ለመጪው ምርጫ ዝግጅት ሲደረግ ከወዲሁ ሊታሰብባቸው የሚገቡ ጉዳዮች በርካታ ቢሆኑም፣ አንዱና መሠረታዊው ጉዳይ የመንግሥትና የፓርቲ ሚና መደበላለቅ ነው፡፡ ይህ ችግር በኢትዮጵያ ሥር የሰደደ በመሆኑ መነጋገር የግድ ይሆናል፡፡ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ትልቁ ፀጋ ትናንት ተቃዋሚ የነበረው ዛሬ ገዥ፣ ዛሬ ገዥ የሆነው ደግሞ ነገ ተቃዋሚ የሚሆንበት ነፃና ፍትሐዊ ዓውድ መፍጠሩ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሥልጣን የያዘ ገዥ ፓርቲና መንግሥት በመካከላቸው በጉልህ የተሰመረ ድንበር ይኖራቸዋል ማለት ነው፡፡ በእርግጥ ሥልጣን ላይ ያለ ፓርቲ ከሌሎች ሻል ያለ ተጠቃሚነት አለው ቢባል እንኳ፣ ገደቡ የተወሰነና በሕግ መመራት ስላለበት የመንግሥትና የፓርቲ ሚና መደበላለቅ የለበትም፡፡ ገደቡ ሲጣስና ገዥው ፓርቲ የአውራነት ባህሪ ተላብሶ ሁሉም የመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ ገብቶ ሲያንጎዳጉድ ግን፣ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት አለ ለማለት አይቻልም፡፡ ማሰብም ይከብዳል፡፡ የመንግሥት ሹመቶች በሙሉ ፖለቲካዊ ሲሆኑና መዋቅሮቹ በካድሬዎች ሲሞሉ መንግሥትና ፓርቲን ለመለየት ያዳግታል፡፡ በዚህም ሳቢያ ስለዴሞክራሲና ስለሰብዓዊ መብቶች፣ ስለፍትሐዊነትና ስለእኩልነት መነጋገር በፍፁም አይሞከርም፡፡ ኢትዮጵያ የምርጫ ዋዜማ ላይ ሆና ይህንን መሠረታዊ ጉዳይ አንስቶ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ መንግሥትና ገዥው ፓርቲ መደበላለቅ ስለሌለባቸው፡፡
እንደሚታወቀው በአገሪቱ እስካሁን በተካሄዱ አምስት ብሔራዊ ምርጫዎች ገዥ ፓርቲ የነበረው ኢሕአዴግ፣ ከአጋሮቹ ጋር በመሆን ፓርላማውን በበላይነት ተቆጣጥሮት ነበር፡፡ አልፎ አልፎ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አነስተኛ የፓርላማ መቀመጫዎችን የሚያገኙባቸው አጋጣሚዎች የነበሩ ቢሆንም፣ በተከታታይ በተካሄዱት ሁለት ምርጫዎች ነገሮች ተለውጠዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አንድም ተቃዋሚ ፓርቲ የሌለበት ፓርላማ ነው ያለው፡፡ ምንም እንኳ አሁን ነገሮች ተለዋውጠው እውነተኛ ምርጫ ለማድረግ በማለም ቀጠሮ ቢያዝም፣ በአገሪቱ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት በሚፈለገው ደረጃ ካልሰፈነ የአንድ ፓርቲ የበላይነት መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ይኼ ደግሞ ለዚህች አገር አስፈላጊ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ቋንቋዎች፣ እምነቶች፣ ባህሎች፣ አስተሳሰቦች፣ ፍላጎቶችና የመሳሰሉት አገር ናት፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የተለያዩ ፖለቲካዊ አመለካከቶች የሚንፀባረቁባት ናት፡፡ እነዚህ ፍላጎቶች ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መወከል አለባቸው፡፡ ይህ ውክልና የሚገኘው ደግሞ በእውነተኛ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ምርጫ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ቀና መንገድ ላይ መጓዝ ሲቻል ከጠብና ከግጭት ይልቅ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዕውን ይሆናል፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር አገር የሚመራ ሥርዓት ይፈጠራል፡፡ የመንግሥትና የፓርቲ ሚናን መደበላለቅ ለአገር አይበጅም፡፡
የመንግሥትና የፓርቲ ሚና እየተደበላለቀ የሚያስቸግረው ግን፣ ለጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጀርባ በመሰጠቱ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ በየቦታው የሚመደቡ የፖለቲካ ሹማምንት ግልጽነትና ተጠያቂነት ስለሌለባቸው ያሻቸውን ያደርጋሉ፡፡ ባለሙያዎች በተገቢው ቦታ ስለማይመደቡ የመንግሥት ተቋማት አሠራርና ብቃት ከደረጃው የወረደ ይሆናል፡፡ ለተቋማት ግንባታ ትኩረት ካልተሰጠ ሕገወጥነት ይስፋፋል፡፡ ሌብነት ልማድ ይሆናል፡፡ ሕዝብ ተቆጥቶ ጥያቄ ሲያቀርብ አዳማጭ ስለሌለ አመፅ ይቀሰቀሳል፡፡ ለንፁኃን ዕልቂትና ለንብረት ውድመት መዳረግ ይመጣል፡፡ ይህም የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ ግርግር በኋላ የተጠራቀሙ ችግሮችን ለመፍታት መውደቅና መነሳት ይጀመራል፡፡ ድርጊቶች ሁሉ በዕቅድና በጥናት ላይ ስለማይመሠረቱ ለተጨማሪ ስህተቶች በር ይከፈታል፡፡ እንደተለመደው ተግባር የማይጎበኘው የመፈክር ጋጋታ የዕለት ተዕለት ሥራ ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያት መንግሥትና ሕዝብ እንደገና ሆድና ጀርባ ይሆናሉ፡፡ መሬት ላይ የሚታየው ሌላ የሚሠራው ሌላ ይሆንና ወደተለመደው አዙሪት ይገባል፡፡
ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ወደ ብልፅግና ፓርቲነት ተቀይሮ በአዲስ መንፈስ ለመጪው ምርጫ ዝግጅት ሲያደርግ፣ በዘመነ ኢሕአዴግ የተፈጸሙ አሳፋሪ ድርጊቶችን ይደግማል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታዩ አዝማሚያዎቹ ካልታረሙ ግን ችግሩ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እየቀረቡለት ያሉ አቤቱታዎች መብዛት፣ ከዚህ ቀደም ከተፈጸሙ ስህተቶች ወይም ሆን ተብለው ከሚፈጸሙ ድርጊቶች ለመታረም አለመፈለግን ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ ገዥው ፓርቲ የራሱ ርዕዮተ ዓለም፣ የሚመራበት ፖሊሲና ስትራቴጂ፣ ፕሮግራምና ደንብ ግልጽ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ አባላቱ በሚገባ መረዳታቸው የግድ መሆን አለበት፡፡ እንዲሁም ሰሞኑን ይፋ ያደረገው የምርጫ ማኒፌስቶው ግልጽና ጥርት ከማለት በላይ፣ አባላቱ በሚገባ ተረድተውና ሥርዓት ይዘው መፎካከራቸው ሊታወቅ ይገባል፡፡ ፓርቲውም ለየትኛው የኅብረተሰብ ክፍል ወገንተኝነቱ እንደሚያደላ የሚያሳይ ንድፈ ሐሳባዊ ትንተና ያስፈልገዋል፡፡ ይህ ትልቅና ግዙፍ ፓርቲ በዚህ ደረጃ ላይ ካልተገኘ፣ እንደተለመደው የፓርቲና የመንግሥትን ሚና በማደበላለቅ ‹የሞትንም እኛ ያለንም እኛ› መሰል መፈክር የሚያስተጋባ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ትናንት የአብዮታዊ ዴሞክራሲና የልማታዊ መንግሥት መፈክር አስተጋቢ የነበሩ ካድሬዎቹና አባላቱ፣ ዛሬ ደግሞ ከትናንቱ የሚለዩበትን ቀለምና መለያ ይዘው ሕዝብ ፊት መቅረብ ካልቻሉ ግራ አጋቢ ነው፡፡ እርግጥ ነው ይህ ችግር የበርካቶቹ የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መገለጫ ነው፡፡ ብዙዎቹ የራሳቸው መለያ ሳይኖራቸው በደመነፍስ እንደሚንቀሳቀሱ የታወቀ ነው፡፡
በመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ ወትሮም የሚታወቀው የግልጽነትና የተጠያቂነት መጥፋት ነው፡፡ በስንት መከራ የሚገኝ የመንግሥት በጀት በሕጉ መሠረት መጠቀምና ማወራረድ እያቃተ፣ የአገር አንጡራ ሀብት መባከኑ የተለመደ ነው፡፡ የመንግሥት ፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ የሚታዩ አሳሳቢ ችግሮች፣ የፓርቲና የመንግሥት መደበላለቅ የፈጠራቸው ችግሮች መሆናቸው ብዙ የተባለበት ነው፡፡ የአገር ሀብትን ያለ ተጠያቂነት መበተንና የባለሙያና የካድሬ ዳር ድንበር በአግባቡ አለመሰመሩ፣ በኦዲትና በሪፖርት አቀራረብ ወቅት ከሚሰሙ ስሞታዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡ የመንግሥት በጀት ለታለመለት ዓላማ አልዋለም ሲባል ሕግ አልተከበረም ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ማናለብኝነት እንዳለ አስረግጦ ያሳያል፡፡ ይህ ችግር አፍጥጦ የሚታየው ደግሞ በተደጋጋሚ ስማቸው በሚጠራ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ከዚህ ቀደም እንደነበረው ዓይነት በመንግሥት ሀብት እንደፈለገ ለመጠቀም፣ የመንግሥት ሠራተኞችን በማስገደድ የዓላማው አስፈጻሚ መሣሪያ እንዲሆኑ ማድረግ ውስጥ እንዳይገባ ከፍተኛ ቁጥጥር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የማያስችል፣ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል መተማመን እንዲጠፋ የሚያደርግና አገሪቱንም አደጋ ላይ የሚጥል ነው፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት ሲጠፋ ውጤቱ አደገኛ ነው፡፡ የመንግሥትና የፓርቲ ሚና መደበላለቅ ከዚህ የከፋ አደጋም ያስከትላል፡፡
በሌላ በኩል ዛሬ ገዥ ፓርቲ ሆኖ ሥልጣን ላይ ያለ አካል፣ ነገ በምርጫ ተሸንፎ ለሌላ ፓርቲ ሥልጣኑን በሕዝብ ምርጫ እንደሚያስተላልፍ መገንዘብ አለበት፡፡ በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ሥልጣን የሚያዘው በሕዝብ ይሁንታ እንደሆነ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ ይህ ድንጋጌ በተግባር የሚገለጸው ደግሞ ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ነፃ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ፣ ሲቪክ ማኅበራት እንዲያብቡ፣ ሕዝብ በነፃነት ሐሳቡን እንዲገልጽና የፈለገውን ፓርቲ እንዲመርጥ የሚያስችል የፖለቲካ ዓውድ እንዲፈጠር ማድረግ አለበት፡፡ በዚህ ዘመን የአንድ ፓርቲ አውራነትን ለመቀበል የሚሻ ትውልድ የለውም፡፡ የአገሪቱ ብዝኃነት የሐሳብ ልዩነቶችንም በነፃነት ማስተናገድ አለበት፡፡ መንግሥታዊ መዋቅሮች ከፖለቲካ ፓርቲ ተፅዕኖ መላቀቅ አለባቸው፡፡ የአገር መከላከያ፣ ፖሊስና ሌሎችም የፀጥታ ኃይሎች የአገር አገልጋዮች እንጂ የአንድ ፓርቲ ወገንተኞች አለመሆናቸው በተግባር መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ የሙያና ሕዝባዊ ማኅበራት በነፃነት ሊደራጁ ግድ ይላል፡፡ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚፈጠረው ኃላፊነታቸውንና ግዴታቸውን በሚገባ በተገነዘቡ ዜጎች ተሳትፎ ስለሆነ መንቃት፣ መደራጀትና ብሔራዊ ግዴታን በሕጉ መሠረት መወጣት መቼም የሚታለፍ አይሆንም፡፡ አገር ሰላም ሆና ሥልጡን ፖለቲካ ባህል የሚሆነው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር የምትተዳደር አገር መኖሯ የሚጠቅመው አሁን ላለውም ሆነ ወደፊት ለሚመጣው ትውልድ ነው፡፡ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች በዚህ አገር ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ የበኩላቸውን ይወጡ፡፡ ጠብ፣ ግጭትና አላስፈላጊ ድርጊቶች አገርና ሕዝብ ስለሚጎዱ ማንም ተጠቃሚ አይሆንም፡፡ ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ዕውን መሆንና ለነገዋ ኢትዮጵያ ህልውና ሲባል ዴሞክራሲ የምር ይሁን፡፡ ለዚህ ደግሞ የመንግሥትና የፓርቲ ሚና በፍፁም መደበላለቅ የለበትም፡፡ ካልሆነ ግን በዴሞክራሲ መቀለድ ነው የሚሆነው!