ሱዳን በስተ ምሥራቅ የግዛት ወሰኗ በኩል ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር ይገባኛል የምትለውን የወሰን ጉዳይ ለመፍታት፣ በኢትዮጵያና በሱዳን መንግሥታት መካከል ያለውን ለረዥም ዘመናት የተዘለቀ ወዳጅነት መሠረት በማድረግ በውይይት ለመፍታት ረዥም ርቀት ተጉዛለች።
የይገባኛል ጥያቄውን ለመመለስ ሁለቱ አገሮች የጋራ የድንበር ኮሚሽን አቋቁመው ውይይት ሲያደርጉ በቆዩባቸው ዓመታት፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ጎልተው የወጡ ልዩነቶች አልተሰሙም፡፡ ባቋቋሙት የጋራ ድንበር ኮሚሽን የይገባኛል ጥያቄውን ለመመለስ የጀመሩት ጥረት በተለያዩ ውስጣዊ ምክንያቶች ቢጓተትም፣ ሁለቱ አገሮች በመጓተቱ ምክንያት ሲካረሩ ሳይሆን አጓታች የነበሩ ምክንያቶችን ተቀብለው ሲስማሙ አሳልፈዋል።
ይሁን እንጂ ይህ መግባባት ካለፈው ዓመት መጋቢት ወር ወዲህ በሱዳን በኩል አፋጣኝ መፍትሔ ለማግኘት የተለየ ጉትጎታ ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በዚሁ ጊዜ ውስጥ ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያ የተለየ ባህሪን እያንፀባረቀች የታይችበት ወቅት ሲሆን፣ ይህ ወቅት የግድቡ ድርድር በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት እየተመራ የነበረበት ነው።
በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት የተጀመረው ድርድር ሰባት ወራት የፈጁ ሰባት ዙር ስብሰባዎች የተካሄዱበት ቢሆንም፣ ሰባቱም ውይይቶች የሱዳን መንግሥት ባቀረባቸው ተለዋዋጭ ጥያቄዎች መቋረጣቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት ይገልጻል።
ሰባተኛው ዙር ውይይት ያለ ውጤት የተጠናቀቀው በኅዳር 2013 ዓ.ም. ሲሆን፣ ይህ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻ (ውጊያ) የጀመረበት ነው።
በትግራይ የተቀሰቀሰው ውጊያ የኢትዮጵያ መንግሥትን ሙሉ የጦር ኃይል አሰባስቦ ወደ ሰሜን የአገሪቱ ክፍል ትኩረት ባደረገበት ወቅት፣ የሱዳን መንግሥት ከኢትዮጵያ በሚዋሰንበት ድንበር ይገባኛል የሚለውን አካባቢ በኃይል የመቆጣጠር ዘመቻ አካሂዷል።
ይህንን ክስተት የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ ክህደት ሲመለከተው፣ የሱዳን መንግሥት በበኩሉ በሉዓላዊ ግዛቱ ውስጥ የተደረገ የጦር ሥምሪት እንደሆነ የሚገልጽ መግለጫ በይፋ አውጥቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሱዳን በኃይል ከያዘቻቸው አካባቢዎች ጦሯን አስወጥታ የድንበር ይገባኛል ጥያቄውን በተጀመረው የውይይት መንገድ እንዲጨርስ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርብ የቆየ ሲሆን፣ ይህንንም ለማጠናከር የደቡብ ሱዳን መንግሥት እንዲያደራድር ጥያቄ አቅርቦ ተቀባይነት አግኝቷል።
የደቡብ ሱዳንን አደራደሪነትም የሱዳን መንግሥት ተቀብሎታል። ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ድርድሩ ሊካሄድ የሚትችለው የሱዳን ጦር በኃይል የያዘውን አካባቢ ለቆ ወደ ነበረበት ሲመለስ እንደሆነ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል።
ይህ ቅድመ ሁኔታ ግን በሱዳን መንግሥት እስከዚህ ሳምንት ድረስ ተቀባይነት አላገኘም።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ ድርድር ለመቀመጥ እንደማይችል ያስታወቀው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ሱዳን ጦሯን ካላስወጣች የኃይል ዕርምጃ ሊወስድ እንደሚችል አስጠንቅቋል።
በዚህ መንገድም የሱዳንን በጎ ምላሽ ባለማግኘቱ ከሁለት ሳምንታት በፊት የጦር ኃይሉን ወደ ሱዳን ድንበር አስጠግቷል።
ይህንን ተከትሎም የሱዳን መንግሥት የካቲት 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ ጦር ወደ ሱዳን ሉዓላዊ ግዛት ጥሶ እንደገባ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የሱዳንን መግለጫ ተከትሎም የዓረብ ሊግ የካቲት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የተካረረው የድንበር ውዝግብ ወደ ግጭት የሚያመራ ከሆነ፣ የዓረብ ሊግ በማንኛውም መንገድ የሱዳንን የግዛት አንድነት ለመጠበቅ ከሱዳን መንግሥት ጋር እንደሚቆም ይፋ አድርጓል።
ከሱዳን የድንበር ጥያቄ ጀርባ ያሉ እጆች
የሱዳን መንግሥት ይገባኛል የሚለውን የድንበር ጉዳይ ለመፍታት ሲከተለው የነበረውን የውይይት አማራጭ በቅፅበት ለውጦ በኃይል የድንበር አካባቢዎችን የተቆጣጠረው፣ በውጭ ግፊት በመበረታታትና የውስጥ የሥልጣን ጥያቄን በዚህ መንገድ በአቋራጭ ለመመለስ እንደሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ይከሳል።
ለዚህ ተልዕኮ ውስጥ የሱዳን መንግሥት አባላት ሙሉ ተሳትፎ እንደሌላቸውና የሱዳን ሕዝብ ፍላጎትም እንዳልሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ሙሉ ግንዛቤ እንዳለው፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) በተደጋጋሚ ገልጸዋል።
ከዚህ የሱዳን ድንገተኛ የጦር እንቅስቃሴ ጀርባ ያለው የውጭ እጅ በዋናነት የግብፅ መንግሥት እንደሆነ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ኃላፊዎች በተደጋጋሚ ጊዜ በስም ሳይገልጹ ይናገራሉ፡፡
ይህንንም የሚገልጹበት መንገድ፣ ‹‹የህዳሴ ግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል ፍላጎት ካለው ኃይል›› በማለት ነው።
የሱዳን መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን መልካም ግንኙነት በድንገት ቀይሮ የተለየ ባህሪ ማንፀባረቅ የጀመረበትን ጊዜ ወደኋላ በመመለስ የተደረገ ዳሰሳም፣ የሱዳን የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበርና የጦር ኃይሎች ዋና አዛዥ ሌተና ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃንና ምክትላቸው እ.ኤ.አ. በማርች 2020 በግብፅ ካይሮ ተገኝተው ከግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋርና ከግብፅ የደኅንነት ኃላፊ ጋር ያደረጉትን የስምምነት ቋጠሮ ላይ ያደርሳል።
በወቅቱ በግብፅና በሱዳን መካከል የተደረገው ሰምምነት በሁለቱ አገሮች መካከል ሰፊ የሆነ የደኅንነትና ወታደራዊ ትብብርን በፍጥነት ማድረግ፣ እንዲሁም ሁለቱ አገሮች በቀጣናው ውስጥ የሚገጥማቸውን የደኅንነት ሥጋት ለመቀልበስ የሚያሰችላቸውን ወታደራዊ ቁመና መላበስ እንደሆነ ይገልጻል።
በዚህ ስምምነት ውስጥ ከተካተቱት መካከልም የግብፅ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ቅርንጫፍ ቢሮውን በሱዳን እንዲከፍት የሚለው ይገኝበታል።
ሁለቱ አገሮች ተደጋጋሚ የሆነ ጥምር ወታደራዊ ልምምዶችን ማድረግና አቅማቸውን ለማሳደግ ያደረጉት ስምምነት ሌላው ሲሆን፣ ከወቅቱ የኢትዮ ሱዳን የድንበር ውዝግብ ጋር በቀጥታ የሚገናኘው ስምምነት ደግሞ ሉዓላዊ ግዛታቸውን በጋራ መጠበቅና አሸባሪዎችን በጋራ መዋጋት የሚለው ይገኝበታል።
በተጨማሪም ወታደራዊ ኢንዱስትሪዎችን በሱዳን ማቋቋም ሌላው የስምምነቱ አካል ነው።
የኢትዮጵያ ጦር ወደ ሱዳን ድንበር ከተሰማራ በኋላ ኢትዮጵያ ድንበሯን አልፋ እንደገባች ያስታወቀችው ሱዳን፣ የካቲት 7 ቀን 2013 ዓ.ም. በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቷ በኩል ባወጣችው መግለጫ፣ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰደው ዕርምጃ ተቀባይነት የሌለውና መዘዙም ከሁለቱ አገሮች አልፎ የአፍሪካ ቀንድን መረጋጋት የሚያውክ ነው፤›› በማለት አስታውቃለች።
‹‹ኢትዮጵያ የወሰደችው ዕርምጃ ለሚያስከትለው ውጤት ሙሉ ኃላፊነት ትወስዳለች፤›› የሚለው የሱዳን መግለጫ፣ ነገሮች ሳይበላሹ የድንበር ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ስምምነት የተደረሰባቸውን ማዕቀፎች መሠረት አድርጎ በማካለል መፍታት የተሻለ አማራጭ እንደሆነም አሳስቧል።
ይህንን የሱዳን መግለጫ ተከትሎ የዓረብ ሊግ የካቲት 9 ቀን ባወጣው መግለጫ ‹‹የዓረብ ሊግ yአባል አገሮቹ ሉዓላዊነትና የግዛት እንድነትን መከበር አለበት የሚል ጽኑ አቋም አለው። ከዚህ አኳያም የሱዳን መንግሥት የግዛት ወሰኑን ለማስከበር የሚወስደውን ማንኛውም ሕጋዊ ዕርምጃ ደግፈው የዓረብ ሊግ አባል አገሮች ከጎኑ ይቆማሉ፤›› በማለት አስታውቋል።
የዓረብ ሊግ ላወጣው መግለጫ ከኢትዮጵያ በኩል ሪፖርተር ለኅትመት እስከገባበት ማክሰኞ ምሽት ድረስ የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡
ነገር ግን የዓረብ ሊግ መግለጫ በወጣበት ዕለት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን፣ የዓረብ ሊግ አገሮችን በንቃት በምትከታተለው ቱርክ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አድርገው፣ ወደ ህንድ ማቅናታቸው ይታወሳል፡፡
አቶ ደመቀ ከቱርክ አቻቸው ሜቭሉት ካቩሶግሉ ጋር በመሆን በአንካራ የተገነባውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሕንፃ ያስመረቁ ሲሆን፣ ለሁለት ቀናት በነበራቸው ቆይታም በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የተካረረውን የድንበር ውዝግብ ለቱርኩ አቻቸው አስረድተዋል።
የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም የኢትዮጵያና የቱርክ ግንኙነት በወዳጅነት ብቻ የሚገለጽ እንዳልሆነ በማስታወቅ፣ መንግሥታቸው ከኢትዮጵያ ጋር በሁሉም ዘርፍ ተባብሮ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
የቱርክ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ከ15 ቀናት በፊት ባፀደቀው የውሳኔ ሐሳብ የቱርክ የባህር ኃይል በቀይ ባህር፣ በኤደን ባህረ ሰላጤና በዓረብ ባህር ላይ ተሰማርቶ እንዲቆይ ውሳኔ አሳልፏል።
የቱርክ የባህር ኃይል ከአካቢው አገሮች ጋር በትብብር እንዲሠራና እንደ አስፈላጊነቱም የሥምሪት ደረጃውን ከፍ እንዲያደርግ የታቀደለት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በዚህም ውሳኔ የቱርክ የባህር ኃይል የአገሪቱን ፖለቲካዊ ጥቅም እንዲያረጋግጥ ኃላፊነት የተሰጠው ሲሆን፣ ይህንንም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ እንደሚወጣ ተገልጿል።
በሌላ በኩል የዓረብ ሊግ አገሮችን ወታደራዊ እንቅስቃሴ በንቃት የምትከታተለው ኢራን ወደ ሶማሊያ ግዛት በሚጠጋው በዓረብ ባህር፣ ከሩሲያ የባህር ኃይል ጋር በመሆን የጋር ወታደራዊ ልምምድ አድርጋለች፡፡
ይህ ወታደራዊ ልምምድ በተደረገበት ወቅትም የሩሲያ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ነበር።
በመሆኑም በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል በድንገት የተቀሰቀሰው የድንበር ውዝግብ በከፍተኛ ፍጥነት ተካሮ፣ የሌሎች አገሮች የእጅ አዙር ጣልቃ ገብነትና ግጭት አፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ሥጋት ተፈጥሯል፡፡