Tuesday, March 5, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልበባህላዊ ሙዚቃ አሻራውን ያኖረው ‹‹ባለዋሽንቱ››

በባህላዊ ሙዚቃ አሻራውን ያኖረው ‹‹ባለዋሽንቱ››

ቀን:

ፍቅር እስከ መቃብር ትረካ በሕዝብ ልቦና እንዲታወስ ከሚያደርጉት ውስጥ አንዱ ዋሽንቱ ነው፡፡ በዋሽንቱ የሚወጣው ድምፅ የፍቅር እስከ መቃብርን ክንውኖች በትውስታ  እንዲመለሱ እንደሚያደርግ፣ እንዲያውም አንዳንዶች ትረካው ነፍስ እንዲዘራበት ያደረገው ልብ ሰርሳሪው የዋሽንቱ ድምፅ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

የዚህን ትረካ ማጀቢያ የዋሽንት ድምፅ የተጫወቱት ‹‹የዋሽንቱ ንጉሥ›› ዮሐንስ አፈወርቅ (1938-2011) ነው፡፡  በትረካው ከያኒው ወጋየሁ ንጋቱ በድምፁ ከማስዋቡ በተጨማሪ የዋሽንቱ ድምፅ ደግሞ በእጅጉ ትረካውን በብዙኃን ልብ ውስጥ እንዲቀር ማድረጉ ይወሳል፡፡
በቅርቡ በድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ‹‹ማር እስከ ጧፍ›› መግቢያውን ያስዋበው በዋሽንቱ ንጉሥ ነው፡፡

በዚህም ሙዚቃ በደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁ የተጻፈውን ፍቅር እስከ መቃብር ትረካ ወደ ኋላ መለስ ብሎ እንዲታሰብ አድርጎታል፡፡ በድርሰቱ ውስጥ ያሉት ‹‹ሰብለ ወንጌል›› እና ‹‹በዛብህ›› ከዋሽንቱ ድምፅ በበለጠ ያዘነላቸው ያለ አይመስልም፡፡ እንዲሁ የማጀቢያ ድምፁ ሲሰማ የእነዚህን ገፀ ባህርያትና ማንኩሳን ጨምሮ በድርሰቱ የተገለጹ መቼቶች በዓይነ ህሊና ውልብ ያስብላል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ባለዋሽንቱ ዮሐንስ አፈወርቅ ከእነዚህ ሁለቱ ሥራዎች ባሻገር በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ያለ መሰልቸትና ያለ መድከም በዋሽንት ሲጫወት ረዥም ዓመታት አስቆጥሯል፡፡

ዮሐንስ አፈወርቅ ከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ በትውፊታዊ የትንፋሽ መሣሪያ ሲጫወት መቆየቱን፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዴሚ ባለሙያ ፍሬ ሕይወት ባዩ (/)፣ መሰንበቻውን አካዴሚው  ‹‹ዘፈንና ሥነ ቃል ከሀገራዊ ፋይዳ አንፃር›› በሚል ርዕስ ባዘጋጀው ዓውደ ጥናት ላይ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ማጥናት ለሚፈልጉ መነሻ ሐሳብ እንዲሰጥ ታስቦ የተሰናዳ ጽሑፍ ከመሆኑ በበለጠ በሙዚቃ ታሪክ ትልቅ አሻራ ካስቀመጡ ዕውቅ ሙዚቀኞች ይታወሱና ይዘከሩ ዘንድ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ 

በዕለቱ ዋሽንት በምን መልኩ እንደሚሠራ፣ የዮሐንስ አፈወርቅ ዋሽንት ከሌሎች በምን እንደሚለይ ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ ዋሸንት ከሸንበቆ አሊያም ቀርከሃ  የሚዘጋጅ ሲሆን፣ አራትና ከዚያ በላይ ቀዳዳዎች ያለው ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ ነው፡፡ ዋሽንት  አራት ቀዳዳዎች ሲኖሩት ዮሐንስ የሚጠቀመው የዚህ ዓይነቱ ሲሆን፣ ሌሎቹ የሚጫወቱበት ደግሞ አምስትና ስድስት ቀዳዳዎች ባላቸው ዋሽንቶች ነው፡፡

ከ75 ዓመታት በፊት በጎጃም  የተወለደው  ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ከዋሽንት ጋር የተዋወቀው በትውልድ ቀዬው መሆኑ ይነገራል፡፡ የዋሽንት አጨዋወቱን ያዩ የአካባቢው ሰዎች አዲስ አበባ ብትሄድ ይበጃል ባሉት መሠረት የትውልድ መንደሩን የለቀቀው 17 ዓመቱ ነበር።

በተለያዩ የምሽት ቤቶች መሥራቱና  በዚህም ብዙ የሕይወት ውጣ ውረድ መቀበሉ የቀረበው ጽሑፍ ያስረዳል፡፡  ከዋሽንት ውጪ በየትኛውም ዘርፍ እንዳልተሳተፈ የሚነገርለት ከያኒው በተለያዩ መልኩ መደበኛ ሥራቸው ካደረጉ በኋላ በሚሸለሙት ገንዘብም ይተዳደር እንደነበር ተገልጿል፡፡

በቀድሞው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ‹‹ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ›› በአቶ ተስፋዬ ለማ አማካይነት 35 ብር ደመወዝ ተቀጥሮ ይጫወት እንደነበር የሕይወት ታሪኩ ያስረዳል፡፡ በዚህም ለዓመታት እንደሠሩ የባህል ሙዚቃ ተጫዋቾች ሲበተኑ ‹‹ ሰማንያ›› ተብሎ በሚጠራው ሠፈር በክለብ ይሠራ እንደነበር ይነገራል፡፡ በተለይም በሠርግና ልዩ ልዩ ዝግጅቶች፣ ቱሪስቶች ሲመጡ አቶ ዮሐንስ በዋሽንት ሌሎቹ ደግሞ በሌላ የሙዚቃ መሣሪያ ይጫወታሉ፡፡

በኢትዮጵያ ሆነ በሌሎች አገሮች ዋሽንትን ለማሳወቅ መጣራቸውን፣ በተለያዩ አገሮችም ከሌሎች ተጫዋቾች ጋር ማቅረቡን፣ በተለይ በ1962 እና 1963 .. በዋሽንት የተጫወታቸው  በሕዝብ ይበልጥ እንዲታወቅ አድርጎታል፡፡

አንድ መቶ በላይ የዋሽንት ሥራዎች የተቀረፁት ከአብዮቱ በፊት ሲሆን፣ በሀገር ፍቅር ቴአትር 40 ብር የወር ደመወዝ ተቀጥረው የሠራቸው  በቁጥር ባይታወቁም በርካታ መሆናቸውና በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድምፅ ላይብረሪ እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡

በተለይም በ1970ዎቹ በዓለም ስለዞረው የሕዝብ ለሕዝብ ዐደይ አበባ ባህል ቡድን  ፀሐፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ ሲገልጹ፣ ሁሉም ሙዚቀኛ ሁለት ተቀያሪ ባለሙያዎች ሲኖራቸው ዮሐንስ አፈወርቅ ግን ብቸኛ ነበሩ፡፡

ከአንድ ሰዓት በላይ በማይቋረጥ የሙዚቃ ድግስ ውስጥ ሳያቋርጥ ብቻውን በዋሽንት የሚያጅበው አቶ ዮሐንስ ብቻ መሆኑ ተገልጿል፡፡በኩሩ ድምጻዊ ጥላሁን ገሠሠ እዩዋት ስትናፍቀኝን ጨምሮታምራት ሞላ፣ ዓለማየሁ እሸቴ፣ ተፈራ ካሳ፣ ታደሰ ዓለሙ፣ ሒሩት በቀለ፣ ለማ ገብረ ሕይወትና ፀሐይ ዮሐንስና የብዙዎች ዕንቁ ሙዚቀኞች ሥራን በዋሽንት አጅቧል፡፡

በሌላ በኩል ከኢትዮ ጃዝ ፈጣሪ ሙላቱ አስታጥቄ ጋር በአንድ መድረክ ላይ የተጫወቱ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ውጭ ሕዝብ ለሕዝብ በቡድን ሆነው በተለያዩ መድረኮች በዋሽንቱ መድረኮችን አስውቧል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ መለያ የሆነው የዋሽንት ዜማ በዮሐንስ አፈወርቅ እንደሆነ ባይታወቅበትም የእርሱ መሆኑን ጽሑፉን ያቀረቡት ፍሬሕይወት (/) እንደነገሯቸው ያስረዳሉ፡፡ ነገር ግን የአየር መንገዱ መለያ ድምፅ ሆኖም የጃዝ ንጉሥ ሙላቱ አስታጥቄ ስም ተመዝግቦ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡ ዮሐንስ አፈወርቅ ከጊዜ በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ሲጠይቅ በኢትዮ ጃዝ ንጉሥ ሙላቱ አስታጥቄ መመዝገቡን እንደነበር በጽሑፍ ተገልጿል፡፡

የዮሐንስ አፈወርቅ የዋሽንት አጨዋወት ብቃት በተለይም በመስኩ ዕውቀት ያላቸው ሰዎች እንደተናገሩት፣ ዝም ብሎ ዋሽንት የሚጫወት ብቻ ሳይሆን ዓይንና ቀልብ ከሚስብ እንቅስቃሴ ጋር ስለሚያቀርብ የተመልካችን ትኩረት ይስባል፡፡

በሌላ በኩል የሙዚቃ መሣሪያው አስቸጋሪ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ አርቲስት ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) ስለ ዮሐንስ ሲገልጹ፣ በባህላዊ የሙዚቃ መሣሪዎች ትንፋሽ የሚጠይቅ ከባድ መሣሪያ ቢሆንም፣ ዮሐንስ በዚህ መልኩ አንቱ የተባለና ምትክ የሌለው እንደነበር በጥናቱ ተቀምጧል፡፡

ዮሐንስ አፈወርቅ በአገር በቀል ትንፋሽ መሣሪያ የሆነው ዋሽንትን በመጫወት የሚስተካክለው እንደሌለ በተለያዩ መድረኮች ስሙ ቢነሳም፣ ካደረገው አስተዋጽኦ አንፃር የአሁኑ ትውልድ እንዲያውቀው የተደረገበት መንገድ እጅግ አናሳ መሆኑ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ በመድረኩ እንደተወሳው፣ በተለይም በጥበብ ዘርፍ የሚሠሩ ተቋማት፣ የሙዚቃ ሰዎች እንዲሁም አጥኚዎች ስለዋሽንቱ ንጉሥ ዮሐንስ አፈወርቅ በጥልቀት ማጥናትና ትውልድ ሥራዎቹን እንዲያውቅ ማድረግ ይገባል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...