‹‹ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባ›› ይባላል፡፡ አባባሉን አጀብ የሚያሰኝ አንድ ጉዳይ ሳይሰማ ዘመን አይለወጥም በሚለው ግርድፍ ትርጉም መንዝረነው እንለፍ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የምንሰማቸው ጉዶች በዝተዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጉድ ብለን ያወጋነው አንድ ጉዳይ አነጋጋሪነቱ ሳያበቃ ሌላኛው እየተከተለ ተቸግረናል፡፡
እርግጥ ነው አብዛኞቹ ጉድ የሚያሰኙን ድርጊቶች የሚመዘዙት ቀደም ብሎ መሠረት ከጣለው ብልሹ አሠራር ነው፡፡ ይህም የሌብነት ዓይነቶችና ሕገወጥ ተግባራትን በዓይነት በዓይነት እንድንሰማ አድርጎናል፡፡ ለራስ ጥቅም እንጂ ለሕዝብና ለአገር የሚሠራ የጠፋ እስኪመስል ድረስ ትንሹም ትልቁም በቀጥተኛው መንገድ ሠርቶ ማግኘትን ትቶ በአቋራጭ ሲሸፍጥ እናያለን፡፡ ‹‹የቤት ያለህ›› የሚል ዜጋ እያለቀሰ ሌላው በመሻረክና ሥልጣኑን ተመክቶ የሕዝብን ዕድል ሲነጥቁ እናያለን፡፡
የኮንዶሚኒየም ሕንፃ ጠፋ ሲባል እውነት መሆኑን የነቃነው ዘግይተን ነው፡፡ የከተማ መሬት በምን ያህል ሁኔታ ሲዘረፍ እንደነበር የሰማነው በቅርብ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ውስጥ ባለቤት አልባ ሕንፃዎች ቁጥር የትየለሌ መሆናቸውን በአኃዝ ተደግፎ ዕወቁት የተባልነውም አምና መገባደጃው ላይ ነው፡፡ በእነዚህ ወሬዎች የደነቆረው ጆሯችን አረፍ ሳይል የቤቶች ኮርፖሬሽን ኦዲት ተደርጎ አያውቅም ተብሎ የተነገረውን ዜና ከሰማን ገና ወር አልሞላውም፡፡
እንዲህ ያሉ አጀብ የሚያሰኙ ወሬዎች የመጣንበት መንገድ ዘርፈ ብዙ ሌብነቶች በሕጋዊ ስም የተፈጸሙበት እንደነበር ያሳየናል፡፡ አገር አስተዳድሩ የተባሉ ቱባ ባለሥልጣናት ሳይቀሩ ተመሳጥረው የዚችን አገር ሀብት ዘርፈዋል፣ አዘርፈዋል፡፡ ጦሳቸው ግን ዛሬም አልጠፋ ብሎ አጭበርብሮ ለመክበር የሚሹ የብዙ መሰሎቻቸው ሌብነት ቀጥሏል ሊባል ይችላል፡፡
ዛሬም አጀብ የሚያሰኙ ሕገወጥ ተግባራትን እንሰማለን፡፡ በቅርቡ አገር በዘይት እጥረት በምትታመስበትና የዘይት ዋጋ ተሰቀለ ተብሎ ደሃው፣ ‹‹ኧረ ምን ተሻለን?›› በሚልበት ወቅት በሚሊዮን ሌትር የሚቆጠር ዘይት በሕገወጥ መንገድ ከአንድ መጋዘን ተገኘ የመባሉን ዜና ሰምተናል፡፡
ይህ የዘይት ጉዳይ እንደ ቀላል የሚታይ ባለመሆኑ ነገሩን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተመልክቶ መፈተሽና የእርምት ዕርምጃ መውሰድ ይገባል፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮችን በቀላሉ ማስቆም ከባድ በመሆኑም የቅንጅት ሥራ ይጠይቃል፡፡
ጉዳዩ የአንድ ሰሞን መነጋገሪያ፣ እያደርም መታለፍ የሌለበትና ነገሩን ከሥር መሠረቱ አጥርቶ ድርጊቱን ለአደባባይ ማብቃት የሕገወጥ ተግባሩን ተሳታፊዎችም እከሌ ከእከሌ ሳይባል ሕግ ፊት ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡
በዚህ ድርጊት ዙሪያም በርካታ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት አለባቸው፡፡ አገር የተቸገረበት ምርት በሕገወጥ መንገድ መሸሸጉ ሳያንስ፣ በሕገወጥ መንገድ የተከማቸውን ዘይት ጥቅም ላይ ለማዋል የተሄደበትም መንገድ ቢሆን ጉድ የሚያሰኝ ብቻ ሳይሆን ሁኔታውን የሚያወሳስብ ስለመሆኑ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡
ከዚህም ሌላ የድርጊቱን ፈጻሚ ለሕግ ማቅረብ ለምን ዘገየ የሚለውም ጉዳይ መታሰብ አለበት፡፡ የፓልም ዘይት በመንግሥት ድጎማ የሚገባ ነው፡፡ ድጎማ ብቻ ሳይሆን ለኅብረተሰቡ መሠረታዊ የሚባል ምርት ስለሆነ፣ ሌሎች ምርቶችን አዘግይቶ ለፓልም ዘይቱ በልዩ ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ እንዲመደብለት ተደርጎ የሚገባ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ይህንን መሠረታዊ ምርት የሚያቀርቡ ውስን ነጋዴዎች ወይም ተቋማት ናቸው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የዘይት አስመጪዎቹ በየጊዜው ያስመጡትን ምርት በምን ዓይነት መንገድ እንዳከፋፈሉ ምን ያህል፣ መቼ፣ የገባውና የወጣው ጭምር ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሪፖርት ማድረግ የሚጠበቅባቸው ስለሆነ፣ ይህም ፈጻሚውን ለማወቅ የሚቻልበት መንገድ ስለመኖሩ ያመለክታል፡፡ ግን አልሆነም ለምን? ስለዚህ ይህንን ሕገወጥ ተግባር የፈጸመውን አካል በቀላሉ ማወቅ ይቻላል ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ እየሰማን ካለነው ዜና አንፃር ገና ከጅምሩ ዘይቱ በመጋዘኑ ውስጥ ተደብቆ መገኘቱን እንጂ ማን እንዳስቀመጠው እስካሁን የጠራ መረጃ ያለመሰጠቱን ሳንዘነጋ ማለት ነው፡፡
በዚህ ዘይት ጉዳይ ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ተገኘ የተባለው ዘይት መጠን በትክክል ያለመገለጹ ነው፡፡ አንዴ ሁለት ሚሊዮን ጀሪካን ሲባል በሌላ ጊዜ ደግሞ ሁለት ሚሊዮን ሌትር ተብሎ መገለጹ በራሱ አንድ ስህተት ነው፡፡ በዚህ አኃዝ ላይ ተፈጠረው ክፍተት ራሱን የቻለ ሌብነት የነበረበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ትክክለኛው መጠን ታዛቢዎች ባሉበት ተቆጥሮ አለመገለጹ አግባብ አይደለም፡፡ ስለዚህ ይህም ሕጋዊ አሠራሮች እንዴት ናቸው የሚለውን ጥያቄ ያስከትላል፡፡
በሕዝብ ሀብት የተገዛ ዘይት በተወሰኑ ቡድኖች ተደብቆ መገኘቱ ሳያንስ፣ እንደገና ሌላ ያልተገባ ድርጊት ተፈጽመዋል የምንልበት ሌላው ምክንያት ተደብቆ የተገኘውን ዘይት ጥቅም ላይ ለመዋል ከአዲስ አበባ አስተዳደር የተሰጠው ውሳኔ ነው፡፡ ይህም በትክክል ቁጥሩ ያልተገለጸውን ፓልም ዘይት 24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለሸማቾች እንዲከፋፈል አደርጊያለሁ ማለቱ ነው፡፡ እንዴት … እንዴት? ያስብላል፡፡
እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ ዘይቱ በሸማቾች ማኅበር በኩል ይሠራጭ ሲባል፣ በሕገወጥ መንገድ የተያዘው ዘይት በየትኛው የሕግ አግባብ ርክክብ ተፈጽሞና ተደርጎ፣ በየትኛው የሕግ አግባብ መልሶ እንዲሸጥ ተደረገ የሚለውን ወሳኝ ጥያቄ ስለሚያስነሳ ነው፡፡
ጥያቄው በዚህ ብቻ የሚያበቃ አይሆንም፡፡ በፍጥነት ለሸማቾች ተሠራጨ የተባለው ተሸሽጎ የተገኘው የፓልም ዘይት እንዲሸጥ ሲደረግ ከሽያጭ የሚገኘው ገቢ በየትኛው ሕጋዊ አካል አካውንት ገባ? ይህ መታወቅ አለበት፡፡ ስለዚህ ሕገወጥ በሆነ መንገድ የተገኘው ዘይት ጥቅም ላይ ሲውልም ሕግን በተከተለ መንገድ ካልሆነ በወንጀል ላይ ወንጀል ይሆናል፡፡ ስለዚህ የዚህ የዘይት መዘዝ ቀላል አይሆንም፡፡
የዚህ ዘይት ጉድ ሌላም ጥያቄ እንድናነሳ ያደርገናል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ከተሰጡ የተለያዩ አስተያየቶች መረዳት እንደሚቻለው እንዲህ ያለው ውንብድና የሚፈጸመው ለሆዳቸው ባደሩ የመንግሥት ኃላፊዎች ትብብር ጭምር በመሆኑ አሁንም ይህ ዘይት እንዲገባ ኃላፊነት የወሰደው መንግሥታዊ አካል ዘይቱ ከገባ በኋላ ዘይቱ የት ደረሰ? ብሎ አለመጠየቁም ሌላ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ጉዳይ ነው፡፡
ባፈለው ሰሞን ዘይት ጠፋ ሲባል በተለይ ንግድ ሚኒስቴር የዘይት ዋጋ መሸጥ ያለበት በዚህ ነው ብሎ ከመግለጽ ሌላ ዘይት ጠፋ ብሎ አብሮ ሲያለቅስ እንደነበር መዘንጋት የለበትም፡፡ ስለዚህ በሌለ ውጭ ምንዛሪ የገባው ዘይት መድረሻውን አለማወቅ በራሱ ተጠያቂ ሊያደርገው አይችልም? ዶላር መፍቀድ ብቻ ሳይሆን ጭንቅ የመጣ ምርት በአግባቡ ለኅብረተሰቡ መድረስ ካልቻለ ሁሉ ነገር ከንቱ መሆኑም ግልጽ ነው፡፡
አሁንም ሌላ ጥያቄ! የተደበቀው ዘይት ተገኘ በተባለ ማግሥት በሕገወጥ መንገድ ከአዲስ አበባ ሊወጣ ነበር የተባለው በሦስት አይሱዙ ተሽከርካሪ የተጫነ ዘይት መያዙ ነው፡፡ ተያዘ የተባለው ዘይት ለሌሎች ጭልፊቶች ሲሳይ ሆነ ወይስ? ብሎ መጠየቅም ክፋት የለውም፡፡ ድርጊቶቹ አሁንም ለሌላ ወንጀል በር እየከፈቱ ነውና ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡
ዘይቱ የጉምሩክ የአሠራር ሥርዓትን ተከትሎ ይግባም አይግባ ይህንን ያህል መጠን ያለው ዘይት ያለ ችግር ተጓጉዞ ሲሸሽግ ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ምን ሲሠራ ነበር? የሚለውን እንድንጠይቅ ይጋብዛል፡፡ ጉዳዩ ብዙዎች እንዲፈተሹም ጥሩ መነሻ ይሆናል፡፡ እንዴት እንደተሠራጨም እንደገና ይጣራ፡፡ ወንጀለኞችም ለፍርድ ይቅረቡ፡፡ ሕዝብ እያለቀሰ እነሱ የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ያደረጉት ድርጊት ይቅር የማይባል ነው፡፡ አስተዳደሩም ቢሆን የጉዳዩን መጨረሻ ሊነግረን ይገባል፡፡ በዚህ ዙሪያ የወሰነው ውሳኔ ምን ያህል አግባብ ነው የሚለውም መገለጽ አለበት፡፡
ይህ ብቻ ሳይሆን አሁን በአጋጣሚ እንደተያዘው ፓልም ዘይት ሁሉ ፍተሻ ቢደረግ በሌሎች መሠረታዊ ምርቶች ላይም ተመሳሳይ ድርጊት ሊገኝ ይችላል፡፡ ያለዚያ አሁንም ፍተሻ ማድረግና በሕገወጥ መንገድ በሚፈጸሙ ድርጊቶች የሚፈጠሩ የዋጋ ንረቶችን የመቆጣጠር አቅምን ማሳደግ ግድ ይላል፡፡ በመጨረሻ ግን የፓልም ዘይቱን ጉዳይ በተመለከተ ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተሰሙ ያሉ አስተያየቶች እንደተጠበቁ ሆነው ዘይቱን መሸሸግ ያስፈለገው ያላግባብ ለመበልፀግ ታስቦ ብቻ ባይሆንስ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ሸፍጥ በመፍጠር መንግሥት ላይ ጫና ለመፍጠር ታስቦ ቢሆንስ የጉድ አገር!