የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ቢሾፍቱ ከተማ ዓድአ ምርጫ ወረዳ 1 የፓርቲው መዋቅር የነበሩት አቶ ግርማ ሞገስ ለገሠ ላይ ለተፈጸመው ግድያ፣ መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወስድ ጠየቀ፡፡
ፓርቲው መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወስድ የጠየቀው ረቡዕ የካቲት 10 ቀን 2013 ዓ.ም. በዋና ጽሕፈት ቤቱ፣ በፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች የአቶ ግርማ ሞገስ ግድያን አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ነው፡፡
ኢዜማ በአባሉ አቶ ግርማ ላይ የተፈጸመው ግድያ ፖለቲካዊ ነው ብሎ እንደሚያምን የገለጹት የፓርቲው አመራሮች፣ ለዚህም ከዚህ ቀደም ሟቹ ይደርስባቸው የነበረውን ዛቻና ማስፈራሪያ እንደ ማስረጃ በመጥቀስ አብራርተዋል፡፡
‹‹በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች ከማኅበረሰቡ ጋር ለመወያየት፣ አባላትን ለመመልመልና ለማደራጀት በምናደርገው ሙከራ ሥራችንን ለማደናቀፍና ተስፋ ለማስቆረጥ የመንግሥትን መዋቅር ጨምሮ የተለያዩ ኢመደበኛ አካላት ሙከራ ሲያደደርጉ ቆይተዋል፤›› በማለት ፓርቲው ያስታወሰ ሲሆን፣ ‹‹ከዚህ ጋር በተያያዘም ከዚህ ቀደም በቢሾፍቱ ከተማ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ላይ የተለያዩ ችግሮች ሲጋጥሙንና አባላቶቻችን ላይ ማዋከብ ሲያጋጥመን ቆይተናል፤›› ሲል ደረሰብኝ ያለውን በደል በዝርዝር አቅርቧል፡፡
ከቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ውይይት ለማድረግ በተደጋጋሚ ያደረገው ሙከራ በከተማው አስተዳደር እንቢተኝነት መሳካት እንዳልቻለ ኢዜማ ከመግለጽ ባሻገር፣ ‹‹የምርጫ ወረዳ መዋቅራችን የሚጠቀምበት ጽሕፈት ቤትም ለመክፈት ብዙ ውጣ ውረድ ብናልፍም፣ ከከተማው አስተዳደር በሚደረግ ጫና መሳካት አልቻለም፤›› በማለት ስሞታውን አሰምቷል፡፡
በዚህ ምክንያት በከተማው ስብሰባ ለማድረግም ሆነ ጽሕፈት ቤት ለመክፈት የሚደረገውን እንቅስቃሴ የሚመሩት አቶ ግርማ፣ ከፍተኛ ዛቻና ማስፈራሪ ይደርስባቸው እንደነበር አስታውቋል፡፡
የፓርቲው ዋና ጸሐፊ አቶ አበበ አካሉ፣ ‹‹በፓርቲውና በአባላቱ ላይ በሚደርሰው ጫና ተስፋ እንድንቆርጥና ትግሉን እንድናቆም ተፈልጎ ከሆነ አይሳካም፤›› ያሉ ሲሆን፣ ‹‹ለእኛ ግርማ ለ2013 ዓ.ም. አጠቃላይ ምርጫ የመጀመርያው መስዋዕት ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ የፓርቲው ምክትል መሪ አቶ አንዱዓለም አራጌ ለግድያው መንግሥትን ተጠያቂ በማድረግ፣ ‹‹ብዙዎቹ የብልፅግና መሪዎች ሃይማኖተኞች ነን ስለሚሉ የሚያውቁትን ነገር ልጠቅስላቸው እፈልጋለሁ፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ፣ አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ አቶ ፈቃዱ ተሰማ፣ እንዲሁም ወ/ሮ ዓለም ፀሐይ ሽፈራው ወንድማችሁ ግርማ ሞገስ ወዴት አለ? ወንድማችሁ ግርማ ሞገስ ከወዴት ነው? ማን ገደለው? የወንድማችሁ ደም ወደ እናንተ ይጮኻል፤›› በማለት ጠይቀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ አቶ አንዱዓለም፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዴሞክራሲና ለፍትሐዊ ምርጫ የሚጨነቁ ከሆነ በአደባባይ ወጥተው ካድሬዎቻቸውን አደብ ያስይዙ፤›› የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ስለሆነም ፓርቲው መንግሥት የአባላቸውን ገዳይ በአስቸኳይ ለፍትሕ እንዲያቀርብ፣ ቀደም ሲል በአቶ ግርማ ላይና በሌሎች የፓርቲው አባላት ላይ ወከባና ማስፈራሪያ ሲፈጽሙ የነበሩ የቢሾፍቱ የፓርቲና የመንግሥት ኃላፊዎች የምርመራው አካል እንዲሆኑ፣ እንዲሁም ጉዳዩን ቀድመው እንዲያውቁ የተደረጉት የክልሉም ሆነ የፓርቲው ከፍተኛ ኃላፊዎች ግድያውን እንዲያወግዙ ጥያቄ አቅርቧል፡፡