የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ከ40 ሺሕ በላይ ሴት ሥራ ፈጣሪዎች ተጠቃሚ ለማድረግ ከሄሎ ማርኬት ጋር መስማማቱን አስታወቀ፡፡
ሁለቱ ተቋማት የካቲት 5 ቀን 2013 ዓ.ም. በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ሴት ሥራ ፈጣሪዎች አገልግሎታቸውን በማስፋት ለማኅበረሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሴቶች ኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ዮሐንስ ሰሎሞን እንደገለጹት፣ የአምራቾችና አገልግሎት ሰጪዎች አንዱና ዋነኛ ጥረት በርካታ ደንበኞችን በማፍራት የገበያ አድማሳቸውን ማስፋት በመሆኑ ይህ ስምምነት በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡
የሴት ኢንተርፕረነሮች ገቢ በማሳደግና የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅማቸውን በማጎልበት እንዲሁም የገበያ መድረኮችን በማመቻቸት በኩል ሰፊ ሥራ እየተሠራ መሆኑን አቶ ዮሐንስ አስረድተዋል፡፡
አምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚፈልጉትን የማምረቻ መሣሪያ መግዣ ብድር እንዲያገኙ ለማድረግ ከአምስት የካፒታል አቅራቢ ኩባንያዎች ጋር የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረሙ መሆኑን የገለጹት አስተባባሪው፣ ይኼም አምራቾች የዘመናዊ ማምረቻ መሣሪያዎች ባለቤት በመሆን የተሻለና ጥራቱን የጠበቀ ምርት ወደ ገበያ እንዲያቀርቡ የሚረዳቸው ይሆናል ብለዋል፡፡
በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ኢንተርፕረነሮች አውቀውና ተዘጋጅተው ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ የሥልጠና አገልግሎት የሚሰጣቸው መሆኑንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
ከዓለም ባንክ በተገነ ብድር በመንግሥት የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት ለ161 ከተሞች ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ተናግረዋል፡፡
በቅርቡም በተወካዮች ምክር ቤት አማካይነት ለብድር አገልግሎት የሚውል 100 ሚሊዮን ዶላር መፅደቁንና ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ሴት ኢንተርፕረነሮች ያልተቋረጠ የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ የሚረዳ ከመሆኑም በላይ፣ መንግሥት ተመላሹን የብድር ገንዘብ መልሶ ለብድር እንዲውል (Revolving Fund) በማድረግ እየተተገበረ ይገኛል፡፡
በፌዴራል የከተሞች ሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ስር ከሚገኙት ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው የሴቶች ኢንተርፕሪነርሽፕ ልማት ፕሮጀክት፣ በኢትዮጵያ መንግሥትና በዓለም ባንክ የብድር ድጋፍ የተጀመረና በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ለተሰማሩ ሴት ኢንተርፕረነሮች፣ የብድርና የሥልጠና አገልግሎት ለማስተባበርና አገልግሎቱን ለመስጠት የተደራጀ ፕሮጀክት ነው፡፡