Friday, March 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሦስት ቢሊዮን ብር የሚያንቀሳቅሰው የሜትሮፖሊታን ሪል ስቴት ፕሮጀክት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ቅንጡ የሚባሉ የሪል ስቴት ግንባታዎችን በማካሄድ ላይ የሚገኘውና መሠረቱን አሜሪካ ያደረገው ሜትሮፖሊታን ሪል ስቴት አምስተኛ ፕሮጀክቱን ቅዳሜ ጥር 6 ቀን 2013 ዓ.ም. አስጀመረ፡፡

የአዲሱን ፕሮጀክት መጀመር አስመልክቶ ኩባንያው እንዳስታወቀው፣ ሴንትራል ታወር የሚባለውና ጂ+19 ወለሎች ያሉት ሕንፃ በአዲስ አበባ አፍሪካ ኅብረት አካባቢ የሚገነባ ሲሆን፣ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቅና በአራት ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቅ ነው፡፡

በአዲስ አበባ በሪል ስቴት ልማት በሕንፃ ርዝማኔው ከፍተኛ ከሚባሉ አንዱና ቅንጡ ቤቶችን ይይዛል የተባለው አፓርትመንት፣ በአጠቃላይ 76 ቤቶችን የሚይዝ ነው፡፡  

ከምድር በታች ያለ ወለልን ጨምሮ 21 ወለሎች የሚኖሩት ፕሮጀክቱ፣ በውስጡም የመኪና ማቆሚያ፣ ጂምናዚየም፣ የጋራ መዝናኛና የሰገነት ሥፍራ፣ እንዲሁም 24 ሰዓት የማይቋረጥ ካሜራ ይኖረዋል ሲሉ የኩባንያው ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ልዑል ደረጀ ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ግንባታዎቹን የሚያከናውነው ሜትሮፖሊታን ሪል ስቴት፣ በሁሉም ፕሮጀክቶቹ ያሉ ቤቶቹ የተሟላ የማዕድ ቤት ዕቃዎች፣ ኃይድሮሊክ ሲስተም መክፈቻና መዝጊያ፣ የኤምዲኤፍ ኪችን ካቤኔቶችና ቁም ሳጥኖች የሚገጠምላቸውና ከሶፋና አልጋ በስተቀር ዕቃዎች የሚሟሉላቸው ይሆናል ተብሏል፡፡ ግንባታው የተጀመረው ሴንትራል ታወር አፓርትመንት ቤቶች የአንዱ ዋጋ ከአራት እስከ ሰባት ሚሊዮን ብር ይደርሳልም ብለዋል፡፡

አቶ ልዑል እንደገለጹት፣ የመጀመርያው ፕሮጀክት ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ተገንብቶና ተጠናቆ ለባለቤቶቹ የተረከበ ሲሆን፣ ይህ ባለስድስት ወለልና በአንድ ወለል ላይ አንድ ቤት ያለው ቅንጡ አፓርታማ ነው፡፡

ሁለተኛው ፕሮጀክት ቦሌ ሚድትዊን ቅንጡ አፓርታማዎች ፕሮጀክት ሲሆን፣ የሕንፃው ግንባታ ከሁለት ዓመት ያልበለጠ ጊዜ ፈጅቷል፡፡ ሕንፃው 27 ቤቶችን የያዘና 11 ወለሎች ያሉት ነው፡፡

ሦስተኛው ፕሮጀክት ሜትሮፖሊታን ታወር ሲሆን፣ አራት ቤዝመንት ያለውና ባለ 12 ወለል ሕንፃ ነው፡፡ የዚህ አፓርትመንት 85 በመቶ ሽያጭ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱን ልዩ የሚያደርገው እንደ ሁሉም አፓርታማዎች ቁሳቁሶችንና አገልግሎቶችን ከማሟላቱም በላይ በከተማዋ የሚስተዋለውን የውኃ እጥረት ታሳቢ አድርጎ የውኃ ጉድጓድ የተቆፈረለት መሆኑ ነው፡፡

የዌስት ቪው ስታንዳርድ አፓርታማዎች የሚል ስያሜ ያለው ሌላው የኩባንያው ፕሮጀክት፣ ኩባንያው ከሚታወቅበት መሸጫ ዋጋ በግማሽ በመቀነስ የተወሰኑ የግንባታ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ ዕቃዎች በማሟላት አቅምን ያገናዘበና ብዙኃኑን የቤት ባለቤት ለማድረግ ያለመ መሆኑን ኩባንያው አስታውቋል፡፡

በከተማዋ ውስጥ ውድ የሚባሉትን ቅንጡ አፓርትመንቶች እየገነባ ያለው ይህ ኩባንያ፣ ሁሉም ቤቶች ውስጥ ስቶቭ፣ ኦቭን፣ የውኃ ማሞቂያ፣ ኪችን ካቢኔትና ሌሎች ቁሳቁሶች አሟልቶ እንደሚያስረክብ አቶ ልዑል ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ካለው የቤት እጥረት ሳቢያ ኩባንያው ቅንጡ አፓርትመንቶችን ከመገንባት መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ለመድረስ ምን እየሠራ ነው? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ልዑል ትልቁ ዓላማችን መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው ቤት ፈላጊዎች መሄድ በመሆኑ ከሦስት እስከ አምስት ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ ወደዚህ ለመግባት አቅደናል ብለዋል፡፡

ኩባንያው በአሁኑ ወቅት እየሸጣቸው ያለው ቤቶች አነስተኛ ዋጋ ከአራት ሚሊዮን ብር የሚጀምር ሲሆን፣ እስከ 18 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ቤቶችም አሉ፡፡ ኩባንያው የሚገነባቸው ቤቶች ውድ የሚባሉባቸው ምክንያቶች የተለያዩ ሲሆን፣ አንዱ አፓርትመንቶቹ የተገነቡበት አካባቢና ቦታዎቹም ሲገዙም በውድ ዋጋ በመሆናቸው መሆኑን አቶ ልዑል አብራርተዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘትም በውጭ ምንዛሪ ለማገዝም የ15 በመቶ ቅናሽ አድርገው እንደሚሸጡም ገልጸዋል፡፡

 ሜትሮፖሊታን ሪል እስቴት ከተቋቋመ ስድስት ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን፣ በአሜሪካ ኢንቨስተሮች የተመሠረተ ነው፡፡ ላለፉት አምስት ዓመታትም በአዲስ አበባ ቁልፍ ቦታዎች ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ ቆይቷል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱን አጠናቆ ለቤት ግዥዎቹ አስረክቧል፡፡ የመጀመርያው ፕሮጀክቱ 150 ሚሊዮን ብር የፈጀ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ አንድ ቢሊዮን ብር የጠየቀ ነው፡፡ ኩባንያው ወደ ሥራ ሲገባ 23 ሚሊዮን ብር ካፒታል በመያዝ ሲሆን፣ አሁን ወደ ሦስት ቢሊዮን ብር በማንቀሳቀስ ላይ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች