የመን የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ከተዘፈቀች ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ እነዚህ ዓመታት በተለይ ሴቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ፍዳን የቆጠሩበት ነው፡፡ የእርስ በርስ ግጭት ለየመን ብርቅ ባይሆንም፣ ጦርነቱ የለየለት የሳዑዲ መራሹ ጦር እ.ኤ.አ. በ2015 ጣልቃ ሲገባ ነበር፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የተሰጠውን መንግሥት በመደገፍ ለቀድሞ የየመን ፕሬዚዳንት ዓሊ አብዱላህ ሳላህ የወገኑትን ሁቲ ቡድኖች መውጋት የጀመረው የሳዑዲ መራሹ ጦር ለየመን ሰላምን ሳይሆን የለየለትን ጦርነት ነበር ያጎናፀፈው፡፡
የየመን ደም አፋሳሽ ጦርነት ከዓረቡ ዓለም በድህነቷ ለምትጠቀሰው አገር ሕዝብ አሁንም ፈተናነቱ ቀጥሏል፡፡ ጦርነቱ በተጀመረ በሦስት ዓመት ብቻ ከ10 ሺሕ ያላነሱ የመናውያን ተገድለዋል፡፡ ከ40 ሺሕ በላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችም ተፈናቅለዋል፡፡
ጦርነቱ ከተጀመረበት ከ2015 ወዲህ ደግሞ ከ100 ሺሕ በላይ ተገድለዋል፡፡ 12 ሺሕ ያህል ንፁኃን የተገደሉትም ቀጥታ እነሱ ላይ በተሰነዘረ ጥቃት እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) መረጃ ያሳያል፡፡
ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግርን ባለመቀበል በ2011 የተጀመረው የየመን ግጭት ሕፃናትን ይበልጡኑ ጎድቷል፡፡ ዛሬ ላይ በየመን ከአምስት ዓመት በታች ከሚገኙ ሕፃናት 400 ሺሕ ያህሉ በምግብ እጥረት ምክንያት ሞት ከፊታቸው ተደቅኗል ሲል ተመድ ሰሞኑን አስታውቋል፡፡
ከአምስት ዓመት በታች ያሉ 2.3 ሚሊዮን ያህል የየመን ሕፃናት ለከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ተጋልጠዋል ሲልም ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡ የሕፃናት መራብና በረሃብ ምክንያት ከሞት አፋፍ መድረስ የቤተሰቦቻቸውን ፈተና ያሳያል ያለው የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ ቤተሰቦቻቸው ችግር ውስጥ በመሆናቸው ምክንያት ለሕፃናቱ ቶሎ ምላሽ ካልተሰጠ በየቀኑ በርካታ ሕፃናት ይሞታሉ ብሏል፡፡ በረሃብ ምክንያት ከሞት አፋፍ የሚደርሱ ሕፃናት ቁጥር ዓምና ከነበረበት በ22 በመቶ መጨመሩም ተገልጿል፡፡
እስካሁንም 85 ሺሕ ሕፃናት በረሃብ፣ በበሽታና በጦርነቱ ሞተዋል፡፡
1.3 ሚሊዮን ነፍሰ ጡር አሊያም የሚያጠቡ እናቶችም በ2021 ለከፋ ረሃብ ይጋለጣሉ ተብሏል፡፡ 24 ሚሊዮን ከሚጠጉት የመናውያን 80 በመቶ ያህሉ ቀርበዋልም ተበሏል፡፡
በየመን መረጋጋትና ፀጥታ ካልሰፈነ የገበሬዎችንም ሆነ የነዋሪዎችን ሕይወት መታደግ እንደማይቻል ሕዝቡም ለከፋ ረሃብና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንደሚጋለጥ ደግሞ ፋኦ አስታውቋል፡፡
ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ማድረግ ተስኗቸው ጎራ በመለየት እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ ሲፋለሙ የቆዩት በታማኝ ወታደሮቻቸውና በሁቲ ቡድን የሚደገፉት የቀድሞ የየመን ፕሬዚዳንት ዓሊ አብዱላህ ሳላህና በወቅቱ ሥልጣን የተረከቡት የአብድራቡህ ማንሱር ሃዲ ደጋፊዎች የፈጠሩት የእርስ በርስ ጦርነት ዛሬ ላይ የመንን አፈራርሷታል፡፡ የመናውያን እንዲሞቱ፣ እንዲሰደዱና በሰቆቃ ውስጥ እንዲኖሩ አስገድዷል፡፡
አብዱላህ ሳላህን ይደግፋሉ የሚባሉትን ሁቲዎች ለመምታት የተቋቋመውና ኩዌት፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬት፣ ባህሪን፣ ግብፅ፣ ሞሮኮ፣ ጆርዳን፣ ሱዳንና ሴኔጋል ያሉበት በሳዑዲ የሚመራው ጥምር ጦር በየመን የከፋ ምስቅልቅል አድርሷል፡፡
በሳዑዲ ዓረቢያ የሚመራውን ጥምር ጦር የሚደግፉት አሜሪካ፣ እንግሊዝና ፈረንሣይ ለሳዑዲ ጥምር ጦር መሣሪያ የሚያቀርቡ ሲሆን፣ የደኅንነት ሥራዎችንም ያከናውናሉ ሲል አልጀዚራ አስፍሯል፡፡ አሜሪካ ደግሞ የቡድኑ አባላት በአሸባሪዎች መዝገብ አስፍራለች፡፡
ሆኖም ሳዑዲ መሩ ጦርም ሆነ የአሜሪካ ሁቲዎችን በአሸባሪነት ማስቀመጥ ለየመን መከራን እንጂ ሰላምን አላመጣም፡፡ ተመድን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትም 80 በመቶ የየመን ዜጎች ለረሃብ ተጋልጠዋል ሲሉ ጦርነቱ እንዲቆም መወትወት ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡
የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን ሊያስረክቡ ቀን ሲቀራቸው፣ በየመን ሁቲዎች ላይ ባሳለፉት ውሳኔ ወደ የመን ምግብና ማንኛውም አስፈላጊ ዕርዳታ እንዳይደረግ ማገዳቸውን ተከትሎም፣ ዓለም አቀፍ መንግሥታት ባደረጉት ውትወታ አሜሪካ በየመን ሁቲ ላይ ተጥሎ የነበረውን ገደብ አንስታለች፡፡
አልጀዚራ እንደዘገበው፣ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በየመን ለዓመታት የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆምና በአገሪቱ የተከሰተውን የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ለመቀልበስ አሜሪካ በየመን ላይ ያላትን የቀደመ ፖሊሲ ቀልብሳለች፡፡ ይህን የምታደርገውም በዲፕሎማሲያዊ መንገድ በየመን ውስጥ እየተካሄደ ያለውን የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም ነው፡፡
የመንን ለከፋ ረሃብ አጋልጧል የተባለው የአሜሪካ ውሳኔ ከትናንት የካቲት 9 ቀን ጀምሮም ተነስቷል፡፡ ባይደን ከዚህ ውሳኔ ባፋጣኝ የደረሱትም በዓለም አሰቃቂ ሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ የገባችውን የመን ለመታደግ ነው ተብሏል፡፡
ሆኖም በየመን ሰላምን፣ ደኅንነትንና መረጋጋትን ያፈረሱ በተባሉ ሦስት የሁቲ ቡድን መሪዎች ላይ የጣለችው ገደብ አልተነሳም፡፡