ወ/ሮ ጽዮን ተረፈ በፓርኪሰን ፔሸንት ሰፖርት ኦርጋናይዜሽን ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ስለድርጅቱ እንቅስቃሴ ወ/ሮ ጽዮንን ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የድርጅቱ ዓላማና ተግባር ምን እንደሆነ ቢገልጹልን፡፡
ወ/ሮ ጽዮን፡- ፓርኪንሰን ፔሸንት ሰፖርት ኦርጋናይዜሽን ኢትዮጵያ የተቋቋመው የፓርኪንሰን ሕሙማንንና ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት ነው፡፡ የፓርኪንሰን ሕመም በአገራችን ብዙ ትኩረት ያልተሰጠውና ሕሙማን በከፍተኛ ችግር ላይ መኖራቸውን ምክንያት በማድረግ እነሱን ለማገዝ የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡ ከተቋቋመም 10 ዓመት ሆኖታል፡፡ በዋነኛነት የምንሠራው ሕመሙ ምን ይመስላል? የሚለውን ለኅብረተሰቡ ማስገንዘብ ነው፡፡ እንዲሁም ታማሚው ስለሕመሙ በመገናኛ ብዙኃን፣ በሚነበቡ ጽሑፎች አማካይነት ትኩረት እንዲያገኝ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን እንሰጣለን፡፡ ይህም ማለት ራሱ ታማሚው ሕመሙ ምን ይመስላል የሚለውን ነገር በነርቭ ሐኪሞች (ኒውሮሎጂስት) አማካይነት ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ ለአስታማሚዎቻቸውም ሆነ ለጤና ባለሙያም ሥልጠና ይሰጣል፡፡ ሥልጠናው ያስፈለገበት ምክንያት ፓርኪንሰንን ቶሎ መለየት እንዲቻል ነው፡፡ በአገራችን ያሉት ነርቭ ሐኪሞች ከ50 አይበልጡም፡፡ ይህም ለዚህ ሁሉ ሚሊዮን ሕዝብ ሲታይ ኢምንት መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ የነርቭ ስፔሻሊስቶች ሁሉንም ማድረስ አይችሉም፡፡ ስለሆነም ሥልጠናው ጠቅላላ ሐኪሞች፣ የጤና መኮንንኖች፣ ነርሶችና የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች በነርቭ ሐኪሞች ሠልጥነው ሕመሙን መለየት እንዲችሉ በማድረግ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የድጋፍና የእንክብካቤ ሥራዎችን እንሠራለን፡፡ ለታማሚዎች የመድኃኒት ዕገዛ ማድረግ፣ አልጋ ለያዙ ሕሙማን ደግሞ ዳይፐር እንሰጣለን፡፡
ሪፖርተር፡- ኮቪድ በገባበት ወቅት ምን ዓይነት ድጋፍ ነው ያደረጋችሁላቸው?
ወ/ሮ ጽዮን፡- ዱቄት፣ ሳሙና፣ የአፍ መሸፈኛና ሳኒታይዘር ዕገዛ ስናደርግ ቆይተናል፡፡ እንዲሁም ምርኩዝ፣ የድርጅቱ አቅም በፈቀደ መጠን ደግሞ ዊልቸር፣ የመሳሰሉትን ዕገዛ እያደረገ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ታማሚዎች ጉድጓድ መፀዳጃ ላይ ቁጭ ብለው ሊፀዳዱ አይችሉም፡፡ ይኼም የሆነው እግራቸውን ማጠፍና መነሳት ስለማይችሉ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የገቢ ማስገኛ ቀን አድርገን ባገኘነው ገንዘብ ከፍ ያለውና ፍሳሽ ያላቸው መፀዳጃ ቤቶችን እናሠራላቸዋለን፡፡ እስካሁንም ድረስ ለ37 ለሚሆኑ ሕሙማን ፍሳሽ ያለው መፀዳጃ ቤቶችን ሠርተን አስረክበናል፡፡
ሪፖርተር፡- ለጠቅላላ ሐኪሞች ሥልጠና የሚሰጡ ባለሙያዎችን ከየት ነው የምታገኙት?
ወ/ሮ ጽዮን፡- ለጠቅላላ ሐኪሞች ሥልጠና የሚሰጠው ስለፓርኪንሰን ሕመም ነው፡፡ ፓርኪንሰን ሕመምን ጠቅላላ ሐኪም ሲማር ፓርኪንሰን ላይ ትኩረት ያደረገ ብቻ ሳይሆን ትኩረት ባለመሰጠቱ የተነሳ ካሪኩለም ላይ ብዙ ነገር እንደሌለው ይታወቃል፡፡ ሥልጠናውን የሚሰጡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኒውሮሎጂ ዲፓርትመንት ኒውሮሎጂስቶች ናቸው፡፡ ወይም የነርቭ ስፔሻሊስቶች ናቸው፡፡ አዲስ አበባ ከሚገኙ ሆስፒታሎች ቢያንስ ሁለት ወይም አራት ጠቅላላ ሐኪሞች ሠልጥነዋል፡፡ ከዚህ አኳያ በመንግሥት ሆስፒታሎች ውስጥ በፓርኪንሰን የሠለጠኑ ሐኪሞች ይኖሩናል ብለን እናስባለን፡፡ ሥልጠናውም ያተኮረው ፓርኪንሰን ምንድነው? እንዴት ነው የሚታከመው በሚሉና በሌሎችም ርዕሶች ላይ ያተኮረ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- እስካሁን ምን ያህል አሠልጥናችኋል?
ወ/ሮ ጽዮን፡- የሠለጠኑት ብዛት የሚያሳይ መረጃ ለጊዜው አልያዝኩም፡፡ ቢያንስ በዓመቱ 40 እናሠለጥናለን፣ ሥልጠናውን ከጀመርን አራት ዓመት ሆኖናል፡፡
ሪፖርተር፡- ሠልጣኞቹ ባገኙት ዕውቀት በትክክል መሥራታቸውን ወይም ሥልጠናው ለሥራቸው ዕገዛ ማድረጉን የምታገኙበት ግብረ መልስ አለ ወይ?
ወ/ሮ ጽዮን፡- ሥልጠናው እንዴት ነው ውጤታማ የሆነው የሚለውን የምናየው፣ ከዚህ በፊት ታማሚው ሄዶ ፓርኪንሰን መሆኑን ሳያውቅ ለአራትና አምስት ዓመታት ያህል ይንገላታ ነበር፡፡ አሁን ግን ቶሎ ሄደው መለየት ተችሏል፡፡ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ደግሞ በየወሩ ምን ያህል በሽተኞች ናቸው የሚመረመሩት የሚለውን መረጃ እናመጣለን፡፡ በየጊዜው እየጨመረ ይመጣል፡፡ እንዲሁም የሥልጠና ባለሙያዎች ራሳቸውን ዳያግኖስ አድርገው ወደ እኛ ይልኳቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ሥልጠናው የተሰጠው በሽታው ብዙም ስለማይታወቅ ነው? ወይስ ሌላ ምክንያት አለው?
ወ/ሮ ጽዮን፡- ፓርኪሰን አዲስ አይደለም፡፡ ነገር ግን ብዙ ትኩረት ያልተሰጠው ነው፡፡ ፓርኪንሰን በሽታ በዓለም ላይ ከታወቀ 200 ዓመት ሆኖታል፡፡ ከአሥር ዓመት በፊት በአገራችን ከአሥር የማይበልጡ የነርቭ ስፔሻሊስቶች ነበሩ፡፡ አሁን ወደ 50 ተጠግተዋል፡፡ ግን ከ100 ሚሊዮን በላይ የሆነው ሕዝብ በእነዚህ ሐኪሞች ለመረዳት አስቸጋሪ ስለሆነ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ጉዳዩ በይበልጥ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ለበሽታው ትኩረት እንዲሰጠው በእናንተ በኩል የተደረገ ጥረት አለ?
ወ/ሮ ጽዮን፡- እኛ እንግዲህ ከመንግሥት አካላት ጋር የተለያየ ዓውደ ጥናቶችንና ስብሰባዎችን እናካሂዳለን፡፡ በፓርኪንሰን በሽታ የተያዙ ሰዎች ለአገር ትልቅ ውለታ የሠሩ ናቸው፡፡ እንደ መብትም ሕክምና ማግኘት መብታቸው ነው፡፡ ስለዚህ የፓርኪሰን ሕሙማን የመድኃኒት አቅርቦታቸው ማነስና ለሕክምና ወደ ጤና ተቋም ሲሄዱ የሚደርስባቸው መንገላታት መቆም አለበት ብለን እናስባለን፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን የተወሰኑ መሻሻሎች አሉ፡፡ የኒውሮሎጂ ማኅበርም ተቋቁሟል፡፡ ማኅበሩም ከእኛ ጋር በመተባበር ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡ አሁንም ግን የመንግሥት ትኩረት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ ትንሽ ይቀራል፡፡ በዓለም ጤና ድርጅት መሠረት ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው የሚችል የሚጥል በሽታ (ኤፕሊፕሲ) ነው፡፡ መንግሥት እንደ መንግሥት ቅድሚያ ትኩረት የሰጠው ይህንኑ ነው፡፡ ግን እኛም ለፓርኪንሰን ትኩረት እንዲሰጥ መንቀሳቀሳችንን አናቆምም፡፡
ሪፖርተር፡- ምን ያህል የፓርኪንሰን ሕሙማንን ተደራሽ አድርጋችኋል?
ወ/ሮ ጽዮን፡- እንደሚያውቁት እኛ አዲስ አበባ ላይ ብቻ ነው የምንሠራው፡፡ በአሁኑ ጊዜም 746 ፓርኪንሰን ሕሙማንን ነው ተደራሽ ያደረግነው፡፡
ሪፖርተር፡- መድኃኒት መግዛት ላልቻሉ ምን ዓይነት ድጋፍ እያደረጋችሁላቸው ነው? አብዛኞቹ በጡረታ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ የጡረታ አበላቸውን ደግሞ ለመድኃኒት መግዣ እያደረጉ በምትኩ ቤተሰቦቻቸውን ለችግር ዳርገዋል፡፡ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት?
ወ/ሮ ጽዮን፡- አሁን እንዳሉት በጣም ችግሩ ይኼ ነው፡፡ ዕድሜ ገፍቷል፣ ሕመም አለ፡፡ በተጨባጭም በአገራችን ሠርቶ ገንዘብ ማምጣት በአብዛኛው የወንዱ ኃላፊነት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ደግሞ በሽታው ወንዱን ነው የሚያጠቃው፡፡ ስለዚህ የእሱ ገቢ ቆመ ማለት ደግሞ ራሱን የቻለ አንድ ችግር ሲሆን ማስታመሙ ደግሞ ሌላው ችግር ነው፡፡ ስለዚህ በኢኮኖሚ በጣም ነው የሚጎዱት፡፡ እኛ የምንሠራላቸው ነገር ቢኖር ራሳቸውን ታማሚዎችንም እናሠለጥናለን፡፡ ቤተሰቦቻቸውን እናሠለጥናለን፣ አልጋ የያዙ ከሆነ ደግሞ ቤት ለቤት እንሄዳለን፡፡ ዳይፐር ይሰጣቸዋል፡፡ የመድኃኒት ዕገዛ ይደረግላቸዋል፡፡ በሠለጠኑ ነርሶችም እንክብካቤ ይደረግላቸዋል፡፡ ይህም ማለት ደግሞ በቂ ዕገዛ እያደረግን ነው ማለት አይደለም፡፡ አሁን ያሉን ሁለት ነርሶች ናቸው፡፡ ያለን አንድ መኪና ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ በመኪና ማዳረስ አንችልም፡፡ ስለዚህ በታክሲ መንቀሳቀስ ግድ ሆኗል፡፡ በታክሲ ከተንቀሳቀሱ ደግሞ በቀን ከሦስትና ከአራት ታማሚዎች በላይ ማየት አይችሉም፡፡ ትልቁ ተግዳሮታችን ይኼ ነው፡፡ በተረፈ የፓርኪንሰን መድኃኒት በጣም ውድ ነው፡፡ በዛ ላይ ደግሞ ሁልጊዜ አይገኝም፡፡ አሁን ደግሞ የምንዛሪው ጉዳይ ሲታከልበት የበለጠ በጣም ውድና የማይገኝ ሆኗል፡፡
ሪፖርተር፡- ማን ነው የሚረዳችሁ?
ወ/ሮ ጽዮን፡- የሚረዳን ‹‹ብሬድ ፉድ ፎር ዘ ወርልድ›› የተባለ የጀርመን ድርጅት ሲሆን፣ የተወሰነ መድኃኒት መግዣ ይሸፍንልናል፡፡ የመድኃኒት ዕገዛቸውን እንዲያጠናክሩ የሚገልጽ ደብዳቤ አስገብተናል፡፡ በአሁኑ ጊዜም ለ260 ፓርኪንሰን ታማሚዎች የመድኃኒት ዕገዛ እናደርጋለን፡፡ ‹‹ወርልድ ፓርክንሰን ፕሮግራም›› የተባለ የካናዳ ድርጅት ለ80 ታካሚዎች የስድስት ወር መድኃኒት ዕገዛ አድርጎልናል፡፡