Saturday, May 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባለይዞታዎችንና ቤት ፈላጊዎችን በማስተሳሰር 100 ሺሕ ቤቶች እንደሚገነቡ ተነገረ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ከተማ የግል መሬት ባለይዞታዎችንና ቤት ፈላጊዎችን በማቀናጀት ባይዞታዎች ባሉበት ቦታ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት፣ ከአንድ መቶ ሺሕ በላይ ቤቶችን ሊገነባ መሆኑን ጎጆ ብሪጅ ሐውሲንግ የተባለ ኩባንያ አስታወቀ፡፡

ኩባንያው የካቲት 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ባስተዋወቀው መርሐ ግብር ከሁለት ሚሊዮን ብር ባነሰና ከሁለት ዓመታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ፣ ባለሦስት መኝታ ቤቶችን ገንብቶ ለቤት ፈላጊዎች ለማስተላለፍ ሥራ መጀመሩን ገልጿል፡፡

ቅድመ ክፍያ 350 ሺሕ ብር በመክፈል የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ማኅበር አባል መሆን እንደሚቻል፣ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አልማው ጋሪ ተናግረዋል፡፡

ከተቋቋመ ሁለት ዓመታት ባስቆጠረው ድርጅት እስካሁን 2,500 የቤት ባለይዞታዎች መመዝገባቸውን፣ 300 የሚሆኑት ቦታዎች ተለይተው ለግንባታ ዝግጁ ተደርገዋል ሲሉ ዋና ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡

ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ይሆኑበታል ለተባለው ፕሮጀክት፣ ‹‹በቅርቡ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ቤት ፈላጊ ይመዘገባል ብለን እናስባለን፤›› ሲሉ አቶ አልማው ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ በተያዘው ዓመት ብቻ በአራት አካባቢዎች ማለትም ቡልጋሪያ፣ ጎሮ፣ ጣሊያን ኤምባሲና ላንቻ አካባቢዎች 1,000 ቤቶችን ለመገንባት ማቀዱን ተናግሯል፡፡

ከቤት ፈላጊዎቹ የሚሰበሰበው ገንዘብ በማኅበራቱ አካውንት እንደሚቀመጥ የተገለጸ ሲሆን፣ ጎጆ ብሪጅ ሐውሲንግ ተመጣጣኝ የሆነ የአገልግሎት ክፍያ ከባለ ይዞታዎችና ከቤት ፈላጊዎች በመጠየቅ ሥራውን እንደሚያከናውን አቶ አልማው ጠቁመዋል፡፡

ቤት ገዥዎች አስፈላጊውን ክፍያ ለባለይዞታዎች ከፈጸሙ በኋላ ቤት ገዥዎችና ባለይዞታዎች የቤት ግንባታ ማኅበር እንደሚመሠርቱ ተነግሯል፡፡

ማኅበሩ የመኖሪያ ሕንፃዎችን በጥራትና በታቀደለት ጊዜ ገንብቶ ለእያንዳንዱ የማኅበር አባል በውል መሠረት እንዲያስረክብ፣ ድርጅቱ አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡

በዚህም በከተማው መሀል የተጎሳቆሉ የመኖሪያ ቤቶችን እንደገና አፍርሶ መፈጠሩ፣ ለከተማዋ አዲስ ገጽታ እንደሚፈጥር ተገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ የቤት ፈላጊዎች ቁጥር እየጨመረ እንደመጣና የጋራ መኖሪያ ቤቶች በየጊዜው ቢገነቡም፣ ችግሩን ማቃል እንዳልተቻለ የከተማ አስተዳሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ ተናግረዋል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት ከ600 ሺሕ በላይ ቤት ፈላጊዎች ተመዝግበው እንደሚገኙና ጎጆ ብሪጅ ሐውሲንግ በአዲስ ሦስተኛ አማራጭ መምጣቱ፣ የሚያስመሰግን ነው›› ሲሉ አቶ ጥሪቱ ገልጸዋል፡፡

የከተማው ዋና ሥራ አስኪያጅ በቤት ግንባታ ዘርፍ የሚታዩ ችግሮች በተለይም የማስፈጸም አቅም ማነስ፣ ማጭበርበር፣ ሌብነትና የቅንጅት ማነስ ትልቅ ማነቆ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች