በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ስድስት ወራት ውስጥ ከ1.9 ብር በላይ ግምታ ዋጋ ያላቸው የገቢና ወጪ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ እንደገለጸው፣ በስድስት ወራት ውስጥ ከተያዘው ኮንትሮባንድ ዕቃ 1,988,214,981 ብር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ አንድ ቢሊዮን 608 ሚሊዮን 582 ሺሕ 897 ብር የሚገመቱ የገቢ ኮንትሮባንድ ዕቃዎችና ሕገወጥ ገንዘብ ነው፡፡ 379 ሚሊዮን 632 ሺህ 084 ብር የሚገመቱት ደግሞ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችና ከአገር ሊወጡ ሲል የተያዙ ሕገወጥ ገንዘብ መሆኑን ገልጿል፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ የተያዙት በ14 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ሲሆን፣ በሐዋሳ፣ ጅግጅጋና ድሬዳዋ የሚገኙ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ከፍተኛ የዋጋ ግምት ያላቸው የገቢ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች በቁጥጥር ሥር እንዲውል በማድረግ ቀዳሚውን ሥፍራ ሲይዙ፣ የወጪ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች ሞያሌ፣ አዲስ አበባ ኤርፖርትና በሐዋሳ ከፍተኛ ዋጋ ያለው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች የያዙ መሆናቸውም ተጠቅሷል።
ከአገር ሊወጡ ሲሉ የተያዙት ኮንትሮባንድ ዕቃዎች አደንዛኝ ዕፆች፣ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርና ማዕድናት ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ ሲይዙ ወደ አገር በመግባት ላይ እያሉ የተደረሰባቸው ዋና ዋና የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ደግሞ ተሽከርካሪዎች፣ አዳዲስ አልባሳትና ኤሌክትሮኒክስ ናቸው፡፡
ሚኒስቴሩ የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹን በመያዝ የተሳተፉ የጉምሩክ አመራርና ሠራተኞች እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ የፀጥታ አካላትን አመስግኗል።