በኢትዮጵያ አዲስ የለውጥ ፖለቲካ ምዕራፍ ከተከፈተ ወዲህ በግንቦት ወር 2013 ዓ.ም. የሚካሄደው የመጀመርያው አገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያን ውስብስብ የሰብዓዊ መብቶች ችግር ለመፍታት ወሳኝ የሆኑ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችል ዕድል ይፈጥራል የተባለና ባለስድስት ነጥብ የሰብዓዊ መብቶች አጀንዳ ቀረበ፡፡ አጀንዳውን ያቀረበው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሲሆን፣ ሁሉም የምርጫው ተሳታፊ ባለድርሻ አካላት በተለይም የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመንግሥት አካላት፣ የሲቪል ማኅበራትና የሚዲያ ተቋማት ባለስድስት ነጥብ የሰብዓዊ መብቶች አጀንዳ ለማክበር፣ ለመፈጸምና ለማስፈጸም በይፋ ቃል እንዲገቡና በገቡት ቃል መሠረት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ኮሚሽኑ ጥሪውን ያቀረበው አገራዊ ምርጫው ሰብዓዊ መብቶች የተከበሩበት፣ ተዓማኒና ሰላማዊ የምርጫ ሒደት መሆኑን ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም ለሰብዓዊ መብቶች ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ የሚሆኑ መሠረታዊ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ እንዲያስችል መሆኑን አስታውቋል፡፡
በዚህም መሠረት በምርጫ የሚወዳደሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ዕጩዎች በሙሉ ምርጫውን ካሸነፉ ሰብዓዊ መብቶችን ለማክበር፣ ለማስከበርና ለማሟላት የሚወስዷቸውን ተጨባጭ ዕርምጃዎች በምርጫ መወዳደሪያ ጥሪ ሰነዳቸው (ማኒፌስቶ) ውስጥ በግልጽ እንዲያስቀምጡና በተለይም ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን፣ ሕፃናትን፣ የአካል ጉዳተኞችን፣ ህዳጣንን፣ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችንና ስደተኞችን ሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ በተመለከተ የሚወስዱዋቸውን ተጨባጭ ዕርምጃዎች ለሕዝብ በይፋ እንዲያሳወቁና ቃል መግባት አለባቸው ብሏል፡፡
በመንግሥት ሥልጣን ላይ የሚገኙም ሆነ ሌሎች ዕጩዎችና ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ በአጠቃላይ የምርጫ ሒደቱ ሰብዓዊ መብቶችን አክብረው በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ብቻ እንዲንቀሳቀሱ፣ በአባላቶቻቸውና በደጋፊዎቻቸው የሚፈጸምን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንደማይታገሱ በይፋ እንዲያስታውቁ፣ እንዲሁም በአባሎቻቸው የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በመመርመር ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ግልጽ የሆነ የውስጥ አሠራር በመዘርጋት ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጡ ጠይቋል፡፡
ምርጫ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሴቶችን ተሳትፎ ለማሻሻል ግልጽ አመላካቾች ያሏቸውን ሥልቶች በመንደፍ እንዲተገብሩ፣ እንዲሁም ሁሉም ባለድርሻ አካላትም የምርጫው ሒደቶች በሙሉ ለሥርዓተ ፆታ ምላሽ ሰጪ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ኢሰመኮ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በምርጫው ያሸነፉም ሆነ የተሸነፉ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሁሉም ፓርቲዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ያለውን ውስብስብ የፖለቲካና የሰብዓዊ መብቶች ቀውስ በዘላቂነት ለመፍታት፣ እንዲሁም ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት የሆኑ የሕግ፣ የፖሊሲና የአስተዳደር ጉዳዮችን ለመፈተሽና በሰብዓዊ መብቶች መርሆች ላይ የተመሠረተ እንዲሆን አስፈላጊውን የሕግና የፖሊሲ ማሻሻያዎች ለማድረግ በይፋ ቃል እንዲገቡና እንዲተገብሩ ሲል ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡
የፌዴራልና የክልል መንግሥት አካላት በተለይም የፀጥታ አካላት ተግባራቸውን በገለልተኝነትና በከፍተኛ ኃላፊነት ስሜት በመወጣት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችና ዕጩዎች፣ እንዲሁም ሚዲያና ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችንም ጨምሮ ያለ ምንም ገደብ፣ ክልከላ፣ አድልኦ፣ አግባብ ያልሆነ ጣልቃ ገብነት ወይም የበቀል ዕርምጃ በሙሉ ነፃነት መንቀሳቀስ፣ መረጃ ማግኘት፣ መደራጀትና ሐሳባቸውን በነፃነት መግለጽ እንዲችሉ፣ እንዲሁም የፖለቲካ ተሳትፎ መብቶቻቸው በሙሉ መጠበቃቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው አስታውቋል፡፡
ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ዕጩዎች፣ የሚዲያ ተቋማት፣ ሲቪል ማኅበራትና የማኅበረሰብ አንቂዎች በሁሉም የምርጫው ሒደቶች በአጠቃላይ ግጭት ቀስቃሽ፣ ጥላቻና ለመብት ጥሰት ምክንያት ከሚሆኑ ንግግሮችና ተግባራት፣ በተለይም ከማናቸውም ዓይነት የኃይል ዕርምጃ ፈጽሞ እንዲቆጠቡ ሲል ነጥቦቹን አጠቃሏል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ ‹‹የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ በአገራዊ ምርጫው አጀንዳ እንዲሆን ማድረግ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት በኮሚሽኑ የተቀመጡትን የሰብዓዊ መብት አጀንዳ ነጥቦች አትኩሮት ሰጥተው እንዲመለከቷቸው፣ ቃል እንዲገቡ በጠየቅናቸው ጉዳዮች ላይ የሚገቡትን ቃል ኪዳን እንዲያሳውቁና በአጀንዳው በተቀመጠው መሠረት ሰብዓዊ መብቶችን በማክበር እንዲቀሳቀሱ፤›› ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።