Tuesday, May 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ነዳጅ አቅራቢዎችና ቸርቻሪዎች ከቅድመ ክፍያ ጋር በተያያዘ ችግር ይፈጠራል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ገለጹ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከነዳጅ ኩባንያዎች ነዳጅ ተቀብለው የሚቸረችሩ ነዳጅ ማደያዎች፣ ‹‹በጥሬ ገንዘብ ከፍለው እንዲጠቀሙ›› የሚለው አሠራር በአገሪቱ የነዳጅ ሥርጭት ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል የሚል ሥጋት እንዳለው የነዳጅ አዳዮች ማኅበር ገለጸ፡፡

መንግሥት ለነዳጅ ኩባንያዎች ከዚህ በኋላ የሚረከቡትን ነዳጅ በጥሬ ገንዘብ ከፍለው ማሠራጨት እንደሚኖርባቸው ካስታወቀ በኋላ የነዳጅ ኩባንያዎችም የነዳጅ አዳዮች የሚቸረችሩትን ነዳጅ በጥሬ ገንዘብ ከፍለው መውሰድ እንዳለባቸው ማሳወቁ በእጅጉ እንዳሳሰባቸውም አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማኅበር የሁኔታውን አሳሳቢነት በመገንዘብ ባለፈው ዓርብ የካቲት 12 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፣ አዲሱ አሠራር ችግር ሊፈጠር የሚችል መሆኑና ከዱቤ አሠራር በቀጥታ በገንዘብ በሚከፈል አሠራር እንዲለወጥ መደረጉ ሊያስከትል የሚችለው ችግር ግንዛቤ ውስጥ መግባት እንደነበረበት ተናግሯል፡፡

ቀድሞም ቢሆን በአነስተኛ የትርፍ ህዳግ የሚሠሩ መሆኑን የሚገልጹት የነዳጅ አዳዮች ማኅበር የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ሔኖክ መኮንን፣ አሁን ደግሞ በጥሬ ገንዘብ ተረክባችሁ ቸርችሩ መባሉ የበለጠ የሚጎዳቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አንድ ቦቴ ተሽከርካሪ ነዳጅ ለማራገፍ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑና ይህንን ለመሸፈን የሚያስችል አቅም ስለሌላቸው በነዳጅ ሥርጭቱ ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል የሚል ሥጋታቸውን በመግለጽ መንግሥት ጉዳዩን በድጋሚ እንዲያጤነውም ጥሪ አድርገዋል፡፡

እንደ ማኅበሩ አመራሮች ገለጻ በዘርፉ በርካታ ችግሮች ያሉ ሲሆን በተለይ በአሁኑ ሁኔታ የነዳጅ እጥረት አለ በሚባልበት ወቅት አዲሱን አሠራር ከመጋቢት 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የሚተገበር ከሆነ ችግሩን ሊያባብሰው እንደሚችልም ሳያመላክቱ አላለፉም፡፡

እንዲህ ያለ ውሳኔ ከመወሰኑ በፊት የነዳጅ አዳዩም ችግር መታየት እንደነበረበት ያስታወሱት የማኅበሩ አመራሮች ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ቢሆንም የመንግሥት አካላት የነዳጅ አዳዮችን ለማነጋገር ያለመፈለጉ ቅር አሰኝቷቸዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ለመምከር ያደረጉትን ጥረት እንዳልተሳካላቸው አምርረው የተናገሩት የማኅበሩ አመራሮች አሁን ወደ ሚፈለገው አሠራር ለመግባት ከተፈለገ በቅድሚያ የትርፍ ህዳጋቸው ሊጨምር የሚገባ መሆኑን ነው፡፡

የትርፍ ህዳጉ ሳይጨመር በጥሬ ገንዘብ ተረከቡ የሚለው አሠራር አለመተግበር አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸውም ተናግረዋል፡፡ አሁን በሊትር ወደ 23 ሳንቲም የትርፍ ህዳግ የሚታሰብላቸው ቢሆንም ይህ በቂ ያለመሆኑና በአግባቡ ለመሥራት የትርፍ ህዳጋቸው እስከ 80 ሳንቲም ከፍ ሊል እንደሚገባም ፍላጎት እንዳላቸው አመልክተዋል፡፡

በአጠቃላይ በዘርፉ ብዙ ችግሮች አሉ የሚሉት የማኅበሩ አመራሮች መንግሥት ዘርፉን በጥልቀት መመልከትና አሠራሮቹ እንዲሻሻሉ ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበት ጭምር አመልክተዋል፡፡

በተለይ በገንዘብ ተረከቡ ከሚለው አሠራር ጋር በተያያዘ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ተገንዝቦ ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም ማድረግ ያስፈልጋል የሚል አቋም አላቸው፡፡

መንግሥት ወደዚህ ዕርምጃ የገባው አንዳንድ በቅርብ የገቡ የነዳጅ ኩባንያዎች በዱቤ የወሰዱትን ነዳጅ ሊከፍሉ ባለመቻላቸው የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅትን ጫና ላይ ስለከተተው መሆኑ ቢገለጽም በአግባቡ የሚሠሩትን በዱቤ እንዲስተናገዱና ያልከፈሉትን ደግሞ ቅድሚያ ክፍያ ከፍለው እንዲጠቀሙ በማድረግ ችግሩን መቅረፍ ይቻል እንደነበርም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ለነዳጅ ኩባንያዎች በዱቤ ሲሰጥ የነበረውን ነዳጅ በገንዘብ ከፍለው እንዲረከቡ የሚለውን ውሳኔ ለመወሰን የተገደደው አንዳንድ የነዳጅ ኩባንያዎች በዱቤ የወሰዱትን ነዳጅ ዋጋ ሊከፍሉ ባለመቻላቸው በድርጅቱ ላይ በፈጠረው ከፍተኛ ጫና መሆኑ መገለጹ አይዘነጋም፡፡  ይህም አሠራር ከመተግበሩ ቀደም ብሎ ከስድስት ወራት በላይ የመዘጋጃ ጊዜ ሰጥቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት 35 የነዳጅ ኩባንያዎች ያሉ ሲሆን ሁለቱ የውጭ ቀሪዎቹ ደግሞ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች በመላ አገሪቱ ከ800 በላይ ማደያ አላቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች