በዕዳ የተዋጡትን የመንግስት ልማት ድርጅቶች፣ እንዲሁም ለድርጅቶቹ ያበደረውን የኢትይጵያ ንግድ ባንክን ለመታደግ በመንግስት የተቀረፀው ስትራቴጂ ወደ ሥራ እንዲገባ ተወስኗል።
ይህ ስትራቴጂ የመንግስት ልማት ድርጅቶች አንገት ድረስ የደረሰውን የአገር ውስጥ ዕዳ በማቃለልና ወደ ጤናማ እንቅስቃሴ እንዲሸጋገሩ ማድረግ አንደኛው ዓለማ ሲሆን፣ ለልማት ድርጅቶቹ ከፍተኛ ብድር አቅርቦት ድርጅቶቹ መክፈል ባለመቻላቸው አደገኛ አጣብቂኝ ውስጥ የገባውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአደጋው መታደግ የስትራቴጂው ሌላ ዓላማ ነው።
በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፀደቀው ይኼው ስትራቴጂ ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት ዓላማዎች በመሠረታዊነት ማሳካት ዋና ግቡ ቢሆንም፣ ይህንን ግብ በማሳካት የኢትዮጵያ መንግስትን አጠቃላይ የዕዳ ጫና ማቅለል በሦስተኛ ደረጃ የሚጠቀስ ተሸጋጋሪ ግብ የተቀመጠለት ነው።
ሦስት ገጽታዎች ያሉትን ይህንን ዓላማ የማሳካት ሸክምና ኃላፊነት የሚወድቅበት ደግሞ የሚንስትሮች ምክር ቤት እንዲቋቋም የወሰነው (የመንግስት ልማት ድርጅቶች ዕዳና ሀብት አስተዳደር ኩባንያ) Liability and Asset management company የተባለው አዲስ ኩባንያ ነው።
ይህ ኩባንያ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለማካሄድ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ከውጭ አበዳሪዎች ተበድረው እስከ አንገታቸው ድረስ በዕዳ የተዋጡትን የመንግስት ልማት ድርጅቶች የአገር ውስጥ ብድር በመውረስ ተቋማቱን ከአደጋ አውጥቶ ወደ ተልዕኳቸው የመመለስ ኃላፊነትና በዚሁ መንገድም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ዕዳ ከፍሎ ባንኩን ከሥጋት የማውጣት ትልቅ ሸክም በዋናነት ይወስዳል።
በከፍተኛ ዕዳ ውስጥ የተዘፈቁት የልማት ድርጅቶች ሰባት ሲሆኑ በጥቅሉ 780 ቢሊዮን ብር ለንግድ ባንክ የሚከፈል ዕዳ አለባቸው። የመንግስት ልማት ድርጅቶቹም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ ስኳር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኢንደስትሪ (የቀድሞው ሜቴክ)፣ ኬሚካል ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ይገኙበታል።
የሚቋቋመው የዕዳና ሀብት አስተዳደር ኩባንያ የተጠቀሱት የልማት ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተበድረው ካልመለሱት ዕዳ ውስጥ 570 ቢሊዮን ብሩን ወርሶ እንዲያስተዳድር ኃላፊነት ተጥሎበታል።
በተወሰነው መሠረትም ኩባንያው የምድር ባቡር ኮርፖሬሽንን ዕዳን መቶ በመቶ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዕዳን 50 በመቶ፣ የቀድሞውን ሜቴክ ወይም ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ኢንደስተሪ ዕዳ 76 በመቶ፣ የኤሌክሪክ አገልግሎት ዕዳን 21 በመቶ እና የኬሚካል ኮሮፖርሽን 94 በመቶ፣ እንዲሁም የስኳር ኮርፖሬሽንን ዕዳ እንዲወርስ ተወስኖበታል።
ይህንን ኩባንያ ለማቋቋምና የልማት ድርጅቶቹን ዕዳ ወርሶ በማስተዳደር ተቋማቱንም ሆነ አበዳሪውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲታደግ ለማድረግ እንዲችልም ከኢትዮ ቴሌኮም ከፊል ሽያጭ (ፕራይቬታይዜሽን) የሚገኘውን ሀብት አመዛኙን እንዲወስድ የሚደረግ መሆኑን ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስቴር ፕሬስ ሰክሬታሪ በሚዘጋጀው ፖሊስ ማተርስ ፕሮግራም ላይ የቀረቡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ገልጸዋል።
ከፕራይቬታይዜሽን ከሚገኘው ገቢ በተጨማሪ ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሚገኝ ዓመታዊ ትርፍ ወደሚቋቋመው ኩባንያ ፈሰስ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
የገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው አጠቃላይ የዕዳ መጠን መግለጫ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ዕዳ እ.ኤ.አ. እስከ ሴፕቴምበር 2020 ድረስ ማዕከላዊ መንግሥቱ በቀጥታ እንዲሁም፣ መንግሥት በሰጠው የብድር ዋስትና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከአገር ውስጥና ከውጭ ምንጮች ተበደረው ያልከፈሉት አጠቃላይ ዕዳ 54.7 ቢሊዮን ዶላር እንደደረሰ ያመለክታል።
ከአጠቃላይ 54.7 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 28.99 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነው ከውጭ የብድር ምንጮች የተገኘ ሲሆን፣ ይህም ሰነዱ በተዘጋጀበት ወቅት በነበረ የብር የውጭ ምንዛሪ ተመን ተሠልቶ 1.06 ትሪሊዮን ብር እንደሆነ ሰነዱ ያመለክታል።
ከተጠቀሰው 54.7 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ከውጭ ብድር ምንጭች የተገኘው ተቀንሶ የሚቀረው 25.7 ቢሊዮን ዶላር ደግሞ ለአገር ውስጥ የብድር ምንጮች የሚከፈል የአገር ውስጥ ዕዳ እንደሆነ ሰነዱ ያመለክታል። ለአገር ውስጥ የብድር ምንጮች መከፈል ያለበት ዕዳ ይህ የዕዳ መጠን ሰነዱ በተዘጋጀበት ወቅት በነበረ የብር የውጭ ምንዛሪ ተመን ተሠልቶ የተቀረበ ሲሆን፣ በዚህ ሥሌት መሠረትም የአገር ውስጥ የመንግሥት ዕዳ 945 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ተጠቅሷል።
አጠቃላይ ከሆነው 54.7 ቢሊዮን ዶላር የአገር ውስጥና የውጭ የዕዳ መጠን ውስጥ 30.6 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነውን በቀጥታ ማዕከላዊ መንግሥትን የሚመለከት ሲሆን ይህም የአጠቃላይ ዕዳው 56 በመቶ ነው።
ከአጠቃላይ የዕዳ መጠን ውስጥ ማዕካለዊ መንግሥትን የሚመለከተው ከተቀነሰ በኋላ የሚቀረው 24.1 ቢሊዮን ዶላር ወይም የአጠቃላይ ዕዳው 44 በመቶ የሚሆነው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ዕዳ ነው።
ከአጠቃላይ የዕዳ መጠን ውስጥ 25.7 ቢሊዮን ዶላር ወይም 945 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ከአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት የተወሰደ ሲሆን፣ በአመዛኙም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተወሰደ መሆኑን ሰነዱ ያለመለክታል።
ከተጠቀሰው የአገር ውስጥ ዕዳ 525 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን ያበደረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደሆነ መረጃው ያመለክታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከጥቂት ወራት በፊት ይህንኑ ሁኔታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማስናዳታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በወቅቱ ባደረጉት ንግግርም መንግሥታቸው ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው የኢኮኖሚና የፋይናንስ ዘርፍ ሪፎርም ፈጥኖ ባይደርስ ኖሮ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመውደቅ አደጋ ተጋርጦበት ነበር ማለታቸው ይታወሳል።
አጠቃላይ የመንግሥት ዕዳ የኢኮኖሚ ዕድገት መለኪያ ከሆነው አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) 50.8 በመቶ እንደሚሆን መረጃው ያመለክታል። ከዚህ ውስጥ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች የአገር ውስጥ ዕዳ ለብቻው ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት አንፃር 12.5 በመቶ ድርሻ ይዟል።