Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በእጅ በእጅ ሽያጭ ውሳኔና የነዳጅ ቸርቻሪዎች ሥጋት

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቅርቡ መንግሥት ከዚህ ቀደም ለነዳጅ ኩባንያዎች በዱቤ ይሰጥ የነበረውን ነዳጅ ከመጋቢት 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በጥሬ ገንዘብ በመክፈል መውሰድ እንደሚገባቸው ማሳወቁ ይታወሳል፡፡

ይህንን የመንግሥት ውሳኔ ተከትሎም የነዳጅ ኩባንያዎች ለነዳጅ አዳዮች እነሱም በዱቤ እንደሚሰጡ በደብዳቤ እያስታወቋቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማኅበር አስታውቋል፡፡ ይህ ዕርምጃ ግን በነዳጅ እንደላው ላይ ተፅዕኖ ከመፍጠሩም በላይ የነዳጅ አዳዮች የጉዳዩ ባለቤት ቢሆኑም፣ ጉዳዩን እንደ ባለድርሻ ቆጥረው እንዲመክሩበት ባለመደረጉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

የጉዳዩን አሳሳቢነት በአጠቃላይ በነዳጅ እደላና አሠራር ዙሪያ ያሉ ችግሮችን በዝርዝር ባቀረቡበት ጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ እንዳመለከቱት፣ መንግሥት ዘርፉን መፈተሽ ጭምር ያለበት መሆኑን የጠቀሰበት ነው፡፡    

እንዲህ ያለው ውሳኔ ሲወሰን የእኛ ማኅበር መሳተፍ ነበረበት የሚሉት የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች፣ ነገር ግን በዱቤ ሽያጩ ላይ እኛ አንድንመክርበት አለመደረጉ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ወደዚህ ውሳኔ የገባው የዱቤ ሽያጩ ችግር አስከትሎበት ሊሆን ይችላል ያሉት የቦርድ ሊቀመንበሩ አቶ ሔኖክ መኮንን ከኢትዮጵያ ነዳጃ ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ በተገለጸው መሠረት፣ አንዳንድ በቅርቡ ወደ ሥራ የገቡ ኩባንያዎች በዱቤ የወሰዱትን ነዳጅ ሊከፍሉ አልቻሉም በሚል የእጅ በእጅ ሽያጩ ተፈጻሚ እንዲሆን መወሰኑን አስታውሰዋል፡፡ ኩባንያዎቹ ዱቤውን ያለመክፈላቸው የነዳጅ ድርጅትን ሥራ ማስኬጃ ጭምር ያስተጓጎለ ነበር፡፡

አዳዲስ የተባሉት ኩባንያዎች በዱቤ ወስደው ያለመመለሳቸው ችግር መፍጠሩ ከታወቀ ሊከፍሉ ያልቻሉትን ኩባንያዎች በገንዘብ ሥርዓት እንዲጠቀሙ ማድረግና ነባሮቹ ግን በነበረው አሠራር ቢቀጥሉ ኢንዱስትሪው ያለ ችግር ሊጓዝ ይችል እንደነበር ያምናሉ፡፡ ይህም ካልሆነ የነዳጅ አዳዮች ያሉበት ምክክር ተደርጎ ወደ ገንዘብ ሥርዓቱ የሚገባበት አሠራር መመቻቸት ይችል ነበር ብለዋል፡፡ በአዲሱ ውሳኔ መሠረት ከመጋቢት 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ብር 10 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ፣ ቀጥሎም 25 በመቶ እያለ በዓመቱ ማጠቃለያ ላይ 100 በመቶ በገንዘብ ክፍያ ሽያጩ እንዲያከናውን የሚያደርግ ነው፡፡

በዚሁ ውሳኔ መሠረት አንዳንድ የነዳጅ ድርጅቶች ለነዳጁ አንዳንዶቹ እንዳሳወቁት፣ ከመጋቢት 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የ80 በመቶ ክፍያ ካልፈጸሙ ነዳጅ የማይቀርብላቸው መሆኑ እጅግ እንዳሳሰባቸውና በነዳጅ ሥርጭቱ ላይ ችግር እንደሚፈጥር አሳውቀዋል፡፡ እንደ ቦርድ ሊቀመንበሩ ገለጻ ይህ አሠራር መተግበሩ አደጋ ይኖረዋል የሚለው ሥጋታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡

የዱቤ ሽያጭ መቅረትና ሥጋቱ

ለዓመታት በዱቤ ሽያጭ ሲሠሩ በቆዩበት ወቅት በቂ የትርፍ ህዳግ ሳይኖር አሁን በጥሬ ገንዘብ ይሁን ሲባል ያለው የትርፍ ህዳግ አነስተኛ በመሆኑ ከምናወጣው ገንዘብ ጋር ተመጣጣኝ ስላልሆነ ለነዳጅ አዳዮች በጣም አስቸጋሪ ይሆናል በማለት አቤት ቢሉም ከመንግሥት የተሰጣቸው ምላሽ አለመኖሩን የማኅበሩ አመራሮች በምሬት ይገልጿል፡፡

አዲሱ አሠራር በሚተገበርበት ጊዜ አንድ ነዳጅ ማደያ ለሚወያጣው ጥሬ ገንዘብ ተመጣጣኝ ትርፍ ካላገኘ ሥራውን ለመቀጠል ያስቸግራልም ብለዋል፡፡ ስለዚህ ከሁኔታው አሳሳቢነት አንፃር መንግሥት አስቸኳይ መፍትሔ ሊሰጠን ያሉት የማኅበሩ አመራሮች፣ ከዚህ በኋላ ነዳጅ በጥሬ ገንዘብ ነው የሚቀርብላችሁ መባሉን የማይቃወሙ ቢሆንም፣ በጥሬ ገንዘብ የሚተገበር ከሆነ ግን ለምናወጣው ወጪ ተመጣጣኝ ትርፍ ህዳግ ሊሰጠን ይገባል ይላሉ፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ አደዲሱ አሠራር ከመተግበሩ በፊት በቂ ጊዜ ሊሰጥ እንደሚገባና የነዳጅ ሥርጭቱ እንዳይስተጓጎል ጉዳዩ በንግግር እንዲፈታ ጊዜ መስጠት እንዳለበትም ያምናሉ፡፡

በሁለት ወራት ብቻ የነዳጅ ዋጋ በ20 በመቶ መጨመሩን በማስታወስም ይህም የሥራ ማስኬጃ ወጪያቸውን የሚጨምር በመሆኑ ሥራውን ለመሥራት ከባድ ያደርገዋል በማለትም ሠግተዋል፡፡ መንግሥት በዱቤ ያቀርብ የነበረውን የነዳጅ ሽያጭ ወደ ገንዘብ ሞዳሊቲ መቀየሩን ለነዳጅ ኩባንያዎቹ በደብዳቤ ማሳወቁን በመጥቀስ አስተያየታቸውን የሰጡበት የማኅበሩ የቦርድ አባል የሆኑት አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ ደግሞ ለዚህም በቂ የዝግጅት ጊዜ መስጠቱንም ይገልጻሉ፡፡

ሆኖም ይህ ውሳኔ በቀጥታ ከነዳጅ አዳዮች ጋር የሚገናኝ ነገር አይደለም፡፡ የኩባንያዎቹና የነዳጅ አቅራቢዎቹ ስምምነት ነው፡፡ ነገር ግን በኩባንያዎቹ በመንግሥት መካከል የተደረሰው ስምምነት በቀጥታ እንዲያርፍ የተደረገው ነዳጅ አዳዮቹ ላይ ነው፡፡ ይህንን የነዳጅ ኩባንያዎቹም የነዳጅ አዳዮቹን በጥሬ ገንዘብ ትወስዳላችሁ የሚለውን ተከትለውም 100 በመቶ ከፍላችሁ ነዳጁን ተወስዳላችሁ እያሉ እያሳወቁ በመሆኑ ይህንን ቅድመ ክፍያ ከፍሎ ነዳጁን ማሠራጨት ከባድ መሆኑንም አሳውቀዋል፡፡ እስካሁን የክፍያ ሥርዓት ለውጥ ስለመደረጉ ያላሳወቀው ኖክ ብቻ መሆኑን የገለጹት አቶ ኤፍሬም፣ ሌሎቹ ኩባንያዎች ግን ከፍላችሁ ውሰዱ በማለታቸው አሠራሩን አስቸጋሪ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ አሁን ይጀመራል በተባለው አሠራር መሠረት የሚያሠራጩትን ነዳጅ ቀድሞ በመክፈል የሚሠራው ሥራ ተጨማሪ ወጪ የሚያስፈልገው በመሆኑ አሁን ያለው የትርፍ ህዳጉ አያዋጣንም ብለዋል፡፡ በትርፍ ህዳግ ዙሪያ ከመንግሥት ጋር ያልተግባባንባቸው ጉዳዮች አሉ የሚሉት አቶ ኤፍሬም፣ ዘርፉ በቂ የሆነ የትርፍ ህዳግ አልተሰጠውም፡፡ በቅርብ ግን በስንት ውትወታና ልመናም ጭምር የተወሰነ ጭማሪ መደረጉን በመግለጽም የተደረገው የትርፍ ህዳግ ጭማሪ ያለውን ዋጋ ግሽበት ያላገናዘበ ነው ብለው ይሞግታሉ፡፡ የትርፍ ህዳጉ እጅግ አነስተኛ በመሆኑ የነዳጅ አዳዮች ምንም ዕድገት እንዳሳ ማድረጉንም ሳይጠቅሱ አላፉም፡፡

ትርፍና ህዳግ የማኅበሩ ጥያቄ

መረጃዎች እንደሚያሳዩት ነዳጅ አዳዮች የትርፍ ህዳግ ለረዥም ጊዜ በአንድ ሌትር ሦስትና አራት ሳንቲም ነበር፡፡ አቶ ሔኖክ እንደገለጹትም፣ አንድ ሌትር ነዳጅ በአንድ ብር ገዝተን የሚታሰብልን ሦስት ሳንቲም ነበር፡፡ በ20 ብር በገዛንበት ወቅት የትርፍ ምጣኔው ሦስት ሳንቲም አግኝተናል፡፡ ስለዚህ ትርፍ ምጣኔው ሳይለወጥ ብዙ ጊዜ ተሠርቷል፡፡

ባፈለው ሁለት ዓመት ግን ትንሽ ትንሽ ጭማሪ እየተደረገ የምናገኘው ትርፍ ወደ 23 ሳንቲም ደርሷል፡፡ 49 ሺሕ ሌትር ነዳጅ የሚይዝ መኪና ለማራገፍ አሁን ወደ 1.2 ሚሊዮን ብር ይፈጃል፡፡ ይህንን ያህል ብር አውጥተን የተረከብነው ነዳጅ የሚገኝበት ትርፍ አሥር ሺሕ ብር ብቻ ነው ስለዚህ አዋጪ አይደለም ይላሉ፡፡

የነዳጅ ሥራ ደግሞ በሚጓጓዝበት ወቅት ጉድለት የሚታይበትና ትርፍ ለማግኘት የማይችልበት ሁኔታ ስለሚኖር በቅድሚያ ክፍያ ለመሥራት ያስቸግረናል በማለት አዲሱን አሠራር እንዳይተገበር መንግሥት ያዝ ቢያደርግልን ብለው ጠይቀዋል፡፡ በትርፍ ህዳግ ዙሪያ ከመንግሥት ጋር ያልተግባባንባቸው ጉዳዮች አሉ የሚሉት አቶ ኤፍሬም ዘርፉ በቂ የሆነ የትርፍ ህዳግ አልተሰጠውም፡፡ በቅርብ ግን በስንት ውትወታና ልመናም ጭምር የተወሰነ ጭማሪ መደረጉን በመግለጸም የተደረገው የትርፍ ህዳግ ጭማሪ ያለውን ዋጋ ግሽበት ያላገናዘበ ነው ብለው ይሞግታሉ፡፡

የትርፍ ህዳግ እጅግ አነስተኛ በመሆኑ የነዳጅ አዳዮች ምንም ዕድገት ሳያሳዩ ባሉበት ለመቀጠላቸው ዋናው ምክንያትም ይኼው የትርፍ ህዳጉ መጠን አነስተኛ መሆን ነውና ይህ መለወጥ አለበት ይላሉ፡፡  

የማኅበሩ የቦርድ አባል የሆኑት አቶ አፈወርቅ ጥላሁን በበኩላቸው፣ አሁን እንዲተገበር የሚፈለገውና በጥሬ ገንዘብ ግዙ የሚለው አሠራር ይበልጥ የሚያሠጋቸው አሁን ካለው የነዳጅ እጥረት ሳቢያ ይህ አሠራር ከተጫረ የባሰ ይሆናል ይላሉ፡፡

አንድ በመቶ ትርፍ የሌለው ሥራ ይዘን በ16 በመቶ ከባንክ ተበድሮ በጥሬ ገንዘብ እየከፈሉ ሥራውን ማካሄድ ስለማይቻል ነገሩ አስቸጋሪ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ እንዲህ ባለው ሁኔታ ባንክስ ያበድሩናል ወይ? ባንክ የሚበደረው ገቢና ወጪውን አይቶ በመሆኑ፣ ተገባ የተባለው አሠራር ችግር እንዳያመጣ መንግሥት ሁኔታውን ማየት እንደሚኖበትም አስገዝበዋል፡፡ መንግሥት ይህንን አሠራር ከመተግበሩ በፊት ሁኔታውን ይገምግም እስከዚያም ጊዜ ይስጠው ብለዋል፡፡

ለብዙ ዓመት በ0.4 በመቶ ትርፍ ሥንሠራ ነበር ያሉት ሌላው የቦርድ አባል አቶ ደምሴ ይህ የትርፍ ህዳግ አነስተኛ ስለመሆኑ በተመሳሳይ መንገድ የነዳጅ ዋጋን በየወሩ ከሚከልሱት እንደ ደቡብ አፍሪካ ያሉ አገሮች 7.5 በመቶ ነው የሚያገኙት በማለት የኢትዮጵያ የነዳጅ አዳዮች የትርፍ ህዳግ መጠን አነስተኛ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡ እዚህ ግን 7.5 በመቶ ይሰጠን ሳይሆን፣ አንድ በመቶ ብቻ የሰጠ ነው ብለዋል፡፡   

የውጭ ኩባንያዎችና የነዳጅ አዳዮቹ ብሦት

በአሁኑ ወቅት ካሉ 35 ከሚደርሱ የነዳጅ ኩባንያዎች ሁለቱ የውጭ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለት የውጭ ኩባንያዎች ግን ተፅዕኖ እየፈጠሩብንም ነው ብለው ያመለክታሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በተለይ የውጭ ኩባንያዎቹ በተለያየ መልክ እየጎዳቸው ስለመሆኑ የማኅበሩ አመራሮች ይገልጻሉ፡፡

መንግሥት ለማደያዎች የትርፍ ህዳጋችን በሚያሳድግበት ወቅት ኩባንያዎቹ እየጠበቁ በኪራይ መልክ ይወልዱቡናል የሚሉት የማኅበሩ አመራሮች የሚሉት የማኅበሩ አመራሮች ስለዚህ ዛሬ የምናገኘው 23 ሳንቲም ትርፍ ይባል እንጂ በኪራይ ሰበብ የሚወሰድብን ገንዘብ 23 ሳንቲሙንም እየወሰዱብን ነው ብለው ያማርራሉ፡፡

የነዳጅ ዋጋ በመንግሥት የሚተመን ነው፡፡ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት የትርፍ ህዳግ የሚቀመጠውም በመንግሥት ነው፡፡ የትራንስፖርተሮች የኩባንያዎችን የነዳጅ ቸርቻሪዎችን የትርፍ ህዳግ በመወሰን የሚሠራ ነው በነፃ ገበያ የሚሠራ አይደለም፡፡   

የትርፍ ህዳጉ ላይ መጨመር አይችሉም፡፡ ኩባንያዎቹም ከእኛ የትርፍ ህዳግም መውሰድ አይችሉም፡፡ ነገር ግን በተለያየ መንገድ በኪራይና በመሳሰሉት ሰበቦች የነዳጅ ኩባንያዎቹ ከነዳጅ አዳዮቹ ያልተገባ ክፍያ ይወስዱታልና ይህንንም መንግሥት ያስቀምጥልን በማለት የማኅበሩ አመራሮች ይጠቁማሉ፡፡

የዘይት ሥርጭትና ሕገወጥ ተግባር

የነዳጅ ቸርቻሪዎች ከነዳጅ ሽያጫቸው ባሻገር የተለያየ የሞተር ዘይቶችንም በመሸጥ ይታወቃል፡፡ በማደያዎቻቸው ውስጥ እንደየ ካፌ የላቫጆ (መኪና ዕጥበት) የጎሚስታ አገልግሎቶችንም በመስጠት ይታወቃል፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህ ድርብ አገልግሎቶች በተለያየ መንገድ ከእጃቸው እየወጣ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም የዘይት ሽያጭ ግብይቱ ከማደያዎች ውጪ እየሆነ መቸገራቸውን አመልክተዋል፡፡

በአንፃሩ ግን የማኅበሩ አባላት የነዳጅ ችርቻሮ የትርፍ ህዳግ ይደረግልን ብለው ሲጠይቁ፣ ከሚሰጡ ምላሾች አንዱ የሞተር ዘይት ሽያጭ የምታገኙት ትርፍ ከፍተኛ በመሆኑ በዚያ ታካክሳላችሁ ሲባል ቆይቷል፡፡ በእርግጥም ከዘይት ሽያጭ የሚገኘው ትርፍ ከፍተኛ ቢሆንም፣ የነዳጅ ኩባንያዎቹ ለነዳጅ ቸርቻሪዎች የሚሰጡትን ዘይት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሳቸው ማደያዎቹ ገቢ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ በዘይት ግብይቱ በአጠቃላይ የተቃወሰ መሆኑንና አንዳንድ የነዳጅ ኩባንያዎችም ዘይቱን ከማደያ ውጪ ባሉ መደብሮች እንዲሸጥ በማድረግ፣ ተገልጋዮች በተመጣጣኝ ዋጋ ገዝተው እንዳይጠቀሙ በማድረግ ጭምር ችግር እየፈጠረ ነው፡፡ ይህም ማደያዎችን እየጎዳ ከመሆኑም በላይ በአጠቃላይ የግብይት ሥርዓቱ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ ከማደያ ውጪ የሚደረግ የዘይት ግብይት ከሕገወጥ አሠራር እንደሰፋ ብሎም የዘይት ዋጋ በሚወጣበትና በሚወርድበት ጊዜ የተፈለገው ዋጋ እየተተከለ እየተሸጠ ነው በማለት ያለውን ችግር አስረድተዋል፡፡

በ400 ብር መሸጥ ያለበት ዘይት ጠፋ ተብሎ እስከ 1,200 ብር እንዲሸጥ የሚደረገውም በግብይቱ ላይ ቁጥጥር ያለመደረጉ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡ በገበያ አግባብ ግብይቱ አለመፈጸሙም መንግሥት ከዘይት ሽያጭ ማግኘት የሚገባው የታክስ ገቢ እንዳያገኝ እያደረገ በመሆኑ መንግሥት ዕርምት እንዲወስድም አሳስበዋል፡፡

የማኅበሩ የሕግ አማካሪ አቶ በሱፈቃድ አማረ በበኩላቸው በዘይት ግብይት ዙሪያ ያለው ችግር በርካታ ነው ይላሉ፡፡ ዘይቱን ኩባንያዎች የሚያስገቡ ቢሆንም፣ መንግሥት ዘይቱን በልዩ ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ በመፍቀድ እንዲገባ ያደርጋል፡፡ ዘይት ወሳኝ ስለሆነ የንግድ ሚኒስቴር ዋጋ ለኩባንያው ዘይቱን በዚህ ዋጋ ይሸጥ ብሎ ይወስናል፡፡ ኩባንያው ደግሞ ለነዳጅ አዳዮች በተተመነው ዋጋ ያከፋፍላል፡፡ ነገር ግን ኩባንያዎቹ ለነዳጅ አዳዮች ከመስጠት ይልቅ ለኪዎስኮች ያለ ተመን ማሠራጨታቸው በግብይቱ ላይ ችግር ይፈጥራል፡፡ ይህም ገበያውን አበላሽቶታል፡፡ ኪዮስኮቹ በፈለጉት ዋጋ ይሽጡ፣ ሌሎች ያልተገቡ ሥራዎችም ይሠራሉ፡፡ መንግሥትም የነዳጅ አዳዩም እየተጎዳ ነው፡፡ ይህንን ቢያስተካክል እንኳን ነዳጅ አዳዩ አቅም ሊፈጥርም ይችላል በማለት ችግሩን ተናግሯል፡፡

የጌታና የሎሌ ስምምነት

የማኅበሩ አመራሮች ችግራቸው ዘርፈ ብዙ ነው ብለው ከጠቀሱት ውስጥ ከነዳጅ ኩባንያዎች ጋር ያላቸው ስምምነት የሕግ መሠረት የሌለው መሆኑ ነው፡፡ የሚገርመውና የሚያሳፍረው የነዳጅ አዳዮቹና የነዳጅ ኩባንያዎቹ ስምምነት የመንደር ስምምነት በማለት አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ደምሴ፣ ስምምነቱ የአንድን ወገን መብት የሚያስከብር እንጂ፣ ሁለት ወገኖች በሕግ አግባብ የተዋዋሉት ስምምነት አይደለም፡፡ አሁን ተፈራርመን የምንሠራበትን ውል በሰነዶችና ምዝገባ እናፅድቀው ስንል ከፈለጋችሁ ሥሩ ካልፈለጋችሁ ተውት መባላቸውን ነው፡፡ ስለዚህ ይህ የዘርፉ ሌላው ችግር በመሆኑ መንግሥት ይይልን ብለዋል፡፡ አሁን ባለው ስምምነት መሠረት ነዳጅ ኩባንያው አንድን ነዳጅ አዳይ ጥፋት ሠርተሃል ከተባለ በአንድ ወር ውስጥ ሥራውን የሚያስቆምበት አንቀጽ ሁሉ ያለው በመሆኑ በደላችን የበዛ ነው ይላሉ፡፡

ለኪራይ እያሉ የሚያስከፍሉትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሆኑ ነዳጅ አዳዮች እየተቸገሩ ነው ተብሏል፡፡ ስለዚህ ስምምነታቸውን የጌታና የሎሌ ስምምነት ሆኖ ተቸግረናል የሚሉት አቶ ደምሴ እንዲህ ዓይነት ስምምነቶች በውል ክፍፍል መፅደቅ እንደሚኖርባቸው ቢታወቅም፣ ሕግ ተጥሶ እየተሠራ በመሆኑ መንግሥት ይህንም ማወቅ አለበት ብለዋል፡፡

አንድ ሰው ቤት ሠርቶ ቤቱን ሊያከራይ ይችላል፡፡ ኩባንያዎቹ ነዳጅ ከማደያ ሠርተው የራሳቸውን ነዳጅ የሚሸጥበት ነው፡፡ የእነሱ ሥራ እየተሠራ መልሰው ኪራይ መጠየቃቸው አግባብ አይደለም፡፡ እንዲያውም አገልግሎቱን ካልሰጠን ለእኛ መክፈል አለበት እንጂ እንደገና ኪራይ ክፈሉ ተብሎ መጠየቅ አልነበረብንም አሁን ግን ኪራዩን ምረነዋል፡፡ ለምሳሌ ቶታል እስከ 70 በመቶ ዋጋ ጨምሮብናል በማለት አቤቱታቸውን ያቀርባሉ፡፡

አቶ አፈወርቅ በበኩላቸው፣ በኩባንያውና በማደያው መካከል ያለው ውል በሚመለከተው አካል መፅደቅ ሲገባው፣ ባለመፅደቁ ለኩባንያዎቹ የምንከፍለውን ኪራይ እንኳን የገቢዎች ሚኒስቴር እንደ ወጪ አንይዝም ወደሚለው ነገር አስቸጋሪ ነው ብለዋል፡፡ በውልና ማስረጃ ስላልፀደቀ ተቀባይነት የለውም ስለሚባል ወጪው እየተጣለበት ነው፡፡

እናንተስ ዘንድ ችግር የለም?

የነዳጅ አዳዮች ችግር በዚህ መንገድ የገለጹ ቢሆንም፣ ብዙ ነዳጅ ማደያዎች ከሥነ ምግባር ውጪ በርካታ አላስፈላጊ ሥራዎችን እየሠሩ መሆኑ የሚገለጽ በመሆኑ እናንተስ ሥነ ምግባር ጠብቆ መሥራት ላይ ያላችሁ አስተያየት ምንድነው የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡ በዚህ ጥያቄ ላይ ምላሽ የሰጡት አቶ ኤፍሬም ችግሩ መኖሩን አምነው፣ ይህ ችግር ግን የሁሉም ያለመሆኑንና በተለያየ ደረጃ የሚገለጽ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ችግር ፈጣሪዎች እንዳሉ ሁሉ በአግባቡ የሚሠሩ እንዳሉ መታወቅ አለበት፡፡ ነገር ግን አለ ለሚባለውም ችግር የመንግሥት ቁጥጥር ማነስ ጭምር መሆኑን መታወቅ አለበት ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከ800 በላይ የነዳጅ ማደያዎች በአገሪቱ ያሉ ሲሆን፣ 35 የነዳጅ ኩባንያዎች ፈቃድ ወሰደው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ ከ40 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው የነዳጅ አዳዮች ማኅበር 120 አባላት ያሉት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች