Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአርብቶ አደሮች ከልማት ተጠቃሚነት እስከምን ድረስ?

የአርብቶ አደሮች ከልማት ተጠቃሚነት እስከምን ድረስ?

ቀን:

በኢትዮጵያ አርብቶ አደር በስፋት የሚገኝባቸው አካባቢዎች አፋር፣ ሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች ሲሆኑ፣ ደቡብና ጋምቤላም በከፊል አርብቶ አደርነት ስማቸው ይጠቀሳል፡፡

እነዚህ ቦታዎች ላይ ማዕድናት፣ ሰፊ ቦታዎች እንዲሁም ማኅበረሰባዊ ዕውቀቶች ቢኖሩም፣ ለዘመናት አርብቶ አደሩ በዚህ ሳይጠቀም በመቅረቱ እንዳያድግ ማነቆ ሆኗል፡፡

በተለይም አርብቶ አደሩ የመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ጋር በተያያዘ ፖሊሲን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳሉበት ይነገራል፡፡ ለዚህም የአርብቶ አደር የመሬት አጠቃቀምና ተያያዥ ተቋማትን አስመልክቶ በቅርቡ በአንድ መድረክ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት የፓስቶሪያሊስት ፎረም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተዘራ ጌታሁን ናቸው፡፡

ጥናቱ በዋናነት የአርብቶ አደሮች ችግሮችና መፍትሔዎቻቸውን ይዳስሳል፡፡ አርብቶ አደሮች ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዳሉባቸው ጥናቱ ያመለክታል፡፡ በዚህም ከፍ እያለ የመጣው ኢፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፣ የባህላዊ መተዳደሪያ ሥርዓቶች መዳከም፣ የመሬት መራቆት፣ የሕዝብ ብዛት እንዲሁም ለወጣቶች የሥራ ዕድል አናሳ መሆን ይጠቀሳሉ፡፡

በሌላ በኩል የአርብቶ  አደሮች አለማደግ ትልቅ ማነቆ የፖሊስና ስትራቴጂ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ተጠቃሚነታቸው ያላጎሉ የስኳር ፋብሪካዎችና መሰል ሥራዎች ሲከናወኑ ያላግባብ ከቦታው እንዲነሱ መደረጉን አቶ ተዘራ ይጠቀሳሉ፡፡

አርብቶ አደሩ ከመሬቱ ማፈናቀሉ ከ50 ዓመታት በፊት የነበረ መሆኑን የሚያስረዱት አቶ ተዘራ፣ በ2010 ዓ.ም. በተደረገ የዳሰሳ ጥናት በአዋሽ ሸለቆ 52,370 ሔክታር መሬታቸው ለአግሮ ኢንዱስትሪ ልማት ተወስዷል፡፡

የዚህ መሬት መወሰድ ማሳያ ሆነ እንጂ ብዙ መሬቶቻቸው በተለያዩ የልማት ሥራዎች በሚል ያላግባብ የተነጠቁ መኖራቸውንም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

በዋናነት አርብቶ አደሩ በምን መልኩ አካባቢው ላይ በሚገነቡ ፋብሪካዎችና መሰል ኢንቨስትንት ተጠቃሚ ማድረግ እንዲቻል ማድረግ የጥናቱ ዋና ዓላማ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የሀብቱ ተካፋይ እንዲሆንም ሼር እንዲኖረው ማድረግ፣ በአካባቢው መሠረተ ልማቶች እንዲገነቡ ማድረግና መሬቱን እንዲሸጥና እንዲለወጥ በማድረግ ይልቅ ራሱ የሀብቱ ተጠቃሚ እንዲሆን መንግሥት ማድረግ ስላለበት ነገር አቅጣጫ ያስቀምጣል፡፡

ብዙዎች የአርብቶ አደሩን ባህሪ፣ አኗኗርና ባህላዊ ዕውቀቶችን ለይቶ የማወቅ ችግር እንዳለባቸው የጠቆሙት አቶ ተዘራ፣ ከሥር ጀምሮ የአርብቶ አደሩን ገጽታ በማየት ችግሮቹን በቀላሉ መፍታት ያስችላል ይላሉ፡፡

አካባቢው በተለያዩ የገፀ ምድር ሀብት የታደገ ቢሆንም፣ ከነዋሪዎች ይልቅ ሌሎች የሚጠቀሙበት መንገድ የሚበዛ በመሆኑ እያደር አርብቶ አደሩ በድህነት እንዲኖር ምክንያት ሆኗል፡፡ ለግጦሽ፣ ለደን፣ ለአነስተኛ እርሻ ሥራና ለሌሎች አገልግሎት የሚውሉ የአርብቶ አደሮች መሬት መኖሩና በባህላዊ አስተዳደሩ ሲጠቀም መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡

የገጠር መሬት አጠቃቀም አዋጅ ቢኖርም በመሬት ላይ ያለው አተገባበር እጅግ አናሳ መሆኑን በማውሳትም በመሬት አጠቃቀም ላይ አርብቶ አደሩ በቂ ዕውቀት መስጠትና የውሳኔ አካል ማድረግ እንደሚገባም አቶ ተዘራ ያሳስባሉ፡፡ በሕግ ተደንግጎ መቀመጥ እንዳለበትም ያክላሉ፡፡

በባለሙያው አገላለጽ አርብቶ አደሩን ወደ አርሶ አደርነት ይቀየራል የሚለውን ያልተገባ አመለካከት በመተው፣ ባለበት የሚያድግበትና ከሀብቱ ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ መዘርጋት ይገባል፡፡

በዋነኛነት የመሬት የካሳ ክፍያ ጉዳይ ትኩረት የሚሻ መሆኑን የገለጹት አቶ ተዘራ፣ መብቱ እንዲከበርና ከሌሎች ዘርፎች በበለጠ አርብቶ አደሩ ለአገር የሚያደርገው አስተዋጽኦ ግምት ውስጥ ያስገባ ሥራ መሠራት እንዳለበትም ይገልጻሉ፡፡

አርብቶ አደሩ ሁልጊዜ የምግብ ዕርዳታ ጠባቂ ተደርጎ የሚታየውን እሳቤ በማስወጣት፣ በአካባቢው ካለው የገፀ በረከት ሀብት ተጠቃሚ በማድረግ ችግሩን መቅረፍ እንደሚገባ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

ለዚህም በምሳሌነት በአፋር ክልል የአፍዴራ የጨው ምርት የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ በማድረግ ኑሮው እንዲሻሻልና ከሀብቱ ተጠቃሚ ማድረግ በዋነኝነት የተነሳ ነጥብ ነው፡፡

ፖሊሲና መሰል አዋጅና መመርያዎች ሲሰናዱ ከአርብቶ አደሩን ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓትና ዕውቀት ጋር የሚመቻችና የሚናበብ መሆን እንዳለበትም ተጠቁሟል፡፡

በኢትዮጵያ ከ15 ሚሊዮን በላይ አርብቶ አደሮች የሚገኙ ሲሆን፣ ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት 60 በመቶ እንደሚደርስ ይታመናል፡፡

በ2008 ዓ.ም. የወጣ መረጃ በኢትዮጵያ አርብቶ አደርነት ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት 16 በመቶ ያበረክታል፡፡ በሌላ በኩል በአርብቶ አደር አካባቢ የሚገኙ ወጣቶች በከፍተኛ ደረጃ የሥራ ዕድል ችግር ሲኖር ከሌሎች አካባቢዎች ይልቅ የአርብቶ አደሮች አካባቢ ላይ ከፍተኛ ድህነት መንሰራፋቱ ይወሳል፡፡

በመድረኩ እንደተገለጸው፣ ይህንንም ችግር ለመፍታት መንግሥት የፖሊሲ ክፍተቶችን መፈተሽ፣ ለአካባቢ ምቹ የሆኑ የሥራ ዘርፎች እንዲኖሩ ማድረግና በአካባቢው ካለው ሀብት ተጠቃሚ ማድረግ ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ይታወቃል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...