Sunday, January 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ነዳጅና አናዳጅ

የነዳጅ ዋጋ ጨመረ ሲባል ኢኮኖሚያችን ይደነግጣል ሸማች ከንፈሩን ይመጣል፣ ፀጉሩን ይነጫል፡፡ አጋጣሚውን ሠርግና ምላሻቸው የሚያደርጉ ስግብግቦች ደግሞ ያልተገባ ዋጋ ጭማሪ በማድረግ ገበያውን ያምሱታል፡፡ መንግሥት የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ ተደርጓል ብሎ ያውጅና ዞር ይላል፡፡ ይህ ለዓመታት ስንመለከተው የነበረው የግብይት ሥርዓታችን ክፉ መገለጫ ነው፡፡ ከሰሞኑም መንግሥት በነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ ማድረጉ እንደተሰማ ይህ የተጠበቀ ክፉ አመል ፍንትው ብሎ ወጣ፡፡ ወትሮም ሰበብ የሚፈልገው የአገራችን ግብይት ሥርዓት አሁን ላይ ሰበብ አግኝቶ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው መረጃ በቅጡ ሳይደርስ ስግብግብ ባለመደብሮች ነዳጅ ላይ ጭማሪ መደረጉ የሚሸጡት ዕቃ ላይ ዋጋ በመጨመር ዜናውን ይነግሩታል፡፡

በቀድሞው የነዳጅ ዋጋ ወደ አገር ውስጥ የገባ ምርት ነዳጅ ጨመረ በተባለ በሰዓታት ልዩነት አዲስ ዋጋ ተተክሎላቸው ያለ ይሉንታ መሸጥ ጀምሯል፡፡

በመደርደሪያ ላይ የከረመ ሸቀጥ ነዳጅ ጭማሪው ተሳብቦ እንደተለመደው በአቦ ሰጠኝ ዋጋቸው ቀጥሎ ሲሸጥ መች ይሆን ለህሊና፣ ለሕግና ለሥነ ምግባር ተገዥ ሆነን ሕዝብን የምናገለግለው የሚለውን ጥያቄ ዛሬም እንድናነሳ ያደርገናል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ የአገሪቱን የዋጋ ግሽበት ለማውረድና የኑሮ ውድነቱ እንዳይበረታ በሚፈለግበት ሰዓት፣ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ሰበብ በማድረግ አላስፈላጊ ዋጋ በመጨመር ግብይት እየተፈጸመ መሆኑ አደገኛ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

በእርግጥም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በግብይት ውስጥ የዋጋ ለውጥ መምጣቱ አይታበልም፡፡ እያንዳንዱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከነዳጅ ጋር የተያያዘ ከመሆኑ አንፃር በአገር ውስጥ ምርትም ሆነ በገቢ ዕቃዎች ላይ ዋጋ ሊጨምር የሚችልበት ዕድል ይኖራል፡፡ ችግሩ ግን የነዳጅ ዋጋው ጭማሪ በሸቀጦች ላይ ምን ያህል ዋጋ ሊያስጨምር ይችላል የሚለውን በአግባቡ ባለማስላትና አጋጣሚውን ተጠቅሞ ከልክ በላይ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉ ነው፡፡

ነገሩ አደገኛ የሚሆነውም እዚህ ላይ ነው፡፡ አሁን በገበያ ውስጥ እያየን እንዳለው ጥቂት የሚባሉ ሆድ አደሮች የነዳጅ ማደያዎች በአዲሱ ዋጋ ነዳጅ መቅጃ ማሽናቸውን ሳያስተካክሉ ተሯሩጠው የአገልግሎት ዋጋቸው ላይ በዘፈቀደ  የሚከተሉት ዋጋ ሊቀንስ ያልቻለውን የዋጋ ግሽበት ከሚታሰበውም በላይ በማድረግ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሊያደርጉብን ነው፡፡

አሁን በተደረገ የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ ሥሌት መሠረት አንድ ምርት ወደ ግብይት ሥፍራዎች ሲደርስ ምን ያህል ጭማሪ ሊኖረው ይችላል የሚለው ሳይታሰብ የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ አደገኛ የሚሆንበት ሌላም ማሳያ አለው፡፡ ይህም ማሳያ በአዲሱ የነዳጅ ዋጋ ምርቱ ሲገባ ደግሞ አሁን ላይ ያለአግባብ ያደረጉት ጭማሪ ላይ እንደገና ሌላ ጭማሪ ለማከል የማይመለሱ መሆናቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ የኑሮ ውድነቱን ምን ያህል እንደሚያባብሰው ኢኮኖሚውን ላይ የሚፈጥረው ጫና እንዲህ በቀላል የሚታይ አይሆንም፡፡

ወትሮም የኑሮ ውድነቱ እያጎበጠው ያለውን ሸማች የበለጠ ይጎዳዋል፡፡ ለአገራችን የዋጋ ግሽበት ምክንያት ተብለው የሚጠቀሱት በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ ቢታመንም ከሰሞኑ እንደምናየው ዓይነት ቅጥ የሌለው የግብይት ሥርዓታችን ስለመሆኑ ጭምር መገንዘብ አለብን፡፡

በተለይ እንዲህ ባለ ሰዓት በነዳጅ ጨመረ ሰበብ የሚሠራ ውንብድና የዋጋ ንረቱን ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ በመሆኑ ነገሮችን ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዳይወስዱ መንግሥት በብርቱ ሊያስብበት እንደሚገባ ብናምንም ምን ያህል ውጤት ማምጣት ይሆንበታል የሚለው ግን ያሳስባል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪውን በዚህ ሰዓት ማድረጉ እንደ አንድ ክፍተት የሚታይ መሆኑም መጠቀስ ይኖርበታል፡፡ በእርግጥም ያደረገው የዋጋ ማስተካከያ የዓለም ነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ ነው ከተባለ ነዳጅ ጥንቡን በጣለበት ሰዓት የተደረገ ማስተካከያ ሳይኖር ጨመረ በተባለበት ወቅት ዋጋ ለመጨመር መነሳቱ በራሱ ብዙ የሚያነጋግር ነው፡፡

እንደሚባለው መንግሥት ነዳጅ ሲደጉም እንደነበር የተጠቀሰ ቢሆንም፣ የዓለም ነዳጅ ዋጋ ሲጨምር እዚህ ማስተካከል የሚጠበቅ መሆኑ ባይካድም ከአሁን ያለውን የኑሮ ውድነት ከግምት በማስገባት ጭማሪውን ለተወሰነ ጊዜ ማዘግየት ይቻል እንደነበርም የብዙዎች አስተያየት ነው፡፡

ይህ ምን ያህል ታስቦበት የተተገበረ እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ተደርጎበት መተግበር ከጀመረ በኋላ ሊመጣ የሚችለውን ችግር መስመር ማስያዙ ላይ ግን መሥራት ድርብ ኃላፊነት እንዳለበት ያመለክታል፡፡

ነዳጅ ዋጋ ተጨመረ ከተባለበት ዕለት ጀምሮ ገበያውን ለማጋልና አላስፈላጊ የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉትን ተቆጣጥሮ አደብ በማስገዛትና ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኑሮ ውድነቱ ሊያባብሱ የሚችሉ ተግባራትን በመከታተል መፍትሔ ሊያበጁለት ግድ ነው፡፡

በዚህ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ሊከሰት የሚችለውን የዋጋ ግሽበትና ኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ ከግምት በማስገባት የማይሠራ ከሆነ ደግሞ በነዳጁ ላይ ያረገው የዋጋ ጭማሪ በመቀነስ  ከሚችለው ጥቅም በላይ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላልና መንግሥት ዋጋ ጨምሬያለሁ ብቻ ሳይሆን ዋጋ ስጨምር የሚፈጠረውን ችግርም መፍትሔ ይሆናል ያለውን ዕርምጃ የመውሰድ ግዴታ አለበት፡፡ ከነጣቂ ነጋዴዎች ሸማቹን መገላገል ብቻ ሳይሆን በጭማሪው ሳቢያ ይበልጥ ተጎጂ የሚሆኑትን የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚያግዝ አሠራር ሊዘረጋ ይገባል፡፡

ነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አናዳጅ የሚሆነውም ያለአግባብ ከልክ በላይ ዋጋ ለመጨመር ሰበብ የሚፈልጉ ወገኖች በአጋጣሚው ያልተገባ ዋጋ መትከላቸው ሲሆን፣ ይህንን ያለመቆጣጠር ደግሞ በችግሩ እሳት ላይ ነዳጅ ማርከፍከፍ ይሆናል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት