Friday, April 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ማዳበሪያ ማምረትና ግብይት ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለውይይት ቀረበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የግብርና ሚኒስቴር የአፈር ማዳበሪያ ማምረትና ግብይት የሚመለከት የተሻሻለ የሕግ ማዕቀፍ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መርቶ እየተገመገመ እንደሚገኝና በቅርቡም ይፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታወቀ፡፡

ይህ የተገለጸው የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የተመሠረተበትን አምስተኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን የተለያዩ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ ኃላፊዎች በተገኙበት፣ የካቲት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ገላን በሚገኘው አትላስ ሪዞርት ባከበረበት ወቅት ነው፡፡

በበዓሉ ላይ የታደሙት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሤ፣ በግብርና ሚኒስቴር ከተቀረፁ የሪፎርም አጀንዳዎች ለምርትና ምርታማነት አንዱና ወሳኙ ቴክኖሎጂና ግብዓት አቅርቦት ነው በማለት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ሚኒስቴሩ ለአብነት ዘርፉን ወደፊት ለማምጣትና ለመደገፍ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት መሣሪያዎች ከታክስ ነፃ እንዲገቡ ማድረጉ ይታወሳል ያሉት ወ/ሮ ዓይናለም፣ የእንስሳት፣ የሰብልና ሌሎችን ጨምሮ 524 ግብዓቶች በአሁኑ ጊዜ ከታክስ ነፃ ወደ አገር እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ከአፈር ማዳበሪያ ግዥ ጋር በተገናኘ ከ20 ዓመታት በፊት የተዘጋጀ አዋጅ እንዳለ ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ ነገር ግን አዋጁ ማገልገል ካለበት ጊዜ በላይ ማገልገሉን፣ በውስጡም በአሁኑ ወቅት የሌሉ ተቋማትን እንዳሉ አድርጎ የሚያይ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከሦስት ሚሊዮን ያላነሰ ኩንታል ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ በምታስገባበት ጊዜ የነበረ አዋጅ እንደሆነ ያስታወሱት ወ/ሮ ዓይናለም፣ አገሪቱ በዚህ ወቅት ከ18 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ እያስመጣች በመሆኑ ይህ አዋጅ ወቅታዊውን የአገሪቱን ሁኔታ ከግንዛቤ በማስገባት መሻሻል አለበት ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደ ማሪያም በበኩላቸው፣ የአፈር ማዳበሪያ ግብይት ሥርዓቱ ከረዥም ዓመት በፊት በወጣ የሕግ ማዕቀፍ ሲከናወን መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ በመሆኑም አሁን አገሪቱ ልትደርስ ካሰበችበትና እየሄደችበት ካለው የግብርና ዘርፍ እንቅስቃሴ ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም ብለዋል፡፡ ወደፊት አገሪቱ በውጭ ማዳበሪያ ግዥ ላይ ብቻ መጠመድ ስለሌለባት፣ ማዳበሪያ በአገር ውስጥ ማምረት ይጠበቅባታል ነው ያሉት አቶ ክፍሌ፡፡ ይህንን ለማሟላት ደግሞ ብዙ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ማለትም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ዋነኞቹ የሆኑትን ክልሎች፣ ዋነኛው የጉዳዩ አስተባባሪ የሆነውን ግብርና ሚኒስቴር፣ በማጓጓዙ ላይ ድርሻ ያለውን የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት፣ እንዲሁም የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ያካተተ የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻል አስፈልጓል ብለዋል፡፡

የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የማዳበሪያ ማምረትና ግብይት አዋጅ ተዘጋጅቶ በሚመለከታቸው አካላት ታይቶ አሁን ወደ ማጠናቀቁ ሒደት ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ አገራዊው ምርጫ ከተከናወነ በኋላ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሻሻለው አዋጅ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተወካይ፣ ‹‹ቋሚ ኮሚቴው የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ይከታተላል፣ የሚሻሻል የሕግ ማዕቀፍ ካለ ያሻሽላል፣ አዲስ የሚወጣ ሕግ ካለ ያወጣል፣ የወጡ ሕጎችን ተፈጻሚነት ይከታተላል፤›› ብለው፣ የመንግሥት ተቋማት በሥራቸው ሒደት የሚያጋጥሟቸው ችግሮች የማይፈቱላቸው ከሆነ ጫናዎች በመደራረብ የተቋቋሙላቸውን ዓላማ እንዳይተገብሩ ይዳርጋልና ጥንቃቄ ያስፈልጋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ በዚህም ቋሚ ኮሚቴው በሚኒስትሮች ምክር ቤት እየታየ ያለውንና ከማዳበሪያ ጋር የተያያዘውን የሕግ ማዕቀፍ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ሥራ ላይ እንዲውል ቋሚ ኮሚቴው አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች