የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን አራት የመንገድና ሁለት የመንገድ ዳር መብራት ዝርጋታዎችን ያካተተ፣ በአጠቃላይ ስድስት ፕሮጀክቶችን በ1.2 ቢሊዮን ብር ለማስገንባት ከአምስት አገር በቀል መንገድ ተቋራጮች ጋር የካቲት 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ስምምነት ተፈራረመ፡፡
ግንባታው 9.24 ኪሎ ሜትር የሚሆኑ የአስፋልት መንገዶችና 7.77 ኪሎ ሜትር የሚሆኑ ደግሞ በኮንዶሚኒየም ቤቶች አካባቢ በኮብልስቶን ንጣፍ፣ እንዲሁም በቂርቆስና በአራዳ ክፍላተ ከተሞች የመንገድ ዳር የመብራት ዝርጋታን አቅፎ የያዘ ፕሮጀክት መሆኑ ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሞገስ ጥበቡ (ኢንጂነር) እንደገለጹት፣ ለኅብረተሰቡ የመንገድ ተደራሽነትን በማስፋትና የከተማዋን ዕድገት ዘላቂነት ባለው መንገድ ለማስቀጠል ይህ ፕሮጀክት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡
ፕሮጀክቶቹም ኮተቤ ኪዳነ ምሕረት አካባቢ፣ በሻሌ ኮንዶሚኒየም፣ ፋኑኤል ወታደር ሠፈርና ፉሪ ሃና አካባቢዎችን የአስፋልት ግንባታና የኮብልስቶን ንጣፎችን የሚያካሂድ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸው፣ የመንገድ ዳር መብራት ዝርጋታዎችን ደግሞ በቂርቆስና በአራዳ ክፍላተ ከተሞች ተግባራዊ የሚደረግ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከተለያዩ የአገር ውስጥና የዓለም አቀፍ የሥራ ተቋራጮች ጋር እየተገቡ ያሉ የመንገድ ግንባታ ስምምነቶች ቁጥር 18 መድረሱን፣ በአጠቃላይ የተያዙት ፕሮጀክቶች ርዝመት 102 ኪሎ ሜትር እንደሆነ አቶ ሞገስ (ኢንጂነር) ተናግረዋል፡፡ በአጠቃላይ 8.4 ቢሊዮን ብር እንደሚወጣባቸውም አክለዋል፡፡
በእነዚህ 18 የመንገድ ልማት ፕሮጀክቶች ከ6,000 በላይ የሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው፣ 16 ያህል ፕሮጀክቶችም በአገር በቀል መንገድ ተቋራጮች ግንባታቸው እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የፕሮጀክቱን ግንባታ በአፋጣኝ ለማስጀመር የውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን፣ የኢትዮ ቴሌኮም፣ የኤሌክትሪክ ዩቲሊቲ ተቋማትና የክፍለ ከተማ ኃላፊዎች መንገዶች በሚገነቡባቸው አካባቢዎች ማኅበረሰቡን በማስተባበር የወሰን ማስከበር ሥራውን በአፋጣኝ እንዲያጠናቅቁ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
ከኮተቤ ኪዳነ ምሕረት እስከ ኮተቤ ደኅንነት ቢሮ አካባቢ 1.52 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 20 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ‹መሆኑን፣ ይህንንም ፕሮጀክት አጠናቆ ለመጨረስ ከ245.66 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚጠይቅ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን የምሕንድስናና የግዥ ዳይሬክተር አቶ መሐመድ አወል ሰኢድ (ኢንጂነር) ተናግረዋል፡፡
የኮንትራቱ የውል ፊርማ ሥነ ሥርዓት የሚከናወንላቸው እነዚህ የመንገድ ፕሮጀክቶች በአማካይ ከአሥር እስከ 20 ሜትር የሚደርስ የጎን ስፋት ያላቸው መሆኑን፣ የመንገድ ዳር መብራት ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ከዘጠኝ እስከ 19 ወራት የግንባታ ጊዜ እንደሚወስዱ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም ባለሥልጣኑ ኅዳር 13 ቀን 2013 ዓ.ም. 49 ኪሎ ሜትር ርዝመትና ከአሥር እስከ 40 ሜትር የጎን ስፋት ያላቸው አዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በሲኤምሲ ሰሚት መጋጠሚያ፣ በቱሉ ዲምቱና በኮዬ ፈጬ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ከ2.6 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የግንባታ ሥራ መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡
ከባለሥልጣኑ ጋር ስምምነት የተፈራረሙት ማርሻን ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ጥላሁን አበበ ጠቅላላ የሥራ ተቋራጭ፣ ዋግዋሳ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ቫራይቲ ኤሌክትሮ ሜካኒካል ኢንጂነሪንግና ሰናን ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ናቸው፡፡