Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሰሞኑን ተግባራዊ የተደረገው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ተገቢነት እያነጋገረ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከኢትዮጵያ ዓመታዊ በጀት ውስጥ ከፍተኛውን በጀት በመውሰድ ለዘመናት የዘለቀው የነዳጅ ግዥ ነው፡፡ ለነዳጅ የሚወጣው ዓመታዊ ወጪም በየዓመቱ እየጨመረ ነው፡፡ ባለፉት አሥር ተከታታይ ዓመታት መረጃዎች እንደሚያሳዩት ለነዳጅ ግዥ የወጣው የውጭ ምንዛሪ እያደገ ሄዷል፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅትን መረጃ ዋቤ ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አኃዛዊ መረጃ እንደሚያሳው፣ በ2003 ዓ.ም. አገሪቱ ለነዳጅ ዋጋ ያወጣችው የውጭ ምንዛሪ በወቅቱ የምንዛሪ ዋጋ መሠረት 22.8 ቢሊዮን ብር መሆኑን ነው፡፡ ይህ አኃዝ እያደገ መጥቶ በ2012 መጨረሻ ላይ 62.05 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በ2012 ዓ.ም. ለነዳጅ የወጣው ወጪ ግን ከሌሎች ዓመታት በተለየ በአንዱ ዓመት ልዩነት ወደ ስምንት ቢሊዮን ብር ቅናሽ የታየበት ነበር፡፡ ይህም ባለፈው ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ ቅናሽ ያሳየ በመሆኑ የአገሪቱ ዓመታዊ የነዳጅ ዋጋ ወጪ ሊቀንስ መቻሉን የሚጠቁም ነው፡፡ ከአንድ ዓመት ቀደም ብሎ በ2011 ዓ.ም. እስካሁን ኢትዮጵያ ለነዳጅ ግዥ በአንድ ዓመት ውስጥ ከፍተኛ የተባለውን ወጪ ያወጣችበት ዓመት ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ ይህም 70 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን የሚያመለክት ነው፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በነዳጅ የመሸጫ ዋጋ ማስተካከያ እንደተደረገበት በማሳወቅ አዲስ የነዳጅ ሽያጭ ዋጋ ያስቀመጠ ሲሆን፣ ይህም የነዳጅ ዋጋ መሸጫ በአማካይ 20 በመቶ ጭማሪ እንደተደገበት የሚያሳይ ነው፡፡

የዋጋ ግሽበት 20 በመቶ ወጥቶ ለወራት በዘለቀበት በዚህ ወቅት የተደረገው በአዲሱ የነዳጅ ማሸጫ ዋጋ እንደ የአካባቢ የሚለያይ ቢሆንም ለአዲስ አበባ የነበረው የአንድ ሌትር ናፍጣ 21 ከ46 ሳንቲም ብር ሆኗል፡፡

ይህ መረጃ ከተነገረበት ጊዜ ጀምሮ በገበያ ውስጥ የሸቀጣ ሸቀጥ ምርቶች ዋጋ ሳይታሰብ እያሻቀበ የወጣ መሆኑ ሁኔታውን አሳሳቢ አድርጎታል፡፡ እንዲህ ያለ የነዳጅ ጭማሪ ሲደረግ የዋጋ ዕድገት የሚጠበቅ ቢሆንም በአዲሱ የነዳጅ ዋጋ ሳይነካው የገባ ዕቃ ሁሉ አዲስ ዋጋ እየወጣለት መሆኑ የሰሞኑ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡

ከብዙዎቹ አስተያየት ግን የነዳጅ ጭማሪ የኑሮ ውድነቱን ያብሰዋል የሚል ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በእርግጥ በዚህ ወቅት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ማድረግ ተገቢ ነው ወይ የሚለው ጥያቄም የብዙዎች ሆኗል፡፡ ከሰሞኑ በተደረገው የዋጋ ጭማሪውን በተመለከተ የንግድ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከሰጡት መረጃ መገንዘብ እንደሚቻለው ለነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ዋነኛ ምክንያት የዓለም የነዳጅ ዋጋ መጨመር ባለፉት ዓመታትም መንግሥት ነዳጅን በመደጎም ለኅብረተሰቡ ሲያቀርብም እንደነበር የሚጠቀስ ሲሆን፣ ባለፉት ሁለት ዓመታትም ለነዳጅ ወደ ሦስት ቢሊዮን ብር ለነዳጅ ድጎማ ማድረጉን ያመለክታል፡፡  

መንግሥት ይህንን ይበል እንጂ በዓለም ደረጃ ነዳጅ በቀነሰበት ወቅት ቅናሽ ሳያደርግ አሁን ጨመረ ተብሎ ዋጋ መጨመሩ በአንዳንድ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ዘንድም ብዥታ ፈጥሯል፡፡

በዚሁ ጉዳይ ጋር ያነጋገርናቸው አንድ የኢኮኖሚ ባለሙያ የነዳጅ ጋር ማስተካከያ አሠራሩ የዓለም ገበያን መሠረት ያደረገው ነው ከተባለ የነዳጅ ዋጋ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ዋጋው ቁልቁል በወረደበት ጊዜ የዋጋ ቅናሽ ሳይደረግ ወይም የዓለምን ዋጋ ባገናዘበ ሁኔታ ማስተካከያ ሲደረግ ቆይቶ አሁን ላይ መጠገኛ ጭማሪ ታየ ተብሎ ዋጋ መጨመሩ ተገቢ ነው ብለው እንደማያምኑ ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡

አሁን የተደረገው የዋጋ ጭማሪም ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ የሚችልና አሁን እየወጣ ያለውን የዋጋ ግሽበት ለመቀነስ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል የሚል እምነታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ እንደእሳቸው ምልከታ መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር እየወሰደ ያለው ዕርምጃ በቅርብ የሚያውቁ ቢሆንም፣ ግሽበቱን ከ20 በመቶ በታች ለማውረድ ባልተቻለበት ወቅት የነዳጅም ዋጋ ላይ ጭማሪ በማድረግ ተገቢ ነው ብለው አያምኑም፡፡  

አንደ ኢኮኖሚው ባለሙያ ማብራሪያ ዋጋውን መጨመር ግድ የሚል ከሆነ ነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በሚደረግበት ወቅት ግምት ውስጥ መግባት ያለበት የትኛው የነዳጅ ዓይነት ምን ያህል ጭማሪ ተደረገበት የሚለው ነው ይላሉ፡፡

በናፍጣና በቤንዚን ላይ የተጨመረው ዋጋ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖረው ተፅዕኖ ይለያያል፡፡ ከሁሉም የነዳጅ ዓይነቶች የዋጋ ግሽበት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚኖረው ናፍጣ በመሆኑ በዚህ ምርት ላይ የሚደረግ ጭማሪ በተለየ መታየት ይኖርበታልም ብለዋል፡፡

‹‹የትኛውም ምርት እንቅስቃሴ ከናፍጣ ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቅሰው፣ ምናልባት የግል ተሽከርካሪ ያላቸው ቤንዚን ላይ ሲጨምር ብዙ ድምፆች ሊያሰሙ ይችላሉ፡፡ ከኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ አንፃር ግን ከቤንዚን ይልቅ በናፍጣ ላይ የሚደረግ የዋጋ ጭማሪ በጥንቃቄ መታየት ለበት በመሆኑ ናፍጣን በመደጎም የዋጋ ግሽበቱ እንዳይባባስ መደረግ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ከሌሎች የነዳጅ ዓይነቶች ናፍጣን በተለየ መደጎሙ የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር ወይም አሁን ካለውም በላይ እንዳይወጣ ይረዳ ነበር ያሉት እኚሁ ኢኮኖሚ ባለሙያ፣ መንግሥት ይህንን ሥሌት ውስጥ አስገብቶ ማስተካከያ ማድረግ ግድ ሊለው እንደሚገባ ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

ስለዚህ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ማስተካከያ ወይም ጭማሪ በሚደረግበት ወቅት የዋጋ አጨማመሩ ምንን መሠረት ያደረገ ነው የሚለው መታየት እንደሚኖርበት ገልጸው፣ የሰሞኑ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የተደረገው ከዓለም አቀፉ የነዳጅ ዋጋ መጨመር ጋር የተያያዘ ነው የሚለውን ብዙም የማይስማሙበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ሲወጣና ሲወርድ በዚህም ማስተካከያ መደረግ እንደሚኖርበት የሚታመን ቢሆንም፣ አሁን ላይ በዚህን ያህል ደረጃ ዋጋ ጭማሪ ማድረጉ ተገቢነት ላይ የተለየ አመለካከት አላቸው፡፡ ይህም እየወጣ የመጣውን የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር በመንግሥት እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎች አሁን ላይ ብዙም ለውጥ ሳያሳይ ግሽበቱ ከ20 በመቶ በላይ መሆኑ እየታወቀ እንደገና ነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ ማድረግ ሁኔታውን ያባብሳል የሚል ሥጋት ስላላቸው ነው፡፡

ከሌላ አንፃር ሲታይም መንግሥት ጭማሪውን ያደረግሁት የዓለም የነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ ነው የሚል ምክንያት ላይም የተለየ አመለካከታቸውን ያንፀባረቁት ኢኮኖሚ ባለሙያው የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ በቀነሰበት ወቅት ዋጋው ላይ ማስተካከያና ቅናሽ ሳይደረግ አሁን የዓለም ዋጋ መጠነኛ ጭማሪ ስላሳየ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ላይ ጭማሪ መደረጉ ትክክለኛ አሠራር ነው ብለው ስለማያምኑ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው በነዳጅ ዋጋ ክለሳና ማስተካከያዎችን የተመለከቱ አሠራሮች ክፍተት ያለባቸው ስለመሆኑም ነው ይላሉ፡፡

ይህንንም ሲያብራሩ ከዚህ ቀደም የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያዎች ሲደረጉ እንዲተገበሩ የወጡ ሕጎች ሳይቀሩ በትክክል ካለመተግበራቸው ጋር የተያያዘ ወይም ግልጽ ካለመሆኑ ነው፡፡ ለዚህ አባባላቸው እንደ ምሳሌ የጠቀሱት ደግሞ፣ የነዳጅም ዋጋ ማስተካከያዎች በሚደረጉበት ወቅት የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያዎች በሚያደርጉበት ወቅት የሚፈጠርን ችግር በመቀነስ የነዳጅ ዋጋን የሚያረጋጋ ፈንድ በአዋጅ ተቋቁሞ ሳለ አሠራሩ ግልጽ ያለመሆኑን ነው፡፡ 

ስለዚህ የነዳጅ ዋጋ አጨማመርና አሠራር በራሱ ብቻ ችግር ያለበት መሆኑን የጠቆሙት እኚሁ የኢኮኖሚ ባለሙያ የነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ እንደተጠቀሰው፣ የፈንዱ ዋነኛ ዓላማ በዓለም ገበያ በሚከሰተው የነዳጅ ዋጋ ማደግ ምክንያት የሚያስፈልገውን ተጨማሪ ወጪ በመደጎም የነዳጅ ዋጋ ማረጋጋት ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ ዓላማን ሳያደናቅፍ መንግሥት ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ሥራዎች ወጪ መሸፈን ይሆናል በሚል ተጠቅሷል፡፡

ይህም ፈንድ የገቢ ምንጮች በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ በመቀነሱ ምክንያት ከሚገኝ ትርፍ ሒሳብና ለነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ እንዲውል ከሚገኝ የውጭ ዕርዳታ እንደሚሆን ያመለክታል፡፡

በዚህ ፈንድ በኩል የሚሰበሰብ ገንዘብ የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት የአገር ውስጥ ነዳጅ መሸጫ ዋጋ በሚወሰንበት ጊዜ ለነዳጅ መግዣና ለሌሎች ጉዳዮች ታሳቢ ተደርገው የነበሩ ወጪዎችና በትክክል በተደረገው መካከል የሚኖረውን ልዩነት ለፈንዱ ሒሳብ ገቢ የሚደረግ እንደሚሆን ይጠቀሳል፡፡ ይህ አዋጅ በትክክል እየተተገበረ ነው ከተባለ አሁን የሚደረገው ጭማሪ ጥያቄ የሚነሳበት ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል፡፡ በተለይ በ2012 በጀት ዓመት የነዳጅ ዋጋ በመቀነሱ ከቅናሹ የሚገኝ ገቢ በመኖሩ አሁን ላይ በዓለም ላይ የነዳጅ ጭማሪ ሲደረግ ከዚህ ፈንድ መደጎም ነበረበትም በማለት መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡

በጥቅል ሲታይ ግን በዚህ ሰዓት የነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ ማድረግ ምንም በማያጠራጥር ሁኔታ የሸቀጣ ሸቀጥ ምርት ላይ ዋጋ መጨመሩ የማይቀር መሆኑ ነው፡፡ ያላግባብ የዋጋ ጭማሪ የሚደረግበት ሁኔታ ስለሚፈጠር ይህንን ለመከላከል መንግሥት ሌላ ሥራ እንዲሚጠብቀው ያደርጋልም ይላሉ፡፡

ባለሙያው ናፍጣን ከሌሎች ነዳጅ ዓይነቶች ለይቶ መደጎም አንድ መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡ ድጎማ የሚበረታታ ባይሆንም አሁን ካለው የዋጋ ግሽበት አንፃር በነዳጅ ላይ የዋጋ ጭማሪ አድርጎ የዋጋ ግሽበቱ እንዳይጨምር ካልሆነ ናፍጣን ነጥሎ መደጎም ተገቢ የሚሆነው የናፍጣ ጭማሪ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ተፅዕኖ ከፍተኛ በመሆኑና የማይነካካው ነገር ስለሌለ ነው፡፡

የአገሪቱ የነዳጅ ዋጋ ሥሌትና አተማመንን በተመለከተ የጠራ ነገር ሊኖረው ይገባል በሚል የሚሞግቱ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ከአጠቃይ አሠራሩ በደንብ ሊፈተሽ ይገባል ብለዋል፡፡ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ ሊወሰዱ ይገባል ብለው ያስቀመጡት ሌላው የመፍትሔ ሐሳብ በአዋጅ ጭምር ይቋቋማል የተባለው የነዳጅ ፈንድ አሁን ላይ ምን እየሠራ እንደሆነም ታውቆ ከዚህ በኋላ አሠራሩን ግልጽ በማድረግ ከዚህ በኋላ ሊፈጠር የሚችለውን ክፍተት ሊደፍን ይችላል የሚል ግምታቸውንም ሰጥተዋል፡፡

መንግሥት ለነዳጅ ድጎማ አቁሜያለሁ ብሎ በይፋ ከስምንት ዓመታት በፊት ከገለጹ በኋላ፣ ይህንኑ ውሳኔውን ተከትሎ ስላቋቋመው ፈንድ ምንም የሚሰማ ነገር አለመኖሩ አሠራሩ ላይ ችግር እንዳለ የሚደርስ በመሆኑም ይህም መጣራት ይኖርበታል ብለዋል፡፡ የነዳጅ ፈንድ ሲቋቋም ዋነኛ ዓላማ ያደረገው ነዳጅ ሲቀንስ ገንዘብ ያጠራቅማል፡፡ ነዳጅ የሚመጣበት ዋጋ ስለሚቀንስ በቀነሰ ቁጥር ያሰባሰበውን ሀብት ዋጋው ሲጨምር ደግሞ ያጠራቀመውን እያወጣ የሚጠቁም በመሆኑ ዋጋውን ሊያረጋጋ ይችላል ተብሏል፡፡

አዋጅ መሠረት የተቋቋመው ፈንድ ወደ መሬት አለመውረዱ አንዱ ችግር ሲሆን፣ ፈንዱ እየሠራ ከሆነም በዚህ ወቅት የነዳጅ ዋጋ እንዳይጨምር መደጎም ነበረበት የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡  

የሰሞኑ የዋጋ ጭማሪ ከፍተኛ ነው የሚለው ላይ የተለያዩ አመለካከቶች ሲሰነዘሩም አሁን ከተደረገው ጭማሪ በተለይ የነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ ተደርጎ እንደነበር ያመለክታሉ፡፡ የአገሪቱን ያለፉት ዓመታት የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ በተደጋጋሚ የተከለሰ ሲሆን፣ አንድም ጊዜ የሚጨመረውን ያህል ዓለም አቀፍ ዋጋው ሲቀንስ ቅናሹን ያገናዘበ ዋጋ ቅናሽ ያለመደረጉን ነው፡፡

ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ጎልቶ የሚታየው ናፍጣ የችግርቻሮ የመሸጫ ዋጋው ከአምስት ብር በላይ የሆነው 1996 ዓ.ም. ነው፡፡ ከ1996 ዓ.ም. በኋላ የዓለም አቀፉ የነዳጅ ዋጋ ፈጠን ብሎ እየጨመረ የመጣበት ወቅት እንደነበር የሚገልጹ ሲሆን፣ ይህንኑ የዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥትም የነዳጅ የችርቻሮ የመሸጫ ዋጋን በተከታይ ከልሷል፡፡ በአዲስ አበባ ታኅሳስ 1999 ዓ.ም. በተደረገ የነዳጅ ዋጋ ክለሳ የአንድ ሌትር ናፍጣ የችርቻሮ የመሸጫ ዋጋ 6.75 ሳንቲም እንደነበር፣ በወቅቱ በአንድ ሌትር ናፍጣ ላይ ተደርጎ የነበረው የዋጋ ጭማሪ ከአንድ ብር በ50 ያነሰ ወደ 1.30 ሳንቲም አካባቢ ጭማሪ የተደረገበት እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በ2000 ዓ.ም. በተደረገ ማስተካከያና የአንድ ሌትር የናፍጣ ዋጋ በ1.85 ብር ጨምሮ 9 ብር ከ60 ብር ሲሸጥ ቆይቶ፣ መሀል ላይ በዚሁ ዋጋ የቆየው ዋጋ በኅዳር 2003 ዓ.ም. የአንድ ሌትር ናፍጣ መሸጫ ዋጋ ከአሥር ብር አልፎ 14 ብር ከ87 ሳንቲም እንዲሆን ተወሰነ፡፡ በዚሁ 2003 ዓ.ም. ባልተጠበቀ ሁኔታ በወራት ልዩነት ውስጥ ሳይጠናቀቅ በወራት ልዩነት እንደገና የዋጋ ማስተካከያ ተደርጎ በአንድ ሌትር የናፍጣ የችርቻሮ የመሸጫ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ተደርጎበት ወደ 22 ብር ከ27 ሳንቲም መሸጥ ጀመረ፡፡

በኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ ማሻሻያ ከተደረገ ረዥም ጊዜ መሆኑን የሚያመለክተው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ የነዳጅ ዋጋ ማሻሻያ የተደረገው ሚያዝያ 2011 ዓ.ም. ላይ ነው፡፡ ከዚያ ወዲህ ምንም ዓይነት የነዳጅ ዋጋ ማሻሻያ ያለመደረጉን አጽንኦት ይሰጥልኛል ይላል፡፡ በተጨማሪ ማብራሪያም ባለፉት ሁለት ዓመታት መንግሥት ወደ ሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ለነዳጅ ድጎማ ማድረጉን መንግሥት ወደ ኅብረተሰቡ የሚሄደውን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በድጎማ እያካካሰ መቆየቱንም ያስረዳል፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያው ግን ድጎማው እንዴት እንደሆነ ግልጽ አይደለም ይላሉ፡፡ ከተቋቋመው የነዳጅ ፈንድ የተወሰደ ነው ወይስ ከሌላ በሚል ሞጋች ጥያቄ ያነሳሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች