የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እንደ አዲስ ለማደራጀትና በአሠራሩ ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ለማድረግ ያስችላል የተባለውን ጥናትና አደረጃጀት ለማሰናዳት የወጣውን ዓለም አቀፍ ጨረታ፣ ማኬንዚ የተባለው የአሜሪካ ኩባንያ ከተወዳዳሪዎቹ ብልጫ ያለው ውጤት በማምጣት አሸናፊ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አጠቃላይ አሠራርን በመለወጥ ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪ ለመሆን ያስችለዋል በተባለው ጥናትና አደረጃጀት በወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ፣ ከ39 ኩባንያዎች ተሳትፈው የነበሩ ሲሆን፣ ከእነዚህ ኩባንያዎች ለመጨረሻ ውድድር አራት ኩባንያዎች ቀርበው እንደነበር ይታወሳል፡፡
አራቱ ኩባንያዎች የመወዳደሪያ ሰነዳቸውን ካስገቡ በኋላ በተገኘው ውጤት መሠረት ማኬንዚ ባቀረበው የፋይናንስ መጠንና የቴክኒክ ምዘና፣ ከሌሎቹ ብልጫ አግኝቶ አሸናፊ ሊሆን መቻሉን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በዚሁ ውጤት መሠረት የባንኩ ማኔጅመንት ከአሸናፊው ኩባንያ ጋር ተጨማሪ ድርድር በማድረግ፣ በይፋ የኮንትራት ስምምነት በመፈረም ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡
ማኬንዚ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ቀጣይ ፍኖተ ካርታና የወደፊት አቅጣጫውን የሚያመላክተውን ጥናት በጥቂት ወራት ውስጥ በማሰናዳት ካቀረበ በኋላ፣ ባንኩ የሚመራበት አዲሱ አሠራር ተግባራዊ መሆን ይጀምራል ተብሏል፡፡
እንደ ምንጮች ገለጻ ማኬንዚ የጨረታው አሸናፊ የሆነው በሁለት ሚሊዮን ዶላር መጫረቻ ዋጋ ነው፡፡ ከማኬንዚ ቀጥሎ ያለውን ውጤት ያገኘው ደግሞ ፒደብሊውሲ ወደ ስድስት ሚሊዮን ዶላር አቅርቦ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህም ማኬንዚ በሰፊ ልዩነት አሸናፊ ሊሆን መቻሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡
አሸናፊው ኩባንያ ከባንኩ ጋር በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ይፈራረማል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ከፊርማው በኋላ በይፋ ሥራውን ይጀምራል፡፡
ባንኩ ባወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ ከማኬንዚ ሌላ ለመጨረሻው ውድድር ቀርበው የነበሩት ኬፒኤምጂ፣ ዲሎይትና ፒደብሊውሲ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ሙሉ ለሙሉ ይለውጣል የተባለው ጥናት የእስካሁን አሠራሩን በመፈተሽ አዲስ አሠራር እንዲዘረጋ የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡ የብድር አሰጣጡን ጨምሮ ሌሎች የባንኩን አገልግሎቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተሠራባቸው ባሉ አሠራሮች የሚተካ ሲሆን፣ ሙሉ አደረጃጀቱንም እንደሚቀይር ታምኗል፡፡ ሌላው ቀርቶ የባንኩ የቦርድ አባላት አሰያየምና የማኔጅመንት አባላት ምደባ እንዴት መሆን እንደሚኖርበት በግልጽ የሚያሳይ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የአገሪቱ ትልቁ ባንክ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለ80 ዓመታት በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ በመቆየት ይታወቃል፡፡
የንግድ ባንክ አደረጃጀትና አሠራር ለመለወጥ ጥናት የሚያደርገው ማኬንዚ አሜሪካ ውስጥ እ.ኤ.አ. በ1926 የተመሠረተ ሲሆን፣ የማኔጅመንት አማካሪ በመሆን ከፍተኛ ልምድ ማካበቱ ይነገርለታል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2018 በወጣ መረጃ መሠረት 27 ሺሕ ያህል ሠራተኞች አሉት፡፡ ዓመታዊ ገቢውም አሥር ቢሊዮን ዶላር ይገመታል፡፡