Thursday, February 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በተለይ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ዳያስፖራዎች የኢትዮጵያን ገጽታ የሚያጠለሹ መረጃዎችን የማረም ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል›› ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በለውጡ ማግሥት በአሜሪካና በሌሎች የአውሮፓ አገሮች እየተዘዋወሩ ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ባነጋገሩበት ወቅት፣ ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ አንድ ጥያቄ ይቀርብላቸዋል፡፡ ጥያቄው የዳያስፖራ ሚኒስቴር ይቋቋም የሚል ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ ‹‹…ያሉትን ሚኒስቴሮች እንቀንሳለን ስንል ሌላ አዲስ ሚኒስቴር ማቋቋም ያስቸግራል፡፡ ስለዚህ ከሚኒስቴር ዝቅ ያለ የዳያስፖራ ተቋም ለማቋቋም እንሞክራለን…›› የሚል መልስ ሰጥተዋቸው ነበር፡፡ በተገባውም ቃል መሠረት ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ተቋቁሞ፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በአንድ መድረክ ለማሰባሰብ እየተሠራ ነው፡፡ ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በኢኮኖሚክስ የመጀመርያ፣ በፒስ ኤንድ ሪኮንስሌሽን ሁለተኛ ዲግሪዎቻቸውን አግኝተዋል፡፡ በአሜሪካ ለሦስት ዓመታት ያህል ኖረዋል፡፡ በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት ሆነው አገልግለዋል፡፡ ባለትዳርና የአንድ ልጅ እናት ናቸው፡፡ በኤጀንሲውና በዳያስፖራው ዙሪያ ከታደሰ ገብረማርያም ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲን አመሠራረትና ዳያስፖራ የሚባሉት እነማን እንደሆኑ ቢገልጹልን?

ወ/ሮ ሰላማዊት፡- የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር ሆኖ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በፀደቀው ደንብ የተቋቋመ ነው፡፡ የሚመራውም ቀደም ብሎ በወጣው የዳያስፖራ ፖሊሲ ነው፡፡ ፖሊሲውም ዳያስፖራን የገለጸው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን በማለት ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከሆኑ በኢትዮጵያ የሚሰጠውን ቢጫ ካርድ የያዙ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ኤጀንሲው ሁለት ዓላማዎች አሉት፡፡ አንደኛው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በያሉበት አገር ክብራቸውና መብታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ፣ አስፈላጊውን ሥራ ጉዳዩ በይበልጥ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ጋር በትብብር ማከናወን ነው፡፡ ሁለተኛው ዓላማ ደግሞ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጉዳይ ውስጥ በልማት እንዲሳተፉ፣ ወይም እያበረከቱ ያለውን ተሳትፎ በይበልጥ እንዲያሳድጉ ለማድረግ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ኤጀንሲው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በተጠቀሱት ሁለት ዓላማዎች ተግባራት ላይ ትኩረት አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኤጀንሲው የዓላማዎቹን ተግባራት ለማስፈጸም የሚያስችሉ ምን ዓይነት አካሄዶችን ነው የቀየሰው?

ወ/ሮ ሰላማዊት፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የዳያስፖራ ጉዳይ ከ15 ዓመታት በላይ ሲሠራበት የቆየ ነው፡፡ ሆኖም ብዙ ችግሮች ነበሩበት፡፡ ኤጀንሲው እንደ አዲስ ከተመሠረተ ወዲህ ግን እነዚህን ችግሮች ላለመድገም፣ ምን ዓይነት መዋቅር መዘርጋትና ምን ዓይነት ስትራቴጂና ሥልት መከተል ያስፈልጋል በሚሉት ነጥቦች ላይ ሰፊ ጥናት ተከናውኗል፡፡ ከጥናቱም በተገኘው ውጤት መሠረት አዳዲስ አካሄድ የዘረጉ አራት ዲፓርትመንቶችን ማቋቋም ግድ ሆነ፡፡ በመሆኑም የዳያስፖራ ማኅበረሰብ ልማት፣ የዳያስፖራ ተሳትፎ፣ የዳያስፖራ መረጃና ጥናት ኮሙዩኒኬሽን፣ የዳያስፖራ የሕግ ድጋፍና ከለላ ዲፓርትመንቶች ተቋቁመዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የዳያስፖራ ማኅበረሰብ ልማት ዲፓርትመንት የዳያስፖራውን አስተሳሰብ የማልማት ሥራ ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ ይህም ማለት በዳያስፖራው መካከል የተለያየ እምነት፣ አመለካከትና የፖለቲካ ልዩነቶች አሉ፡፡ እነዚህ ልዩነቶች እንዳሉ ሆነው አንድ በሚያደርጋቸው፣ ማለትም በአገር ጉዳይና ፕሮጀክቶች ላይ በጋራ እንዲሠሩ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ረገድ ይንቀሳቀሳል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን የእርስ በርስ ቅርርብ፣ ትስስርና ግንኙነት እንዲፈጥሩ፣ ከዚህም ባለፈ ቀጣይና ተከታይነት ያለው ውይይት እንዲያካሂዱ፣ አንድ ላይ እየተናበቡና እጅ ለእጅ ተያይዘው በጋራ የሚኖሩበትን ባህል እንዲያዳብሩ የማድረግ ሥራም ይከናወናል፡፡

የዳያስፖራው ተሳትፎ ዲፓርትመንት ደግሞ ዳያስፖራው ወደ አገሩ መጥቶ ለመሳተፍ በሚፈልግበት ጊዜ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡ ተሳትፏቸውም በኢንቨስትመት፣ በንግድ፣ በባንክና ሬሚታንስ፣ በበጎ አድራጎት ሥራ፣ በማስተማር፣ ዕውቀታቸውን በማካፈልና በሌሎችም ሊሆን ይችላል፡፡ ኤጀንሲው ከማንኛውም ፖለቲካ ነፃና ገለልተኛ የሆነ እንደመሆኑ መጠን፣ የተጠቀሰውም ዲፓርትመንት ይህን አካሄድ በመከተል የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት ይኖርበታል፡፡ የዳያስፖራ መረጃና ጥናት ኮሙዩኒኬሽን ዲፓርትመንት የዳያስፖራውን መረጃ ለአገር፣ በአገር ላይ ያለውን መረጃ ደግሞ ለዳያስፖራው የሚያስተላልፍና በጣም አስፈላጊ ከሚባሉ አንዱ ነው፡፡ የዳያስፖራ የሕግ ድጋፍና ከሌላ ዲፓርትመንት በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መብታቸው የሚነካና የሚጣስ፣ እንዲሁም አካላዊ ጥቃት የሚደርስባቸው ከሆነ መከላከል ወይም ጉዳቶቹ እንዳይከሰቱ የመሥራት፣ ከተጠቁም በኋላ ጠበቃ አቁሞ ተገቢ የሆነ ድጋፍ እያደረገላቸው የሚሠራ ዲፓርትመንት ነው፡፡ በተለይ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ለቤት ውስጥ ሥራ የሚሄዱ ሴቶች፣ ከአገር ከመውጣታቸው በፊት አስፈላጊውን ዕውቀትና ክህሎት ይዘው እንዲሄዱ ያደርጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በዝርዝር የተጠቀሱት ዲፓርትመንቶች የተቀመጠላቸውን የሥራ አቅጣጫ ተከትለው እንዴት ነው ዳያስፖራዎች ላይ ሊደርሱ የሚችሉት?

ወ/ሮ ሰላማዊት፡- የዳያስፖራ ሥራ በአንድ ወገን ወይም ተቋም ብቻ የሚሠራ አይደለም፡፡ ስለሆነም ለሥራው ስኬታማነት ሲባል በውጭ ካሉ ሚሲዮኖቻችን ጋር መቀናጀቱ ያስፈልጋል፡፡ በዚህም የተነሳ ኤጀንሲው በውጭ አገር ካሉ 60 ሚሲዮኖች መካከል 38 ከሚሆኑት ጋር ዓመታዊ ዕቅድ በመፈራረም በቅርበት ይሠራል፡፡ 38 ሚሲዮኖች የተመረጡት የዳያስፖራውን ቁጥር መነሻ በማድረግና ዳያስፖራዎቹ ከሚያስገኙት ጥቅም አኳያ ታይቶ ነው፡፡ የዳያስፖራ ጉዳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንዱ ሥራ እንደ መሆኑ መጠን፣ ሚሲዮኖቹም ይህንን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ኃላፊነት አለባቸው፡፡  

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ድርብ ዜግነት እንዲፈቀድ ዳያስፖራው ሲወተውት ቆይቷል፡፡ ምላሽ ግን አላገኘም፡፡ ይህንን እንዴት ይታያል? በተለያዩ አገሮች የሚኖሩና ቢጫ ካርድ የያዙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ ውስጥ በሚካሄደው ምርጫ እንዲሳተፉ በዳያስፖራ ፖሊሲ ላይ ተቀምጧል፡፡ ከዚህ አኳያ በዘንድሮ ምርጫ ለመሳተፍ እንዲችሉ ምን ዓይነት ምቹ ሁኔታ አለ?

ወ/ሮ ሰላማዊት፡- ድርብ ዜግነት በጣም አስቸጋሪና ጥናትም የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ደረጃ ፈታኝ በሆኑ የዲጂታል ቴክኖጂና የደኅንነት ጉዳዮች ላይ ብዙ መሥራት ይጠበቅባታል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ባልተከናወኑበት ሁኔታ ድርብ ዜግነትን ለመፍቀድ ያስቸግራል፡፡ በኢትዮጵያ የድርብ ዜግነት አይፈቀድም፣ የለምም፡፡ የምርጫ ካርድ የያዙ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በምርጫ ላይ እንዲሳተፉ ይደረጋል የሚል አለ፡፡ ነገር ግን ይኼ ከፍተኛ የሆነ ዝግጅት የሚፈልግ ሥራ ነው፡፡ በፖሊሲ ደረጃ የተፈቀደ ቢሆንም በዝግጅትና በተለያዩ ሲስተሞችና አሠራሮች ዕጦት ምክንያት የቆየ በመሆኑ ለዘንድሮ ምርጫ አይሳካም፡፡  

ሪፖርተር፡- ዳያስፖራው ወደ አገር ውስጥ የሚልከው ገንዘብ ሕጋዊነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለተፈለገው አካል የመድረሱ ሁኔታ ላይ ምን እየተሠራ ነው? ከዳያስፖራው አምና ምን ያህል ገቢ ተገኝቷል? ዘንድሮ ምን ያህል ይገባል ተብሎ ይገመታል? ምን ያህሉ ተሳክቷል?

ወ/ሮ ሰላማዊት፡- በዳያስፖራ ሬሚታንስ ላይ ከምንሠራቸው ሥራዎች አንዱና ዋነኛው፣ ዳያስፖራው ገንዘቡን በሕጋዊ መንግድ እንዲልክ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን ቀጣይነትና ተከታታይነት ባለው መንገድ ማከናወን ነው፡፡ ሕጋዊውን መንገድ ተከትሎ ገንዘቡን ወደ አገር ቤት የሚልክ ዳያስፖራ አገሩንምና ተቀባዩንም ይጠቀማል፡፡ በተለይ በመካከለኛ ምሥራቅ ያሉት ገንዘባቸውን በሰው እየላኩ ሲበሉ ይስተዋላል፡፡ ላክልኝ የተባለው ሰው ሳይልክ ወይም አገር ቤት ከደረሰ በኋላ ለተፈለገው ዓላማ ሳያውልለት የሚቀርበት ጊዜ አለ፡፡ በሕጋዊ መንገድ መጠቀሙ ለዳያስፖራው ብቻ ሳይሆን ለአገርም ጠቀሜታ አለው፡፡ በጥቁር ገበያ በኩል የሚተላለፍ ገንዘብ ለተለያዩ አጥፊ ድርጊቶች ሊውል ይችላል፡፡

ይህም ማለት ሳናውቀው በገንዘባችን አገር እንድትፈርስ እያደረግን ነው ማለት ነው፡፡ ይህንን ዓይነቱን እኩይ ተግባር ለመስበርና ዳያስፖራው በሕጋዊ መንገድ ተጠቅሞ ገንዘቡን እንዲልክ ለማድረግ እንዲቻል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እያከናወንን ነው፡፡ ጎን ለጎን ከባንኮችና በዚህ ዘርፍ ከሚንቀሳቀሱ ተቋማት ጋር በጋራና በቅንጅት እየሠራን ነው፡፡ አምና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ውስጥም ሆነን ከዳያስፖራው ብቻ 3.7 ቢሊዮን ዶላር ወደ አገር ቤት ገቢ ተደርጓል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ወደ አራት ቢሊዮን ዶላር ለማስገባት ተፈልጎ በአምስት ወራት ውስጥ ብቻ የኮቪድ ተፅዕኖ እንዳለ ሆኖ ወደ 1.4 ቢሊዮን ዶላር ገብቷል፡፡ ይህ ይቀጥላል ብለን ነው የምናምነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዳያስፖራው ወደ አገር ቤት ገንዘቡን የሚልክባቸው የተለያዩ ዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ኩባንያዎች ገንዘብ ለማስተላለፍ የሚጠይቁት ኮሚሽን በጣም ውድ ከመሆኑ የተነሳ፣ በኩባንያዎቹ በኩል ከመላክ ተቆጥቧል፡፡ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?

ወ/ሮ ሰላማዊት፡- ሕጋዊ የመላኪያ መንገዶች በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ይህንንም የሚያከናውኑ ኩባንያዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ዳያስፖራው በዚህ በኩል እክል ቢገጥመውም ወይም የቱን ያህል ቢጎዳም፣ ግዴለም ገንዘቤ ደኅንነቱ ተጠብቆ ወደ አገር ቤት ይገባል ወደሚል መተማመኛ ላይ ሊደርስና ሊመጣ ግድ ይላል፡፡ በተረፈ የተጠቀሰውን ወጪ ለመቀነስ ሲባል ኤጀንሲዎችና ባንኮቻችን ከእነዚህ ኩባንያዎች ጋር በቅርበት ሊሠሩ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- በተለያዩ የውጭ አገሮች የሚኖረው ዳያስፖራ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ ለገበታ ለአገር፣ ተፈናቃይ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም፣ ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍና ለሌሎችም የልማት ፕሮጀክቶች እያደረገ ያለው ድጋፍ በምን ይገለጻል?

ወ/ሮ ሰላማዊት፡- ከአገራዊ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱና ዋነኛው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት ትልቅ ከመሆኑም አንፃር ዳያስፖራው ቀደም ብሎ ተገቢውን ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ነገር ግን በመካከሉ በህዳሴው ግድብ ላይ በተፈጠረው ችግርና በታዩት የአሠራር ግድፈቶች የተነሳ ዳያስፖራው ላይ ጥርጣሬ ተፈጥሮበት ነበር፡፡ ይህም በመሆኑ እንደገና ወደ ድጋፉ እንዲመለስ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡ በተለይም የመጀመርያው ሙሌት ከታየ በኋላ የግድቡ ሥራ በተለየ መንገድ መቀጠሉን የሚያሳዩ መረጃዎችን በማሠራጨት ዳያስፖራው ድጋፉን እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡ ይህም የሆነው ልዩ ፕላን ቀርፀን በመንቀሳቀሳችን ነው፡፡ ገንዘብ የማሰባሰቡ ሥራ ከዚህ በፊትም የተጀመረ በመሆኑ እኛ የሠራነው መረጃ የመስጠትና የሞብላይዜሽን ሥራ ነው፡፡ ዘንድሮ አምና ከነበረው ወደ 43 በመቶ በላይ የጨመረ ዓይነት ድጋፍ ነው የተደረገው፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 90 ሚሊዮን ብር ከቦንድ ሽያጭና ከድጋፍ ተሰብስቧል፡፡ የገበታ ለአገርን በምናይበት ጊዜ እስካሁን ዳያስፖራው 27 ሚሊዮን ብር አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በቅድሚያ አሜሪካ ውስጥ ዳያስፖራው የኮቪድ-19 ፕሪቬንሽን ካውንስል ማቋቋሙ አይዘነጋም፡፡ በካውንስሉ አማካይነት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በየሳምንቱ የመረጃ ልውውጥ ያደርግ ነበር፡፡ ከዚህም ሌላ ወረርሽኙ ከታየበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ሞቢላይዝ አድርጓል፡፡ ከዚህም ገንዘብ ውስጥ 200 ሚሊዮን ብር የተሰበሰበው ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ነው፡፡ ገንዘቡም ሊሰበሰብ የቻለው ኮቪድ-19 ከመከላከል አኳያ በአገር ውስጥ ገንዘብ የሚሰበስው ብሔራዊ ኮሚቴ ባወጣው መመርያና የፕሮጀክት አፈጻጸምን አካሄድ በተከተለ መንገድ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ የሕግ ማስከበሩን አስመልክቶ የገንዘብ አሰባሰቡ ሥራ የተካሄደው ለየት ባለ መልክ ነው፡፡ ለየት የሚያደርገውም ገንዘብ የማዋጣቱ ፍላጎት የመጣው ከዳያስፖራው መሆኑ ነው፡፡ የተፈናቀሉትን ማቋቋም፣ የተጎዱትን መርዳት አለብን፣ ዝም ብለን መቀመጥ አይገባንም የሚለው በጎ ሐሳብ፣ ተነሳሽነትና ግፊት የመጣው ከሁሉም ዳያስፖራ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች ከዳያስፖራው እየመጡ ነው በማለት፣ ኤጀንሲው በአገር ውስጥ ለተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ አሳወቀ፡፡ ኮሚቴውም ከዳያስፖራው ያስፈልጋሉ ብሎ በዝርዝር የያዛቸውን በተለይም በአገር ውስጥ በአጭር ጊዜ የማይገኙ የሕክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን በዝርዝር አቀረበ፡፡ እነዚህን ዝርዝር ይዘን ለዳያስፖራው አስተላለፍን፡፡ ዳያስፖራውም በገንዘብና በዓይነት ሊረዳ ወይም ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚችል አረጋገጠልን፡፡ በዚህም መሠረት በአንድ ወር ብቻ ከ100.7 ሚሊዮን ብር በላይ ሊሰበሰብ ተችሏል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያን በጎና መልካም ገጽታ ጥላሸት ለማልበስ የተለያዩ የውጭ ኃይሎችና አንዳንድ ዳያስፖራዎች ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላሉ፡፡ ይህን ተግባር ለማክሸፍ በዳያስፖራው በኩል ምን እየተደረገ ነው?

ወ/ሮ ሰላማዊት፡- በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመረጃ ማዕከል አለን፡፡ ማዕከሉ የሚያወጣው መረጃ በእውነተኛነትና በትክክለኛነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ስለሆነም ይህን መረጃ በመጠቀም ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ ዳያስፖራው እንዲያውቀው እንሠራለን፡፡ የተላከላቸውን መረጃ መሠረት በማድረግ በተለያዩ ቋንቋዎች ስለኢትዮጵያ እንዲጽፉ፣ እንዲናገሩ፣ ትዊት እንዲያደርጉ እናበረታታቸዋለን፡፡ በተለይ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ዳያስፖራዎች ታክስ ከፋይ እስከሆኑ ድረስ ያሉበት አገር ባለሥልጣናት ስለኢትዮጵያ የሚጽፉትን የመከታተል፣ በሐሰት ላይ የተመሠረተ ወይም ትክክል ካልሆነ የማረምና በምትኩ እውነቱን የማሳወቅ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡ ማብራሪያ የሚያስፈልገውም ከሆነ ያብራራሉ፡፡ ለዚህም የተለያዩ ቋንቋዎችን በመጠቀም የኢትዮጵያን በጎ ገጽታ በማንፀባረቅ ለማገዝ የተቋቋሙ የተለያዩ ቡድኖች አሉ፡፡ እነዚህን  ቡድኖች ለመደገፍ፣ ለማገዝና መረጃ ለመስጠት በእኛ በኩል የተቻለውን ሁሉ አያደረግን ነው፡፡ በተለያዩ አገሮች ያሉት ዳያስፖራዎች ደግሞ ይህን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በጣም ወሳኝ የሚባለውን ወቅት እያለፈች ነው፡፡ በዚህም ወቅት ጠላቶቻችንን ደግፈው ወይም ከኢትዮጵያ ጥቅም ተቃራኒ ሆነው የሚንቀሳቀሱ አገሮች፣ አካላትና ግለሰቦች የሚነዙትን የሐሰት ፕሮፓጋንዳ እግር በእግር እየተከታተሉ ማፍረስ፣ በምትኩ ትክክለኛውንና እውነታውን ማንፀባረቅ ለነገ ተብሎ መታየት የሌለበት ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ውሸቱ ተጋልጦ እውነቱ እስከሚወጣ ድረስ አገሪቱ የምታገኘውን ጥቅም  እንዳታጣ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ዘንድሮ እንደ ቀድሞው ጊዜ ሳይሆን በአንድ ትዊት በጣም ብዙ ነገር ይገለባበጣል፡፡ ይህንን እየተከታተሉ በደንብ ማስተካከል ይገባለ፡፡ እኛም ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› የሚል ዘመቻ ጀምረናል፡፡ የትዊተር ዘመቻም በየቦታው እየተካሄደ ነው፡፡ ይህም በስፋትና በተጠናከረ መንገድ መቀጠል አለበት፡፡ በተለይም እየተካሄደ ያለውን የሕግ ማስከበሩን ሥራ ሰብዓዊነት በተሞላበት መንፈስና ዜጎችን በማይጎዳ ሁኔታ መሆኑን በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሣይኛና በዓረብኛ በማስተላለፍ ዳያስፖራው ውጤታማ ሥራ እያከናወነ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ የፓርላማ አባላትና ሚኒስትሮች የኢትዮጵያን ገጽታ የሚያበላሹና የተሳሳተ ትዊት በሚያደርጉበት ጊዜ፣ ዳያስፖራው ከሥር ከሥር እየተከታተለ እዚህ ላይ ተሳስተዋል፣ የያዙት መረጃ ትክክል አይደለም እያለ የማረምና የማስተካከል ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ ለመሳተፍ የሚመጡ ዳያስፖራዎችን እንዴት አድርጋችሁ ነው የምታስተናግዱት? ለዚህስ ምን ምቹ ሁኔታ ፈጥራችኋል?

ወ/ሮ ሰላማዊት፡- አገሬ ውስጥ ኢንቨስት አደርጋለሁ ብሎና ሀብት ይዞ የሚመጣውን ሰው ሁሉ በተቻለ መጠን እንደግፋለን፡፡ ሁኔታዎችንም እናመቻቻለን፡፡ በዚህም ላይ የተወሰኑ ለውጦች አድርገናል፡፡ ቀደም ሲል ኢንቨስት ለማድረግ የሚመጣውን ሰው ጉዳዩ ወደሚመለከተው አካል ተገቢውን ትብብር አድርጉለት የሚል የድጋፍ ደብዳቤ ብቻ ነበር የምንጽፈው፡፡ አሁን ግን ኢንቨስት ለማድረግ የሚመጣው ሰው ፕሮጀክቱን ይዞ እንዲመጣ እናደርጋለን፡፡ ፕሮጀክቱ ካፒታል ይኖረዋል፡፡ ስለሆነም ካፒታሉን እንገመግማለን፡፡ ከገመገምን በኋላ የካፒታሉ ከ25 እስከ 30 በመቶ ያህሉ በውጭ ምንዛሪ በአገር ቤት እንዲገባ ይደረጋል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ወደሚመለከተው የምንመራው፡፡ ከዚህም ሌላ ፕሮጀክቱ በአካባቢው ያለውን ፍላጎት ያሟላል ወይ የሚለውንም እናየያለን፡፡ አንዳንዱ በጣም ሰፊ መሬት ይፈልግ ይሆናል፡፡ ያ ሰፊ መሬት ደግሞ በዚያ ክልል ላይኖር ይችላል፡፡ እንደዚህ ዓይነቱን ችግር ከክልሎች ጋር ሆነን እናጠናለን፡፡ ከዚህም  ሌላ በየክልሉ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቶች አሉን፡፡ ጽሕፈት ቤቶቹም በየክልሉ ያሉትን አቅሞች በየዓመቱ ያሳውቁናል፡፡ ባለው አቅም መሠረትም ኢንቨስተሩን ወደ ሥፍራው እንልካለን፡፡ የተሳካለትም ክልል በአግባቡና በሕጉ መሠረት ያስተናግደዋል፡፡ በዚህ መንገድ መሥራት ከጀመርን ወዲህ ያጋጠመን ችግር የለም፡፡ የምንልካቸው ሰዎች ሁሉ በቀጥታ ወደ ሥራ የሚገቡበት ዕድል ነው ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- አዲስ አበባ ውስጥ ለ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች መቶ በመቶ ከፍለው ቤት የተነፈጉ፣ እንዲሁም ከሪል ስቴት የሚፈለገውን ሁሉ ካሟሉ በኋላ በተለያዩ ሰበቦች ሳይረከቡ የቆዩ ዳያስፖራዎች አሉ፡፡ በዚህ ላይ ያለዎትን አስተያየት ቢያካፍሉን?

ወ/ሮ ሰላማዊት፡- ቤቶችን አስመልክቶ በአጠቃላይ 40/60 ላይ ዳያስፖራ መሳተፉ አይካድም፡፡ በተለይ በሪል ስቴት ዘርፍ የተሳተፉት ዳያስፖራዎች ከ50 በመቶ በላይ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በ40/60 እና በሪል ስቴት በውጭ ምንዛሪ እየቆጠቡና መቶ በመቶ ከፍለው የተረከቡ ወይም የተጠቀሙ እንዳሉ ሁሉ፣ ከፍተኛ ችግር የደረሰባቸውም እንዳሉ መዘንጋት የለበትም፡፡ እዚህ ውስጥ የእኛ ድጋፍ  ቤት ለመሥራት የሚመጣውን ከከተማ አስተዳደሮችና ከክልሎች ጋር ማገናኘት ነው፡፡ አስተዳደሮቹና ክልሎቹ ደግሞ ዳያስፖራው ያለውን የገንዘብ አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት ያስተናግዷቸዋል፡፡ በተረፈ በኢትዮጵያ የመኖሪያ ቤት ችግር አለ፡፡ ከዚህ ችግር ለመላቀቅ በመንግሥት የሚሠሩ ቤቶች እንዳሉ ሆነው፣ በግሉ ዘርፍም የሚሠሩ ቤቶች ቁጥር በጣም መጨመር አለበት፡፡ ከዚህም ሌላ ወደ ጎን ብቻ ሳይሆን ወደ ላይ የሚሠሩ ቤቶች ላይ ትኩረት መደረግ አለበት ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ አበባንና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በአሥር ክልሎች ውስጥ 12 የዳያስፖራ ማኅበራት ተቋቁመዋል፡፡ የተጠቀሱትን ማኅበራት የሚያሰባስብ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበራት ኅብረት ተቋቁሟል፡፡ የኤጀንሲው ሚና ምን ነበር?

ወ/ሮ ሰላማዊት፡- ማኅበራቱም ሆነ ኅብረቱ ተቋቁመው አሁን ያሉበት ደረጃ ሊደርሱ የቻሉት በኤጀንሲው ጥረትና ሰፊ ድጋፍ ነው፡፡ አሁን ደግሞ የዳያስፖራ አማካሪ ምክር ቤት ለማቋቋም እናስባለን፡፡ የማቋቋሙ ሥራ ደግሞ በኤጀንሲው ደንብ ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ አሥራ ሁለቱም ማኅበራት በምክር ቤቱ ውስጥ ከአምስት እስከ ሰባት የሚሆኑ መቀመጫዎች ይኖራቸዋል፡፡ ምክር ቤቱም መንግሥትን የማማከር ተግባር ያከናውናል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተተገበረው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማ ነው ለማለት ያስቸግራል›› አቶ አሰግድ ገብረመድህን፣ የፋይናንስ ባለሙያና አማካሪ

የዓለም ኢኮኖሚ በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ የእያንዳንዱን አገር በር አንኳኩቷል፡፡ መንግሥታት ይህንን ችግር ለማርገብ የተለያዩ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ...

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...

‹‹የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም›› አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በኢኮኖሚክስ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕቅድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለ36 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፍ...