Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፀሐይ ባንክ ከ730 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ይዞ ተመሠረተ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የተፈረመ ካፒታሉ ወደ ሦስት ቢሊዮን ብር ደርሷል

በቅርቡ የባንክ ኢንዱስትሪውን ይቀላቀላሉ ተብለው ከሚጠበቁ ባንኮች ውስጥ አንዱ የሆነው ፀሐይ ባንክ 734.7 ሚሊዮን ብር የተከፈለና 2.9 ቢሊዮን ብር የተፈረመ ካፒታል ይዞ ተመሠረተ፡፡

ጥቅምት 12 ቀን 2013 ዓ.ም. የባንኩ የምሥረታ ጠቅላላ ጉባዔ በተደረገበት ወቅትም፣ ባንኩን የሚመሩ የመጀመርያዎቹ የቦርድ አባላት ተመርጠዋል፡፡ ፀሐይ ባንክ እስካሁን ሥራ ላይ ከሚገኙትና በምሥረታ ላይ ካሉት ባንኮች ለየት ባለ መንገድ ሽያጩን ከ100 ሺሕ ብር በመጀመር ሽያጭ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡  

በኢትዮጰያ የአክሲዮን ሽያጭ ሒደት አነስተኛ ዋጋ ተብሎ ሲሰጥ የነበረው የ50 ሺሕ ብር አክሲዮን የነበረ ሲሆን፣ ፀሐይ ባንክ አነስተኛ የአክሲዮን ሽያጩን በመቶ ሺሕ ብር በመጀመር መሸጡ፣ የባንኩን አብዛኛው ባለአክሲዮኖች በንግዱ ዓለም ውስጥ ያሉ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡

የባንኩ ባለአክሲዮኖች ቁጥር 373 ብቻ ሲሆን፣ ይህም ኢንዱስትሪው ውስጥ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ባለአክሲዮኖችን ያሰባሰበ ባንክ እንዲሆን አስችሎታል፡፡

ዝቅተኛውን የአክሲዮን ሽያጭ 100 ሺሕ ብር እንዲሁም ከፍተኛውን 100 ሚሊዮን ብር በማድረግና የአገልግሎት ክፍያውን ከአምስት በመቶ ወደ ሁለት በመቶ በማውረድ አክሲዮን ገዥዎችን ለማበረታታት የተቀየሰው የሽያጭ ስትራቴጂ በሁሉም ባንኮች ስኬታማ የሆነ የአክሲዮን ሽያጭ ለማከናወን ማስቻሉም ተገልጿል፡፡

የአክሲዮን ማኅበሩ የተፈረመ ካፒታል 2.93 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም በንግድ ሕጉ አንቀጽ 312 መሠረት እያንዳንዳችው 1,000 ብር በሚያወጡ አክሲዮኖች የተከፋፈለ እንደነበር ተገልጿል፡፡ ከተፈረሙት አክሲዮኖችም ቢያንስ 25 በመቶ የተከፈለባቸው ናቸው ተብሏል፡፡

ፀሐይ ባንክ አክሲዮን ማኅበር በባንክ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ኢንቨስት በማድረግ የተመሠረተው በፋይናንሱ ዘርፍ ውስጥ ያለውን መሠረታዊ የባንክ አገልግሎት ፍላጎትና አቅርቦት ክፍተት በመገንዘብ መሆኑን የባንኩ አደራጆች ገልጸዋል፡፡

ምሥረታውን አስመልክቶ ከተሰጠው መረጃ መረዳት እንደተቻለው፣ ባንኩ በቅርቡ ወደ ሥራ የሚገባ ሲሆን፣ ሥራ በሚጀምርበት በመጀመርያው ዓመትም 20 ቅርንጫፎችን በአዲስ አበባና በክልሎች ይከፍታል፡፡

ከምሥረታ ጉባዔው በኋላ ፀሐይ ባንክ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለባንክ ተደራሽነት፣ አካታችነትና ለኢኮኖሚው ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚሠራ መሆኑን የሚያመለክተው የባንኩ መግለጫ፣ ለመካከለኛና አነስተኛ የንግድ ሥራዎች፣ ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚና ለአምራች ኢንዱስትሪው አስተማማኝ አገልግሎት በመስጠት እንደሚሠራና በባንክ ፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተት ግምት ውስጥ በማስገባት የበኩሉን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አበርክቶ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡

የአገልግሎት አሰጣጥ በማዘመንና በማሻሻል፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተላብሶ ከመደበኛው የባንክ አገልግሎት በተጨማሪ የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎት፣ በካፒታል ገበያ ላይ የሚሳተፍ ሲሆን፣ በሕግ የተፈቀዱ ነፃ የባንክ አገልግሎት ጨምሮ ፈርጀ ብዙ የባንክ አገልግሎት የማቅረብ ዓላማ ይዞ እንደተመሠረተ የባንኩ አደራጆች ገልጸዋል፡፡

በዓለም ባንክ በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣ በአገራችን የባንክ አገልግሎት ተደራሽነት ብዙ ይቀረዋል፡፡ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ ከሚገኙ ጎረቤት አገሮች ጋር ሲታይ ብዙ መሥራት ይገባል፡፡

በንፅፅር ደግሞ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በጥቅል አገራዊ ምርት ሲለካ ከምሥራቅ አፍሪካ ግዙፍ ከመሆኑ አንፃር በባንክ ሥራ ዙሪያ ብዙ ሊሠራ እንደሚገባም የባንኩ መሥራቾች ገልጸዋል፡፡

ባንኩ ባዘጋጀው የአዋጪነት ጥናት መሠረት የፀሐይ ባንክ ራዕይ ጠንካራ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ዕድገት ሞተር በመሆን ዕድገት ተኮር ለሆኑ አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ የንግድ ተቋማት ዕገዛ በማድረግ ለባለአክሲዮኖች ጠቅም ያለ ትርፍ ማስገኘት መሆኑንም ይጠቅሳል፡፡

እስከ ምሥረታው ዕለት ድረስ ያለውን የፋይናንስ አፈጻጸም በተመለከተ ከቀረበው ሪፖርት መረዳት እንደተቻለው፣ ከአክሲዮን ሽያጩ መሰብሰብ የሚገባው 58.6 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ የተሰበሰበው ግን 25.2 ሚሊዮን ብር ወይም 43 በመቶው መሆኑን ገልጿል፡፡ ከተሰበሰበው የአገልግሎት ክፍያ እስካሁን ለሥራ ማስኬጃ የወጣ 2.09 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ለባለክሲዮኖቹ ተገልጿል፡፡ ከዚህ የአገልግሎት ክፍያ ውስጥ ከወጪ ቀሪ የሆነው ገንዘብ ብር 2,314 ሚሊዮን ብር በተለያዩ ባንኮች ይገኛልም ተብሏል፡፡

በምሥረታው ላይ እንደተገለጸው፣ በንግድ ሕጉ አንቀጽ 310 ላይ አደራጆች የአክሲዮን ማኅበሩን ለማቋቋም ኃላፊነት ስለወሰዱ፣ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ዕውቀታቸውን አስተዋጽኦ ስላደረጉ ከዓመታዊ የተጣራ ትርፉ ላይ ከ20 በመቶ ያልበለጠ እስከ ሦስት ዓመት ድረስ የትርፍ ወሰን እንዲያገኙ የሚደነግግ በመሆኑ ይህ ተፈጻሚ እንዲሆንም ተወስኗል፡፡

ለአደራጆች ይህንን መብት የሰጠ ቢሆንም፣ ኮሚቴው ሰፊ ውይይት በማድረግ ባንኩ የሚያተርፈው ትርፍ በባለ አክሲዮኖች መሀል ልዩነት ሳያደርግ ለአደራጅ ተብሎ ትርፉ ሳይሸራረፍ ለባለአክሲዮኖች በሙሉ ጠቅላላ ጉባዔው በሚወስነው መሠረት እንዲከፋፈል የሚል ውሳኔም አሳልፈዋል፡፡ አደራጅ ኮሚቴው በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ባንኩን ለመመሥረት የሚያስፈልገውን ሥራ ሁሉ በማጠናቀቁ በአክሲዮን ሽያጭ ጊዜ ከተሰበሰበው ሁለት በመቶ የአገልግሎት ክፍያ ላይ ለእያንዳንዳቸው የተጣራ 300 ሺሕ ብር እንዲከፈል ለጉባዔው የቀረበውን ሐሳብ ባለአክሲዮኖቹ እንዳፀደቁትም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በምሥረታው ላይ ባንኩን በቦርድ አባልነት የሚመሩ 12 አባላት ተመርጠዋል፡፡ የባንኩ የቦርድ አባላት በመሆን የተመረጡት፣ ንዋይ ዘርጌ (ዶ/ር)፣ አቶ ታዬ ዲበኩሉ፣ አቶ ባለው መርሻ፣ አቶ ታደሰ አየነው፣ አቶ ልመንህ እምሩ፣ አቶ ሽመልስ ተቋመብርሃን፣ ዘንዘልማ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ አቶ ገደፋው ባዬ፣ እልልታ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ግሎባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ፀሐይ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር እና አቶ በዕውቀቱ አላምረው ናቸው፡፡

የማደራጀት ሥራው በቀድሞ የኅብረት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ታዬ ዲበኩሉ የሚመራ የነበረ ሲሆን፣ በአዲሱ የቦርድ አባላት ምርጫም ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት አቶ ታዬ ተካተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች