Saturday, May 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የመንግሥት የፋይናንስ ድርጅቶች በ2013 በጀት የመጀመርያው አጋማሽ ከታክስ በፊት 8.48 ቢሊዮን ብር አተረፉ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚገኙ ሁለቱ ባንኮችና አንድ የኢንሹራንስ ኩባንያ በ2013 ግማሽ የሒሳብ ዓመት ከ8.4 ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፋቸውና የትርፍ መጠናቸው ከዕቅዳቸው ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ያነሰ መሆኑ ተመለከተ፡፡

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ እንዳስታወቀው፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በ2013 በጀት የመጀመርያው ግማሽ ዓመት በጊዚያዊ የሒሳብ መረጃ መሠረት ከታክስ በፊት በድምሩ 8.48 ቢሊዮን ብር አትርፈዋል፡፡

አፈጻጸሙ ግን የልማት ድርጅቶቹ አቅደውት ከነበረው የ10.31 ቢሊዮን ብር ትርፍ አንፃር ሲታይ ከዕቅዳቸው የ82.26 በመቶ ወይም ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ልዩነት አሳይቷል፡፡

ሦስቱ የፋይናንስ ተቋማት በግማሽ የበጀት ዓመት ከአገልግሎታቸው እናገኛለን ብለው አቅደው የነበረው ገቢ የባንክና የመድን አገልግሎቶች በመስጠት 45.19 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ክንውናቸው 43.68 ቢሊዮን ብር ገቢ ወይም የዕቅዳቸውን 97 በመቶ ነው፡፡

ከተገኘው ከአጠቃላዩ የ8.48 ቢሊዮን ብር ትርፍ ከፍተኛውን 7.38 ቢሊዮን ብር ወይም የዕቅዱን 77 በመቶ ያከናወነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡ ይኼው ባንክ ከአጠቃላዩ የዘርፉ ትርፍ 87.08 በመቶ ያህል ድርሻ ይዟል፡፡

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት 565.5 ሚሊዮን ብር ወይም የዕቅዱን 93 በመቶ በመፈጸም ከአጠቃላዩ የዘርፉ ትርፍ በሁለተኛ ደረጃ የ6.67 በመቶ ድርሻ አበርክቷል፡፡ አፈጻጸሙን አሻሽሎ በዚህ በጀት ዓመት ወደ ትርፋማነት የመጣው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በአጠቃላይ በግማሽ ዓመቱ 530.5 ሚሊዮን ብር ሊያተርፍ ችሏል፡፡ በዚህም ለዘርፉ አጠቃላይ ትርፍ የ6.25 በመቶ አስተዋጽኦ በማድረግ ሦስተኛ ደረጃን ይዟል፡፡

የካቲት 5 ቀን 2013 .. የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ግምገማ የተካሄደ ሲሆን፣ መድረኩን የመሩት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ሀብታሙ ኃይለ ሚካኤል ናቸው፡፡ የካቲት 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ደግሞ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በመሩት መድረክ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አፈጻጸሞች ተገምግመዋል፡፡

በግምገማዎቹ ማጠቃለያ ላይ የድርጅቶቹ የመጀመርያ መንፈቅ ዓመት አፈጻጸም አበረታች መሆኑ ተጠቅሶ፣ በሀብት አሰባሰብ፣ በውጭ ምንዛሪ ግኝትና ለዘርፉ አስፈላጊ በሆነ የሰው ኃይል ልማት ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ምክረ ሐሳብ ቀርቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች