እነሆ ከፒያሳ ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። ዕቅድ በማይገዛው አንዳንዴም ድካም መሪውን ጨብጦ የማስተዋል ቀልብ በሚከዳን ጎዳና ላይ ዛሬም በእንፉቅቅ እንጓዛለን፡፡ ሳይጀመር የሚያልቀው፣ ሳይወጠን የሚከሽፈው፣ ሳይታለም የሚፈታው ነገር ብዛት የእኔ ቢጤውን አዝሎታል። ዝለቱ ይመስላል ጎዳናውን የሽሙጥና የትችት አውድማ ያደረገው። ምፀት የዚህ ዝለት መታከሚያ ይመስላል። ከልጅ እስከ አዋቂ የተራቢነት፣ የአሽሟጣጭነትና፣ የዘርጣጭነት ማዕረግ ጭኖ በፌዝ ለበቅ ይለባለባል። ግራ ዘመሙ ቀኝ ዘመሙን ‹‹ቆይ ቀንህን ጠብቅ!›› ማለቱን እንደ ቀጠለ ነው። የኑሮ ልዩነቱ እያደር መባባስ ፍርኃቱን ሲያከብድበት ከቀኝም ከግራም ወገን የሌለበት መሀል ሰፋሪ ወደሚተካው ትውልድ ዕጣ ፈንታ በሥጋት ሲያስብና ሲጨነቅ ይስተዋላል። የኅብረተሰብ መስተጋብር በሥጋትና በተስፋ፣ በማግኘትና በማጣት ውጥን ተሰፍቶ ሳለ፣ በርዶ ከመቀዝቀዝ ወይም ሞቆ ከመጋል ለብ ማለትን የመረጠው ብዙ ነው። ሁሉም በሆዱ ቋጥሮና አፍኖ ሰምቶ እንዳልሰማ ዓይቶ እንዳላየ ይኖራል። የዛሬው ተራማጅ ነገን ብቻ ተስፋ አድርጎ ይጓዛል። መኖር ደጉ መሰንበት ደጉ ጥሩ ያስተዛዝበናል። እኛ የሰው ልጆች ዛሬም በትናንቱ ጎዳና በአዲስ ተስፋ እንጓዛለን። በመቆየት ብዙ ያላየ ማን አለ!
‹‹እ! ቶሎ ቶሎ ግቡ! እዚሁ በቆምንበት እኮ የህዳሴው ግድብ ሊጠናቀቅ ነው፤›› ይላል ወያላው። ነገረ ሥራው የመዝናናት ስሜትን ያጭራል። ‹‹ጽንፈኞች አደብ ሳይገዙ ምኑን ገደብን ወንድሜ? ምኑን አገር ገነባን?›› ይላል ድምፁ የሴት ወይዘሮ የሚመስል አንድ ወጣት። ‹‹የጉልበተኞችን ሥራ ለራሳቸው ተውላቸው። እኛ እንደሆንን ሥራችን ዜና መስማት ነው፡፡ ዜና በሚሠሩት ጣጣና ጦስ ውስጥ መግባት አያስፈልግም፤›› ትላለች አንዷ ሂጃብ የጠመጠመች ወጣት። ‹‹እሱስ ቢሆን መቼ ተሳካልን?›› አንድ ጎልማሳ ጨዋታውን ተቀላቀለ። ‹‹አይዞን በ2013 ዓ.ም. የማይሳካ ነገር የለም። ብቻ እናንተ ቶሎ ቶሎ ግቡ፤›› ገብስማ ፀጉሩን ዳበስ ዳበስ እያደረገ ወያላው ይለማመጣል። ‹‹በ2013 ዓ.ም. ሁሉም ይሳካል ስትል ትንቢትህ የወቅቱን ትርዒትና ስሜት ያካትታል?›› ስትል መጨረሻ ወንበር ላይ ማንነታችንን እየረጋገጠች ገብታ የተቀመጠች የቀይ ዳማ ጠየቀችው። ‹‹ሆሆ! ኧረ እኛ የምንጫወተው በገዛ ሜዳችን ነው! በሰው ሜዳ አታጫውችኝ። ምን ይሻላል እናንተ?›› ወያላው የተቀየመ መሰለ። ‹‹አይዞን ጠላት ሸረኛውን ከጠበቀለን፣ ምቀኛ፣ ትምህክተኛውን፣ ጽንፈኛውንና ተንኮለኛውን ቅስሙን ከሰበረልን የማይሳካ ነገር አይኖርም፤›› አለች ሂጃብ ጠምጣሚዋ። ‹‹አፈር ልብላልሽ! ምናለበት እንዳንቺ በቅንነት የሚናገር ቢበረክት? ደርሶ ቅንቅን እየሆነ በነገር በልቶ የሚጨርሰን ባሰ እንጂ . . .›› ወያላው ታክሲው ስለሞላለት በሩን እየዘጋ የሆዱን ዘረገፈው። ታማሚና አስታማሚ በነገር አንድ አንድ ሲባባሉ መንገዱ ተጀመረ። የግድ ነው!
‹‹እናንተ!›› እያሉ ትልቅ ሻሽ የጠመጠሙ ወይዘሮ ተጣሩ። ‹‹አቤት እማማ?›› ወያላው ሌሎቻችን ወክሎ መለሰ። ‹‹ሬዲዮኑና ጋዜጣው ባለፈው ዓመት በርካታ ሚሊየነሮች ተፈጠሩ ብሎ የሚያወራው ምን ለማለት ፈልጎ ነው?›› አዛውንቷ የከነከናቸው ነገር ግልጽ ነበር። ግን ወያላው ብዙ እንዲያወሩ ፈልጓል። ‹‹እንዴት እማማ?›› አላቸው። ‹‹ምን እንዴት ይለኛል? ስንትና ስንት ሚሊዮን ድሆችና ምፅዋተኞች አይደሉም እንዴ አስተዋሽ እንዳጡ የሚቀሩት? አይደለም እንዴ?›› አሉ የአፍንጫቸውን ላብ በአውራ ጣታቸው አበሱ። ‹‹ኤድያ ሲኖርዎት እንጂ ከሌለዎትማ ማን ዞር ብሎ እንደ ሰው ይቆጥርና? አሁን ይኼን ለእርስዎ መንገር ምጥ ማስተማር አይሆንብንም?›› አላቸው ጎልማሳው። ‹‹ሁሉም ወዳለው ነው ወደድክም ጠላህም፣ ያንተ ነገር ሞቷል ከሌለህ የለህም ነውና . . .›› እያለ ወያላው ጥቂት በድምፁ አንጎራጎረ። ‹‹ታዲያስ! ዓለም እኮ እንደ ሸንኮራ አገዳ ነው የምትቆጥረን። ከመጠጠቻቸውና ካጣጣመቻቸው በኋላ ወዘናቸው ሲያልቅና ውኃቸው ሲደርቅ እንደ ቆሻሻ መሬት መጣል የተሠራችበት ‘ፊዚክስ’ አንድ ክፍል ሳይሆን አይቀርም፤›› በማለት የቀይ ዳማዋ ወጣት አጉረመረመች። ‹‹አይ ዓለም አታላይ!›› የሚል ጥቅስ ሥር አፍ ያልፈታ ሕፃን ትምባሆ እያቦነነ ሲተክዝ የሚያሳይ ምሥል ደግሞ ከረዥሙ ወያላ ትከሻ ከፍ ብሎ ጣሪያው ላይ ተለጥፎ ይታያል፡፡ ማን አታላይ ማን ተታላይ እንደሆነ እንጃ እንጂ!
እየሄድን ነው። ‹‹እስኪ ሾፌር ድምፁን ከፍ አድርገው፤›› አለ ጎልማሳው ጆሮውን ወደ ስፒከሩ እየጎተተ። ከወደ ስፒከሩ የሰሞኑን መነጋገሪያ ስለሆነው የውስጥ ክራሞታችን ይተነተናል። ጎልማሳው ከሁላችንም ይበልጥ ተመስጦ ሲያዳምጥ ግንባሩን ሲቋጥርና ሲፈታ ቆይቶ ከት ብሎ ሳቀ። ሾፌሩ የሬዲዮኑን ድምፅ ወዲያው ቀንሶ የሚፈልገውን ሙዚቃ ማጫወት ጀመረ። ጎልማሳው መሳቁን አላቋረጠም። ‹‹ንገረና እስቲ ምን ተገኘ?›› አሉት አዛውንቷ። ‹‹ኧረ ግድ የለም ባልናገረው ይሻለኛል። ከመናገር የተረፈን ወሬኛነት እንጂ መደማመጥና እየተሻሻለ የሚሄድ የዴሞክራሲ ባህል አይደለም፤›› አላቸው። ‹‹በተሰቀለው! አሁን ዴሞክራሲን ማን ጠራው?›› አሉት። ‹‹የሚያስቀኝ እኮ እሱ ነው። መስማት የምንፈልገው ሌላ የሚሆነውና የሚነገረን ሌላ። በዚህ በሠለጠነ ዘመን ዓለም ወደ ዘላቂ ሰላም ትጓዛለች ሲባል ወደ ዘላቂ ብጥብጥና የጦር መድረክነት ትለወጣለች። በዚህ የሰው ልጅ አስተሳሰብና አመለካከት ደረጃ መጥቋል በሚባልበት ወቅት፣ ከሌላው ጊዜ ብሶ የሰው ልጆች መብት የመጠቀሚያና የማትረፊያ ሸቀጥ መሆኑ እያሳዘነኝ ነው፤›› አላቸው። አዛውንቷ በሬዲዮ እኩል የሰማነውን የዜና ትንታኔ እያስታወሱ ጎልማሳውን አተኩረው ያዩታል። እሱ ራሱ የተቃረነች ዓለም በሚላት ዓለም እየመረጠ የሚፈልገውን ብቻ የሚያዳምጥ መሆኑን ሳያስተውሉ አልቀሩም። አቤት ግራ የተጋባው ሰውና ነገር ብዛቱ!
ጉዟችን ቀጥሏል። ከፊት ለፊታችን መኪኖች ተጋጭተው መንገዱ ተዘጋግቷል። የቀይ ዳማዋ ወጣት፣ ‹‹ውይ! መጥኔ! ስንት ሰዓት ተሠልፈን ታክሲ እንይዛለን። በመንገድ መዘጋጋትና መጨናነቅ ደግሞ ጉዟችን ይስተጓጐላል። እንዲህ ተሰቃይተን ቤታችን ስንገባ ደግሞ መብራት ይጠፋል። ኧረ መቼ ይሆን እፎይ የምንለው?›› በማለት እየተመናጨቀች ወደ ታክሲያችን ጣሪያ ቀና አለች። ‹‹እንግዲህ አንዳንዶች የህዳሴው ግድብ እስኪጠናቀቅ ብለዋል፤›› አለ ወያላው። ጋቢና ከተቀመጡ ወጣቶች ደግሞ አንዷ ቀበል አድርጋ፣ ‹‹አንዳንዶች መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ስንሠለፍ ነው ይላሉ፤›› አለች። አጠገቧ የተሰየመው ጎረምሳ ቀበል አድርጎ፣ ‹‹አንዳንዶች ደግሞ የብር ዋጋ ከዶላር ጋር እኩል ሲሆን ነው ይላሉ፤›› ሲል አዛውንቷ፣ ‹‹ምን የሚሆነው?›› አሉ ተገርመው። ‹‹ደልቶን የምንኖረው ነዋ!›› ስትል የቀይ ዳማዋ፣ ‹‹አሁን ምን እያደረግን ነው?›› አሉዋት። ልጀት ከት ብላ ትስቃለች። መልሱን ለሌሎቹ ተሳፋሪዎች ሹክ ያለች ይመስል ‹‹እያኗኗርን!›› ሲል ሁሉም ተራ በተራ መልሱን አቀበላቸው። የተጋጩትን አውቶሞቢሎች ታከን ለማለፍ ግማሽ ሰዓት ያህል ፈጀብን። በአንዱ ግጭት የአንዱ መዘግየት በአንዱ ጥፋት የሌላው ተቀጪ መሆን እንቆቅልሽ የሆነባት ዓለም ገና ብዙ ሳታባብለን አትቀርም። ዕድሜ ለመንገድ!
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ‹‹አይ ዘንድሮ!›› አሉ አዛውንቷ። ‹‹መቼ ጀመረ ገና?›› አለ ዝም ብሎ ተጎልቶ የዋለ ወጣት። ‹‹ወይድ! እንኳን ዘመንን እንኳን ጊዜን የዝንብ ጠንጋራም እናውቃለን!›› አሉትና በቁጣ ዓይናቸው ለበለቡት። ‹‹ማለት? ገና ምኑንም ሳንይዝ?›› አለ ጎልማሳው ወያላ አዛውንቷ ተመችተውት። ‹‹ሳንጠራ መጨመር የማይሰለቸን!›› አሉ እየቆዩ ሲሄዱ ሁሉም ነገር እንደ ሬት የመረራቸው የሚመስሉት አዛውንት። ‹‹በልዩነቱ ተቻችሎና ተከባበሮ አብሮ የኖረ ሕዝብ መስሎኝ ዛሬም ድረስ በጉጉትና በናፍቆት አብሮ የሚኖረው? አይደለም እንዴ?›› ወያላው ሊተዋቸው አልፈቀደም። ‹‹አንተ ተወኝ ብዬሃለሁ ዛሬ! እውነተኛ የኅብረት የድምር ውጤት እንደ ችቦ ነዶ አመድ የሚሆን ጊዜያዊ ነገር ነው ያለህ ማን ነው? እውነተኛዎቹማ አሁን የሉም። ከእነሱ በኋላ ምን ሆንን? ትልቁ ኅብረት ካልክስ እንደ ወረት የማያልቅ፣ ብርሃኑ ሺሕ ትውልድ ድረስ የሚዘልቅና ፋይዳ ባለው ልዩነት ውስጥ ቋሚ የሆነ ኅብረት ነው። አውርደኝ አሁን አታስለፍልፈኝ!›› ብለው ንግግራቸውን ቋጩ። ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ብሎ በሩን ከፈተው። ወርደን በየፊናችን ስንጓዝ፣ ‹‹ወደኋላ እየሄድን የችግራችንን ምክንያት ካላየነው እኮ በአቋራጭ እያሳበሩ መጓዝ የትም አይደርሰንም፤›› ብለው ሲጨምሩልን፣ ልካችንን እንደ ነገሩን ገባኝ፡፡ አቋራጭ ፍለጋችን ገና ያስቀጠቅጠናል እያልኩ ሳስብ የአዋቂ ያለህ የሚያሰኝ ጊዜ ላይ መሆናችን ትዝ አለኝ፡፡ በየሬዲዮኑ፣ በየቴሌቪዥኑ፣ በየማኅበራዊ ሚዲያው ራሳቸውን በራሳቸው ታዋቂ ያደረጉ በበዙበት ዘመን አዋቂዎች ለምን ጠፉ አይባልም? ይህ ያለንበት ጊዜስ አዋቂ ጠፍቶ ታዋቂ በዛ አያሰኝም? የሆነስ ሆነና ከማወቅና ከመታወቅ የቱ ይሻል ይሆን? ግራ ገባን እኮ! መልካም ጉዞ!