Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልያቺ የካቲት 12 ቀን!

ያቺ የካቲት 12 ቀን!

ቀን:

‹‹ራስን ካንገት ላይ ቆራርጦ እየጣለ
በችንካር ቸንክሮ ሰው እየገደለ

ሰውን ከእነቤቱ አብሮ እያቃጠለ

ማነው እንደ ፋሺስት በሰው ግፍ የዋለ?
ሥጋችንን ገድለው ሊቀብሩት ከጀሉ
በዚህ ያልነበሩ ሐሰት እንዳይሉ
እሊህ አስክሬኖች ይመሰክራሉ፡፡
ይህን ታላቅ ሥቃይ መከራና ግፍ
ሲያስታውስ ይኖራል የታሪክ መጽሐፍ…››

ከሰማንያ አራት ዓመታት በፊት፣ በፋሺስት ጣሊያን ጭፍራ ማርሻል ሮዶልፎ ግራዚያኒ አማካይነት በአዲስ አበባ ከተማ ከየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ቀናት በዘለቀው ጭፍጨፋ ሰማዕት ለሆኑት 30 ሺሕ ኢትዮጵያውያን በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዐፀድ በቆመው ሐውልት ግርጌ ከሠፈረው ግጥም የተወሰደ ነው፡፡

የሰማዕታቱ ቀን ሲገለጽ

ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1848 እስከ 1966›› በተሰኘውና በ1989 ዓ.ም. በታተመው መጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ የጣሊያን ፋሺዝም ጽልመታዊ ገጽታ ቁልጭ ብሎ የወጣው በየካቲት 12 ቀን 929 ዓ.ም. ነው፡፡ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የተባሉ ሁለት ወጣቶች በግራዚያኒ ላይ ቦምብ ጥለው ካቆሰሉት በኋላ አዲስ አበባ ላይ መዓት ወረደባት፡፡ ‹‹ጥቁር ሸሚዝ›› እየተባሉ የሚታወቁት የፋሺስት ደቀመዛሙርት መንግሥት አይዟችሁ እያላቸው አዲስ አበባን ቄራ አደረጓት፡፡ የሰው ልጅ ጭንቅላት እንደ ዶሮ እየተቀነጠሰ ወደቀ፡፡ ቤቶች ከእነነዋሪዎቻቸው ጋዩ፡፡

እርጉዝ ሴቶች በሳንጃ ተወጉ፡፡ የጭፍጨፋው ተቀዳሚ ዒላማ የተማሩ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ በተለይም የጥቁር አንበሳ አባላት ከራስ እምሩ ጋር እጃቸውን ከሰጡ በኋላ በከተማይቱ ይገኙ ስለነበር በወረንጦ እየተለቀሙ ተረሸኑ፡፡ ይህ የምሁራን ጭፍጭፋ አንድ ትውልድ እንዳለ ያጠፋ በመሆኑም በአገሪቱ የፖለቲካና ምሁራዊ ታሪክ ላይ የማይሽር ቁስል ጥሎ አለፈ፡፡ በዘመኑ የነበሩት ደራሲ ተመስገን ገብሬ “የዓይን እማኙ ሊቀ ጠበብት እውነቱና የካቲት 12” በተሰኘ ጽሑፋቸው እንዲህ ጽፈዋል፡-

‹‹ከሦስት ቀን የከተማ ጥፋት በኋላ ከሆለታ የመጡ የፋሺስት አውሬዎች በሚመለሱበት ካሚዮን በኋላው በኩል አቶ አርዓያን እግራቸውን ጠርቅመው አሠሯቸው፡፡ ካሚዮኑ ሳይጐትታቸው ‹እኔ ወደ ሰማይ እንድገባ ሰማይ ተከፍቶ ይጠብቀኛል፡፡ ኢየሱስንም በዚያ አየዋለሁ፡፡ ደስ ይለኛል፡፡ ደስ ይለኛል፡፡ ደስ ይለኛል!› የሚለውን የሚሲዮን መዝሙር ዘመሩ፡፡ ፋሽስቶቹም የተሻለውን መዝሙር ብትሰማ ይሻልሃል አሏቸውና ዱኪ ዱኪ የሚለውን መዝሙራቸውን ዘመሩ፡፡ ካሚዮኑም ሞተሩን አስነስቶ ሲነዳ ታስረው ቁመው ነበርና ያን ጊዜ ዘግናኝ አወዳደቅ አቶ አርዓያ ወደቁ፡፡ ካምዮኑም እየፈጠነ ጐተታቸው፡፡

ከአዲስ አበባ እስከ ሆለታ አርባ ኪሎ ሜትር ይሆናል፡፡ ካምዮኑ ከዚያ ሲደርስ ያ ከካሚዮኑ ጋር የታሰረው እግራቸው ብቻ እንደተንጠለጠለ ነበርና የካሚዮኑ ነጂ ከካሚዮኑ ፈታና ለውሾች ወረወረው፡፡ እኔንም ያለሁበትን ቤት ሰብረው ከዚያ ቤት ያለነውን አውጥተው ከየመንደሩም ሕዝቡን አጠራቅመው ኑረዋል፡፡ ከዚያም መሀል ጨመሩን፡፡

‹‹ስምንት መትረየስ በዙሪያችን ጠምደዋል፡፡ በዚያም ቦታ ቁጥራቸው በብዙ የሆኑ ሐበሾችን አስቀድመው ገለዋቸዋል፡፡ ሬሳቸውም ተቆላልፎ በፊታችን ነበረ፡፡ እኛንም በዚያ ሊገድሉን ተዘጋጁ፡፡ ለመትረየስም ተኩስ እንድንመች ያንዳችንን እጅ ካንዱ ጋር አያይዘው አሰሩን፡፡ አሥረውን ወደ መተኰሱ ሳይመለሱ አንድ ታላቅ ሹም መጣ፡፡ የርሱም ፖለቲካ ልዩ ነበረ፡፡ ፋሺስቶች የሚያደርጉትን የሰላማዊ ሕዝብ መግደል፤ ሕፃናቶችን ከአባትና እናታቸው ጋራ በቤት ዘግቶ ማቃጠል መልካም ብሎ ቢወድ እንኳን እኒያ ቦምብ በቤተ መንግሥቱ ስብሰባ የወረወሩት ሐበሾች ሳይታወቁ እንዲቀሩ አይወድም ነበርና ስለዚህ ካሚዮኖች ይዞ እየዞረ ፋሽስቶች የሚገድሉትን እያስጣለ ወደ እስር ቤት ለምርመራ ይወስድ ኑረዋል፡፡

እኛንም እንዲተኮስብን ታሰረን ከቆምንበት ከቅዱሰ ጊዮርጊስ ጠበል አጠገብ ካለው ሸለቆ እስራታችንን አስፈትቶ በአምስት ረድፍ ወደላይኛው መንገድ ለመድረስ ስንሄድ በአካፋ ራሳቸውን የተፈለጡ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡ ምራቄ ደረቀ፡፡ በካሚዮኑ ወደ እስር ቤት አስወሰደን፡፡ ለጊዜው እስር ቤት ያደረጉት ማዘጋጃ ቤትን ነበር፡፡›› ስድስት ኪሎ በሚገኘው የያኔው ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ያሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ፣ ለኔፕልስ ልዑል ልደት ክብር ተብሎ በተዘጋጀው መሰናዶ አጋጣሚ፣ በወቅቱ የተፈጠረውን የፋሺስት ጣሊያን ጭፍጨፋ የታዘበው ሀንጋሪያዊው ሐኪም ዶ/ር ላዲስላስ ሳቫ ዓይኑ ያየውንና የታዘበውን በማስታወሻው መግለጹን በጳውሎስ ኞኞ ‹‹የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት›› መጽሐፍ ላይ እንዲህ ተመልክቷል፡-

‹‹…ከዚህ በኋላ በግቢውና በአካባቢው ወዲያውኑ ጅምላ ጭፍጨፋ ተጀመረ፡፡ … በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ ከነበሩት ኢትዮጵያውያን አንድም በሕይወት የተረፈ ሰው አልነበረም፡፡ ቦታው ላይ የተካሄደው የጅምላ ጭፍጨፋ የተሰበሰቡት ሰዎች ዕድሜያቸው የገፋ፣ ዓይነ ሥውራን፣ አካል ጉዳተኞች፣ የኔብጤዎችና ሕፃናትን የያዙ ድሃ እናቶች ስለነበሩ በዚህ ቦታ የተፈጸመው ሰቆቃ ትርጉም የሌለው፣ የሚሰቀጥጥና የሚያሳፍር ነበር፡፡›› እርመኛ አርበኞቹ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም በግራዚያኒ ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ በተሽከርካሪው ወደ ፍቼ የወሰዳቸው ስምዖን አደፍርስ ነበር፡፡

የፋሺስቶች የግፍ ሰለባ ስለሆነው ስምዖን አደፍርስ በጴጥሮስ ጳውሎስ የካቶሊክ መካነ መቃብር በሚገኘው ሐውልቱ ላይ ገድሉን እንዲህ ጽፎታል፡፡ ‹‹ወጣቱ አርበኛ ስምዖን (1905-1929) የአብርሃና የሞገስ የልብ ጓደኛ ነበር፡፡ ከአደጋውም በኋላ ከአዲስ አበባ ያሸሻቸው በታክሲ መኪናው ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ ተይዞ ደጃች ውቤ ሠፈር በግራዚያኒ ወህኒ ቤት ማቅቆ አካሉ ከሰውነቱ ውጭ ሆኖ በመርዝ ተገደለ፡፡ ዘመዶቹ በድብቅ ቀበሩት፡፡››

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...