- አንዳንድ ልዩ ተልዕኮ ያላቸው ኤጀንሲዎች ኢትዮጵያ ከፍተኛ ዕዳ አለባት እያሉ ስለከፈቱት ዘመቻ ሪፖርት እፈልጋለሁ።
- ለዛሬ ከተዘጋጁት ወቅታዊ ሪፖርቶች አንዱ እሱ ነው ክቡር ሚኒስቴር?
- በል እሱን አስቀድመው. . .
- ያለፈው መንግሥት አፈናን እናስተካክል ብለን የኤንጂኦ አዋጁን ብናሻሽል ጭራሽ በኛ ላይ ይዘባበታሉ?
- እነ ማን ናቸው ክቡር ሚኒስትር?
- ኤጀንሲ ነን የሚሉት ናቸዋ፡፡
- ምንድነው ያደረጉት?
- እንዴት አልሰማህም? የውጭ ዕዳችንን በተመለከተ ምን የሚሉት ሬቲንግ አውጥተው እየተዘባበቱብን አይደለም እንዴ?
- ኦ . . . ዓለም አቀፍ ክሬዲት ሬቲንግ ኤጀንሲዎች ያወጡትን ሪፖርት ነው የሚሉት?
- ዓለም አቀፍ ቢሆኑም የአገሪቱን ሕግ አክብረው ካልተንቀሳቀሱ ዕርምጃ ይወሰድባቸዋል፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ከእርሶ ባላውቅም የሳቱት መሰለኝ።
- ምንድነው የሳትኩት?
- እነዚህ ኤጀንሲዎች የተለዩ ናቸው. . . የአገሮችንና የግዙፍ ኩባንያዎችን ዕዳ የመሸከምና የመክፈል አቅም ተንትነው ደረጃ የሚያወጡ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ናቸው።
- እና ቢሆኑስ? በውስጥ ጉዳያችን ገብተው የዕዳ መጠናችንን ሳያስፈቅዱ ማውጣት ምን ማለት ነው? የዕዳችንን መጠን ማውጣት ብቻ ቢሆን ጥሩ፡፡ ዕዳቸውን መክፈል ሊያቋርጡ ይችላሉ እስከ ማለት እኮ ነው የደፈሩን፡፡
- እንዴት መሰለዎት ክቡር ሚኒስትር ከዚህ ቀደም ከውጭ የግል የገንዘብ ተቋማት የጠየቅነውን ብድር ለማግኘት ስንል መክፈል እንደምንችል እንዲያረጋግጡ ኮንትራት የተሰጣቸው ናቸው። ብድሩን ከፍለን እስክናጠናቅቅ ድረስ የመክፈል አቅማችንን እየመዘኑ ሪፖርት የማድረግ ግዴታ አለባቸው።
- እኛ ከመጣን ወዲህ የተበደርነው የለም። እንኳን ልንበደር ይቅርና የተበደሩትን ለመክፈልም ተቸግረናል።
- ቀድሞ የነበረው መንግሥት የተበደረውን ለመመዘን የተቀጠሩ ናቸው።
- ለዚያ ነዋ?
- ምኑ?
- ከጁንታው ጋር የጥቅም ግንኙነት ስላላቸው ነዋ?
- ክቡር ሚኒስትር ከእርሶ ባለውቅም አሁንም የሳቱት መሰለኝ።
- ከእርሶ ባላውቅም እያለ ሳቱት ይለኛል እንዴ? ምንድነው ከእነሱ ጋር ያለህ ግንኙነት?
- ነገሩን ላስረዳ ብዬ እንጂ ምን አገናኝቶን ክቡር ሚኒስቴር።
- ውጣልኝ!
[ክቡር ሚኒስቴሩ ፓርቲዎች የጀመሩት የምርጫ ዘመቻን በተመለከተ ከፀጥታ ኃላፊው ጋር እየተወያዩ ነው]
- ለትራንስፖርት የተሠለፈው ሕዝብ ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ፡፡
- ቶሎ አስቁሟቸው፡፡
- የምርጫ ቅሰቀሳ በይፋ ስለተጀመረ ይህንን ለማድረግ አንችልም ክቡር ሚኒስትር ሕግ መተላለፍ ነው የሚሆንብን።
- አስቁሙ ብያለሁ፡፡
- ብናስቆምም ውጤቱ ከአንድ ቀን አያልፍም። ነገ ቦርዱ ፈቃድ ይሰጣቸዋል።
- ዛሬን በዚህ ካለፍን ለነገ ሌላ መፍትሔ አናጣም።
- ምን ልናደርግ እንችላለን?
- ክልከላ እንጥላለን።
- የምን ክልከላ ?
- የመንግሥት ሠራተኞች ከፐብሊክ ሰርቪስ ባሶች ውጪ በነፃ እንዳይጠቀሙ የሚከለክል መመርያ እናወጣለን፡፡
- እ. . .
- ነፃ ትራንስፖርትን ማቅረባቸውን ከቀጠሉ ደግሞ ሌላ ክልከላ እንጥላለን።
- ሌላ ክልከላ?
- አዎ። የትራንስፖርት ሥምሪት ኃላፊነት የመንግሥት ብቻ በመሆኑ ሥምሪቱን በማወክ እንከሳቸዋለን!
[ክቡር ሚኒስትሩ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሰፈረው መልዕክት ስላልገባቸው የምርጫ ዘመቻ ኃላፊው ጋር ደወሉ]
- በማኅበራዊ ሚዲያ ስለ ምርጫ ያስተላለፉትን መልዕክት ተመለከትክ?
- አላየሁትም፡፡ ምን አሉ?
- ምን ማለታቸው እንደሆነ ስላልገባኝ ነው የደወልኩልህ?
- ምንድነው ያሉት?
- የመልዕክቱ መጨረሻ ላይ ‹‹Duty’s are ours, Results are God’s›› ብለዋል።
- እኔም አልገባኝም፡፡
- ልክ አይደሉም፡፡
- ቆይ አንቸኩል። ምን ማለታቸው እንደሆነ እናረጋግጥ፡፡
- ቢሆንም ገለልተኛ ከሆነ አካል እንደዚያ ያለ መልዕክት መተላለፍ የለበትም።
- ምን ለማለት እንደፈለጉ ገባዎት እንዴ?
- ሌላ ትርጉም ቢኖረው እንኳን ሕዝቡን በድምፅህ ወስን እያልን ውጤቱን ከፈጣሪ ጋር ማገናኘት ተገቢ አይመስለኝም።
- ሌላ ነገር ለማለት ፈልገውም ሊሆን ስለሚችል ባንቸኩል ጥሩ ነው።
- ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?
- የፀጥታው ሁኔታ ምርጫውን እንዳይሰተጓጎል አሳስቧቸው ሊሆን ይችላል!