን ጉዳይ በዘለለ የምናመካኝበት ሰበብ አልነበረንም፡፡ ፀባችንም ጊዜያዊ ነበር፡፡ ከዚያ ውጪ የሰሜን ማዘጋጃ ልጆች ነን፡፡

  ይህ ሒደት ከአንደኛ ደረጃ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ዘልቆ በመሄድ፣ ከጊዜ በኋላ ከሌሎች ሠፈር ልጆች ጋር ወዳጅነት ፈጥረን እስከ መጋባት ደርሰናል፡፡ አልፈን ተርፈንም ተዋልደናል፡፡ ዩኒቨርሲቲ ስንገባ ግን አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ ወዘተ በመባባል ተማሪዎች በሥለት መሣሪያ ጭምር እየተወጋጉ ራሳቸውን ለአደጋ ሲዳርጉ፣ እንዲሁም ከፍተኛ ረብሻ ሲፈጥሩ ይጨንቀን ነበር፡፡ ያለመድነው በመሆኑም ከፍተኛ ሥቃይ ገጥሞናል፡፡

  ይህ ሁሉ ጣጣ የመጣው ግን ሕወሓት/ኢሕአዴግ የሚሉት ጉድ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረ በኋላ ነው፡፡ እኛ ሠፈር አማራ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ፣ ትግሬ፣ ወላይታ፣ ዶርዜ፣ ከምባታ፣ ወዘተ በሚባሉ ማንነቶች የሚታወቁ ቤተሰቦች ነበሩ፡፡ እነዚህ ሁሉ ቤተሰቦች በአንድ ሠፈር ውስጥ ሲኖሩ በማንነታቸው ምክንያት ሲጣሉ ተሰምቶ አያውቅም፡፡ በሕይወት ያሉ ሰዎች በሙሉ ምስክሮቼ ናቸው፡፡ ማንነቶቹ መኖራቸው ቢታወቅም በማንነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰበት ሰው አልነበረም፡፡

  ሌላው ቀርቶ በዘመነ ቀይ ሽብር የተገደሉ ወጣቶች በማንነታቸው ሳይሆን፣ የኢሕአፓ አባላት ናቸው ተብለው ነው ለሕልፈት የተዳረጉት፡፡ ይህ ደግሞ በብዙ ሥፍራዎች የሆነ ነው፡፡ አንድ ላይ የኖረን ማኅበረሰብ ማንነቱን ወይም እምነቱን በመታከክና በሰነድ የተረጋገጠ ማስረጃ ሳይኖር፣ አገርን ችግር ውስጥ ለመክተትና ሥልጣን ላይ ለብዙ ዓመታት ለመቆየት ሲባል ሕዝቡን ማባላት የተለመደው በሕወሓት መራሹ ኢሕአዴግ ነበር፡፡

  ይህ ኃይል ነው እንግዲህ በኢትዮጵያ ላይ ለ30 ዓመታት ያህል እንደ ዘንዶ ተጠምጥሞ፣ ሕዝባችን እያተራመሰና የአገር ሀብት እየዘረፈ ለበርካታ ዓመታት እንደ ቅኝ ገዥ መንሰራፋት የፈለገው፡፡ በተለይ ሕወሓት የሚባለው የሰይጣኖች ስብስብ ወጣቶች የውሸት ታሪክ እየተጋቱ እርስ በርስ እንዲጋጩና እንዲጋደሉ፣ ለዚህ ደግሞ በተለያዩ ማንነቶች ውስጥ ያሉ እበላ ባዮችን በመጠቀም ሐሰተኛ ድርሰት እንዲጽፉ በማድረግ ኢትዮጵያዊ ማንነትን እንዲበርዙ አደገኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ ኦሮሞው በአማራው፣ አማራው በትግሬው፣ ወዘተ እንዲነሱ በማድረግ እሳት እየጫረ ትልቅ ጉዳት አድርሷል፡፡

  የሐሰተኛ ትርክቱ አጫፋሪ የሆኑት እንደ ኦነግ ያሉ ኃይሎችና ሌሎች አድርባዮችም፣ ለሥልጣንና ለጥቅም ሲሉ ብቻ አገር የማፍረስ እንቅስቃሴ አጃቢ በመሆን ወጣቶችን ለጥፋት ተጠቅመውባቸዋል፡፡ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በሻሸመኔ፣ በአርሲ፣ በባሌ፣ በወለጋ፣ ወዘተ በንፁኃን ወገኖቻችን ላይ የተፈጸሙት አሰቃቂ ግድያዎችና ማፈናቀሎች፣ እንዲሁም የንብረት ውድመቶች የዚህ የጥፋት ሴራ አካላት ናቸው፡፡ ሕወሓትና የጥቅም ሸሪኮቹ እነሱ የሚፈልጓት የተዳከመችና የተፈረካከሰች ኢትዮጵያ ስለሆነች፣ አገር የማፍረስ ዓላማቸው የት ድረስ እንደነበረ በቅርቡ ሕወሓቶች በአገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸሙት የአገር ክህደት በቂ ምስክር ነው፡፡

  በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን ሆኖ ሕወሓት ዳግም እንዳይመለስ ተደርጎ ሲደመሰስ፣ አገር አፍራሾቹ ምን ዓይነት ድርጊት ውስጥ እንደተሰማሩ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ ጦርነት ለማንም አይጠቅምም፣ በሰላማዊ መንገድ አገር ትደግ፣ በሕዝብ ላይ መከራ አይምጣ፣ ከጦርነት ማንም አትራፊ አይሆንም ተብሎ የተለመነው ዕብሪተኛ በመረጠው ውጊያ ሲደመሰስ የምን ለቅሶ ነው? ያንን ሁሉ ልመና ከፈሪነት በመቁጠር ሲፎክር የነበረ ኃይል መጨረሻው ይህ እንደሚሆን፣ የናዚና የፋሽስት ፓርቲዎችን ታሪክ በመመርመር መረዳት ይቻላል፡፡

  ሕወሓትና የትግራይ ሕዝብ አንድ አይደለም ተብሎ ሲነገር የነበረው እውነት ለመሆኑ ማረጋገጫው፣ ሕወሓት መሠረተ ልማቶችን ማፈራረሱና ሕዝቡን ለችግር የሚዳርግ ድርጊት ውስጥ መግባቱ ነው፡፡ ከራሱ ጥቅም በላይ ለምንም ነገር ደንታ የሌለው ስብስብ በጫረው እሳት ተቃጥሎ ሲያበቃለት፣ አሁን ርብርብ መደረግ ያለበት ሕዝቡን ለመታደግ ብቻ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን የትግራይ ወገኖቻችንን ከደረሰባቸው መከራ መታደግ ግዴታችን ነው፡፡ በመሰሪዎች ሴራ የገዛ ወገኖቻችንን እንደ ጠላት እንድናይ የተደረገው ሙከራ የሚከሽፈው፣ በዚህ ታሪካዊ ወቅት ከጎናቸው ሆነን ስናበረታታቸውና ስንደግፋቸው ብቻ ነው፡፡

  በሰሜን ማዘጋጃ ሠፈራችን ቤተሰቦቻችን በማንነትና በእምነት ሳይለያዩ ያስተማሩን፣ የተገኘውን ተካፍሎ አብሮ መብላትና መተጋገዝን ነው፡፡ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎችም የተለመደው ይህ ፈጣሪ የሚወደው ተግባር ነው፡፡ ኢትዮጵያም ፀንታ የኖረችው በዚህ ታላቅ እሴት ነው፡፡ ሴረኞችና መሰሪዎች ገለል ሲሉልን እኛ ኢትዮጵያዊያን እንዴት አብረን በፍቅርና በመተሳሰብ እንደምንኖር እናውቅበታለን፡፡ ነገን የምናሳምረው ዛሬ ስለሆነ፣ ከውሸታም ፖለቲከኞች ሐሰተኛ ትርክት ተላቀን እንደ ሰው እንኑር፡፡

  (ያሬድ ዮሐንስ፣ ከሰሜን ማዘጋጃ)

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img